Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, February 14, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራን ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ታገደ


የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ትላንት ከቀትር በኋላ በፓትርያርኩ የተጻፈውን የእግድ ርምጃ አልተቀበሉትም፡፡

ከ200 በላይ የጉባኤው ተሳታፊ የአብነት መምህራን አዲስ አበባ ገብተው በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጽ/ቤት ተሰብስበዋል፡፡ ፓትርያርኩ በአድራሻ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ የጻፉትን የእግድ ደብዳቤ የያዘው ፖሊስ፣ የማኅበሩ ጽ/ቤት ጉባኤተኞቹን ወደየመጡበት እንዲመልስ በማሳሰብ ላይ እንደኾነ ተነግሯል፡፡

በእግድ ርምጃው ምክንያት÷ ዛሬ፣ የካቲት ፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የአብነት መምህራኑ፣ የቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ሓላፊዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የወተር ኤይድ እና ዩኒሴፍ ተወካዮች በተገኙበት በግዮን ሆቴል ሊካሔድ የነበረው የሀገር አቀፉ የምክክር ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ተስተጓጉሏል፡፡

ጉባኤተኞቹ፣ መርሐ ግብሩን ያስተጓጎለውን የእግድ ርምጃ አስመልክቶ በማኅበሩ አመራር ማብራሪያ ከተሰጣቸው በኋላ ርምጃው እንዲወሰድ ባነሣሱት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ላይ ቁጣቸው ነዷል!!!

ቀደም ሲል በአባ ሰረቀ ግፊት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ ተላልፎ የነበረውን የእግድ ርምጃ በማንሣት የምክክር ጉባኤው እንዲካሔድ የፈቀዱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ትላንት ከቀትር በኋላ በፓትርያርኩ የተጻፈውን የእግድ ርምጃ አልተቀበሉትም፡፡
የአብነት መምህራኑ÷ የእግድ ርምጃው እንዲወሰድ ባነሣሱት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ላይ መውሰድ ስለሚገባው የተባበረ አቋም በከፍተኛ ስሜት ሐሳብ በመለዋወጥ ላይ ናቸው!! ፓትርያርኩን እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡

ጉባኤያቸውን አጥፈው ለሀገር አቀፉ ስብሰባ ከኹሉም አህጉረ ስብከት የመጡ አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ የኾኑ አዕይንተ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሳይቀሩ ተሰብስበው ሲመካከሩ ከዋሉበት ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ጽ/ቤት በሰልፍ በመውጣት ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አምርተዋል፡፡

የአብነት መምህራኑ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅጽር ሲደርሱ በሀገር አቀፉ የምክክር ስብሰባ ላይ የተላለፈውን እግድ ለማስፈጸም ከተመደበው የፖሊስ ኃይል ጋራ ስለማንነታቸውና ስለመጡበት ኹኔታ ካስረዱ በኋላ ፍተሻ! እየተደረገላቸው ወደ ቅጽሩ ዘልቀዋል፤ በእግድ ርምጃውና በአባ ሰረቀ ጉዳይ ከፓትርያርኩ ጋራ ፊት ለፊት ለመነጋገር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተገልጧል፡፡

እንደ በጋሻው ደሳለኝ ‹መጋቤ ሐዲስ›ነት በዘፈቀደ የተለጠፈላቸው ጎጋ ምንደኞች ሳይገባቸው በሚወስዱት የሊቃውንት ሥያሜና የምስክር አሰጣጥ ላይ መወያየትና እነአባ ሰረቀ ሠርተው ባለማሠራት ጥፋት የፈረዱባቸው ቤተ ጉባኤያት ወቅታዊ ተቋማዊ ኹኔታ ከጉባኤው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials