ሰማያዊ ፓርቲ በብዙ አፈና ታጅቦ በጎንደር የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ አከናወነ በጎንደር መስቀል አደባባይ በከፍተኛ ድምቀት ሲካሄድ ያረፈደው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠናቋል። ገና ከጥዋቱ ወደ ጎንደር የሚገባውን የገጠር ህዝብ ትራፊኮችና ፖሊሶች መግቢያውን ዘግተው አናስገባም ቢሉም ከዩኒቨርስቲ የሚመጣውን ተማሪ ፖሊሶች መንገድ ዘግተው እንዳያልፉ ቢያደርጉም ከየሰፈሩ ወደ መስቀል አደባባይ ያመራውን ህዝብ ለመከላከል የወያኔ ፖሊሶች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሞንታርቦ እና የሰማያዊ አመራሮችን ይዛ የነበረውን መኪና አስቁመው ለማጉላላት ቢሞክሩም....ሰልፉ ግን በታላቅ ስኬት ተጠናቋል!!!!
ሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር ህዝብን አስተባብሮ ባደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ወያኔ በሚስጥር ከሱዳን መንግስት ጋር ተደራድሮ መሬት ለሱዳን አሳልፎ መስጠቱንና ወደፊትም ተጨማሪ መሬት ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የጎንደር ህዝብ ግንዛቤ እንዲኖረው አድርጓል። በጎንደር የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበሩት ለህብረተሰቡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ባሰሙት ንግግር “በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና አምባገንን ስርዓት ውስጥ ሆናችሁ፤ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብላችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን” ካሉ በኋላ ሰላማዊ ሰልፉ ታዳሚ ይህ ሰልፍ ለምን ሊደረግ እንደቻለ አብራርተዋል። በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያም ገለጻ አድርገዋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው “ወጣቶች የሃገራችሁን ክብር ለማስጠበቅ ራሳችሁን ከፍርሃት አላቁ። ከፍርሃት እና ከሥጋት ወጥታችሁ ለሃገራችሁ አለኝታ ሁኑ” ብለዋል። ለሥርዓቱ መሪዎችም “ሥልጣን ወቅታዊ ነው፤ ያልፋል። በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ የሚጸመው ደባ ግን አያልፍም” ካሉ በኋላ ይህን ታሪካዊ ስህተት እንዲያስቆሙ በንግግራቸው ዘግበዋል።
“የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ለልጆቻቸው ጥሩ ታሪክን እንጂ ውርደትን ማውረስ የለባቸውም” በማለት የተናገሩት ኢንጂነር ይልቃል በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ስለ ዳርድንበር መከበር
“ከዚህ በኋላ ስለጀግኖቹ ንጉሦች እየዘፈኑ መኖር ያብቃ፤ ታሪካቸውም እኛም በጀግንነታችን እንጠብቀው” ሲሉ መል ዕክታቸውን አስተልፈዋል።
ዛሬ ፌብሩዋሪ 2 ቀን 2014 በጎንደር በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡ
“ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም”
“ወያኔ አይወክለንም”
“እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም”
“አባቶቻችን ያስረከቡንን መሬት አሳልፈን አንሰጥም”
የሚሉም የተቃውሞ መፈክሮችን ሲያሰማ ነበር። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የተፈጸመው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ፣ በአይነቱ በጎንደር ያልተለመደ ነው። የወያኔ ባለስልጣኖች የሰማያዊ ፓርቲ በፈጠረው ጫና ምክንያት ሰሞኑን በሚስጥር ሲያካሂዱት ስለ ነበረው የመሬት ማካለል ጉዳይ በሚቆጣጠርዋችው ሚድያዎች መናገር ጀምረዋል። ሰልፉን በተለየ መልኩ ስኬታማ የሚያደርገው፤ አፈናን፣እስርን እና ንብረት ነጠቃን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ማሰናከያዎች ሊከሽፍ አለመቻሉ ነው። የጫናዎች መደራረብ ሰልፉን አላስቀሩትም። ክስተቱ፤ ከአምባገነኖች ጋር በሚደረግ ትግል መብትን በመናጠቅ እንጂ በመጠበቅ ማረጋገጥ እንደማይቻል ለሌሎችም ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው።
No comments:
Post a Comment