Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, June 27, 2019

ዴንማርካዊ ጥንዶች የግብጽ ፒራሚድ ላይ እርቃናቸውን ሆነው የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቁጣን ከቀሰቀሰ

ዴንማርካዊ ጥንዶች የግብጽ ፒራሚድ ላይ እርቃናቸውን ሆነው የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ ግብጽ የተንቀሳቃሽ ምስሉን ትክክለኛነት ልትመረምር ነው።


ዴንማርካዊ ጥንዶች የግብጽ ፒራሚድ ላይ እርቃናቸውን ሆነው የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ ግብጽ የተንቀሳቃሽ ምስሉን በሚመለከት ምርመራ ለመጀመር ተገድዳለች።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ወግ አጥባቂ በሆነችው ሃገረ ግብጽ ከፍተና ቁጣን ቀስቅሷል።
አቃቤ ሕግ የተንቀሳቃሽ ምስሉን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው የተዘገበ ሲሆን ቪዲዮ እውነት ሆኖ ከተገኘ ጥንዶቹ 140 ሜትር የሚረዝመውን ፒራሚድ እንዴት አድረገው መውጣት ቻሉ የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው።

በግብፅ ጊዛ ከተማ የሚገኘው ፒራሚድ ከ7ቱ የዓለማችን ድንቃ ድንቅ ስፍራዎች መካከል እንዱ ነው።
ተንቀሳቃሽ ምስሉን የቀረጸው ፎቶግራፈር እንደሚለው ከሆነ እሱ እና ጓደኛው ለሰዓታት ተደብቀው ከቆዩ በኋላ የፒራሚዱ አናት ላይ መውጣት ችለዋል።
የግብጽ ባለስልጣናት ፒራሚዶች ላይ መውጣት ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አስታውሰው በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታዩት ትዕይንቶች የግብጽ ሕዝብን ሞራል የሚጥሱም ናቸው ይላሉ።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከግብጽ ውጪም ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። በርካቶች ድርጊቱን ''አሳፋሪ የሌላ ሕዝብን ባህል፣ ሃይማኖት እና እሴት መናቅ ነው'' ሲሉ ገልጸውታል።
ቪዲዮውን የቀረጸው ፎቶግራፈር ለረዥም ዓመታት ፒራሚዱን መሰል ግዙፍ መዋቅር የመውጣት ፍላጎት እንደነበረው በመጥቀስ፤ ''በድርጊታችን በርካቶች ቢበሳጩም አድናቆታቸውን የገለጹልን በርካታ ግብጻውያን መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም'' ብሏል።
ፎቶግራፈሩ ጥንዶቹ በፒራሚዱ አናት ላይ ወሲብ ፈጽመዋል የተባለው ውንጀላ ግን ከእውነት የራቀ እንደሆነ ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ጎብኚዎች የግብጽ ፒራሚዶች አናት ላይ ለመውጣ በሚያደርጉት ሙከራ ህይታቸውን ያጡ ነበር። እአአ 1980 ላይ ግን የግብጽ መንግሥት ፒራሚዶች ላይ መውጣትን ከለከለ። ክልከላው ግን አንዳንድ ሕግ ጣሽ ጎብኚዎችን ከፒራሚዱ አናት ላይ ከመውጣት አልገደበም።
ከሁለት ዓመታት በፊት በአስራዎቹ የሚገኝ ጀርመናዊ ታዳጊ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስል በካሜራው ለማስቀረት ከፒራሚድ አናት ላይ ወጥቶ ነበር።
ጥፋቱ ታዳጊው ላይ እስከ ሶስት ዓመት ሊያስፈርድበት ይችል የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ በጀርመን መንግሥት ጣልቃ ገብነት ታዳጊው ከመከሰስ ተርፏል።
ከአንድ ዓመት በፊትም የቱርክ ዜግነት ያለው ጎብኚ ፒራሚድ ላይ በመውጣቱ ለአጭር ጊዜ ለእስር ተዳርጎ ነበረ።

Wednesday, June 26, 2019

"የጋምቢያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ ደፍረውኛል"



የ23 ዓመቷ የቀድሞ የጋምቢያ የቁንጅና ንግሥት፣ ፋቱ ጃሎው በ2015 በቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ መደፈሯን ተናገረች።
ይህንን ቃሏን የሰጠቸው ሂውማን ራይትስ ዎች እና ትራያል ኢንተርናሽናል ባደረጉት ምርመራ ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ ፈፀሟቸው በተባለው ጾታዊ ትንኮሳና መደፎሮችን ባጋለጠው ዝርዝር ሪፖርት ላይ ነው።
ፋቱ ጃሎው ፕሬዝዳንቱን ስታገኛቸው የቁንጅና ውድድሩን በበላይነት አሸንፋ የነበረ ሲሆን እድሜዋም 18 ነበር።
ይህንን ውድድር ባሸነፈችበት ወር ፕሬዝዳንቱ እንደ አባት እየመከሩ የተለያዩ ስጦታዎችን እና ገንዘብ እየሰጧት አክለውም ቤተሰቦቿ በሚኖሩበት አካባቢ ውሃ እንዲገባ በማስተባበር ቅርበታቸውን አጠናከሩ።
ፋቱ ጃሎውከዛም ትላለች ፋቱ ለፕሬዝዳንቱ ድጋፍ ለማሰባሰብ በተዘጋጀ በአንድ የእራት ግብዣ ላይ የጋብቻ ጥያቄ አቀረቡላት። ፋቱ ግን ጥያቄውን በመቃወም በእራት ግብዣው ላይ ለመስራት የወሰደቻቸውን ኃላፊነቶችን ሰረዘች።
በ2015 ሰኔ ወር ላይ ግን በፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት በተካሄደ ሀይማኖታዊ ፕሮግራም ላይ እንድትገኝ ተጠየቀች። ቤተመንግሥቱ እንደደረሰች ግን የተወሰደችው ወደ ፕሬዝዳንቱ የግል መኖሪያ ነው።
"ምን እንደሚፈጠር ግልፅ ነበር" ትላለች ፋቱ፤ ፕሬዝዳንቱ የጠየቁትን እምቢ በማለቷ መናደዳቸውን በማስታወስ።
ከዛም በጥፊ እንደመቷትና መርፌ እንደወጓት ታስታውሳለች። ቀጥሎም ደፈሯት።
ቢቢሲ ያያ ጃሜን በስደት በሚኖሩበት ኢኳቶሪያል ጊኒ ስለቀረበባቸው ክስ ለማነጋገር ሞክሮ ነበር።
የፓርቲያቸው ቃል አቀባይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ የቀረበውን ክስ በአጠቃላይ ክደዋል።
ቃል አቀባዩ ኡስማን ራምቦ ጃታ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ "እንደፓርቲ እና እንደ ጋምቢያ ህዝብ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ በሚቀርቡ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች ተሰላችተናል" ብለዋል።
"የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለእንዲህ አይነቱ ውሸትና የጥላቻ ዘመቻ መልስ ለመስጠት ጊዜ የላቸውም። የተከበሩ፣ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ አማኝ ለጋምቢያ ሴቶች ክብር ያላቸው ናቸው" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ናቸው።
ጃሎ ለቢቢሲ ፕሬዝዳንቱን ፍርድ አደባባይ ለማቆም እንደምትፈልግ ተናግራለች።
"ይህንን ታሪኬን ለመደበቅ፣ ለማጥፋት ሞክሬያለሁ፤ የታሪኬ አካል እንዳልሆነ ለማድረግ ጥሬያለሁ"
"እውነታው ግን አልቻልኩም፤ አሁን ለመናገር የወሰንኩት ታሪኬን በመናገር ያያ ጃሜ የሰሩትን እንዲሰሙ ስለፈለኩ ነው"
አክላም በጋምቢያ ሀቅና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ፊት ቀርባ ለመመስከርም ፈቃደኛ መሆኗን ተናግራለች።
ይህ የሀቅና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን የተቋቋመው በ2016 በፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ሲሆን በያያ ጃሜ የ22 ዓመት አስተዳደር ወቅት የተጸፀሙ ጥፋቶችን ይመረምራል።

ጋዜጠኛና የመብት ታጋይ እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት እየታሰሩ እንደሆነ ተናገረ BBC


"ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም" እስክንድር ነጋ

እስክንድር ነጋ
ቅዳሜ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት እየታሰሩ እንደሆነ ጋዜጠኛና የመብት ታጋይ እስክንድር ነጋ ገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ ከእስክንድር ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፦ የባልደራስ አባላት ታስረዋል የሚባል መረጃ አለ ምን ያህል እውነት ነው?
እስክንድር፦የባላደራው ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆነው ስንታየሁ ቸኮል ጀምሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ የአመራር አባል የሆኑት ኃይሉ ማሞና መርከቡ ኃይሉ የተለያዩ የአመራር አባላት ታስረዋል፤ እስሩም ቀጥሏል። እኔም ጉዳያቸውን ለማጣራት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄጄ ሞክሬያለሁ ነገር ግን በወቅታዊ ጉዳዮች ታስረዋል ከሚል ውጭ ምንም አይነት መረጃ የሚሰጠኝ ሰው አላገኘሁም። የታሰሩት እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ነው።
ቢቢሲ፦ እስክንድር ታስሯል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነበር። የባህርዳር ቆይታህን ልትነግረን ትችላለህ  ?

እስክንድር፦ እሁድ እለት ህዝባዊ ስብሰባ ስለነበረን ወደ ባህርዳር የሄድኩት ቅዳሜ 11 ሰዓት ነበር፤ የአምሳ ደቂቃ በረራ ነው፤ አየር ላይ በነበርኩበት ሰዓት ነው ሰዓት ነው ይሄ የተከሰተው። አውሮፕላኑ ሲያርፍ ይሄ ነገር ተከስቶ ነው የጠበቀኝ፤ ወደ ውጭ መውጣትም ስላልቻልኩኝ "ለደህንነትህ" ብለው እዛው አየር ማረፊያ ነው ያደርኩት።እዚያው ያደርነውም የአዲስ አበባ ባልደራስ ምክር ቤት አባላት ብቻ ነን። እሁድ ግን ማን እንደከለከለ ባናውቅም ተመልሰን ወደ አዲስ አበባ እንዳንሄድ ተከልክለናል። እንዲያውም መመለስ ትችላለችሁ ተብለን ተጨማሪ ገንዘብ ከፍለን ትኬት ገዝተናል። ነገር ግን ሁሉን ነገር ጨርስን አውሮፕላን ልንገባ ስንል አትሄዱም ተብለን ተጠርተን ተመልሰናል።
ከዚያ በኋላ ወደ ባህርዳር ገብተን 30 ደቂቃም ሳንቆይ ተለያይተን እኔና ስንታየሁ በመኪና ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል። እኛ ከተመለስን በኋላ ግን ሌሎች ሶስት አባላት በአየር እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸው በአየር ተመልሰዋል።
22 ሰዓት መንገድ ላይ ቆይተን ነው አዲስ አበባ የገባነው።

ቢቢሲ፦ ባህርዳር አየር ማረፊያ በነበራችሁበት ወቅት አዲስ አበባና ባህር ዳር ስለሆነው ነገር መረጃ ታገኙ ነበር?
እስክንድር፦ አዎ ቴሌቪዥን ስለነበር ተከታትለናል።
ቢቢሲ፦ ጀኔራል አሳምነው ጋር አውርታችኋል ወይ ስለስብሰባው ጉዳይ?
እስክንድር፦ አላወራንም። እኔ እኮ ተጋባዥ ነኝ። አዘጋጅ ስላልሆንኩ ስለስብሰባው የማስፈቅደው ነገር የለንም። እኔንም ከእሳቸው ጋር ሊያገናኘን የሚችል ቅንጣት ነገር የለም። እዚያ ላይ የተፈጠረው ነገር ፓርቲው ላይ የተፈጠረ ነው። ይህን አሳቦ እኛን ማሳደድ ግን ተገቢም አይደለም፤ ፍትሃዊም አይደለም።
ቢቢሲ፦ መንግስት አጋጣሚውን በመጠቀም እኛን እያጠቃ ነው ብለህ ታምናለህ?
እስክንድር፦በግልጽ እየታየ ነው እኮ። እኛ ከዚህ ጉዳይ ጋር የምንገናኝበት ቅንጣት ታክል ግንኙነት የለም። አጠቃላይ ፓርቲው ጋር የተፈጠረ ነው። እኛ እንኳን አሁን እና ድሮም በጨለማው ዘመን በሰላማዊ መንገድ ነው ስንታገል የነበረው። አሁንም ተልዕኮ የሰጠን ህዝብ በዚሁ እንድንቀጥል ነው የሚፈቅድልን። ለተፈጠረው ችግር የፓርቲው ሰዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው። እነሱን ማዳመጥ ነው። የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ጉዳዩን በዝርዘር ለህዝብ አቅርበዋል፤ እነሱን መከታተል ብቻ ተጨማሪ መረጃ ሳያስፈልግ ጉዳዩን መረዳት ይቻላል።
ቢቢሲ፦እስክንድር በግልህ አደጋ ይደርስብኛል ብለህ ትሰጋለህ? በመንግስት በኩልስ ጥበቃ ይደረግልሃል ወይ?
እስክንድር፦በመንግስት በኩል ጥበቃ አይደረግልኝም፤ አልፈልግምም። ጥበቃ የሚያስፈልገኝ ሰውም አይደለሁም። እኔ ሙሉ ለሙሉ ጠባቂዬ እግዚአብሔር ነው ብየ ስለማምን። በተለያየ አጋጣሚ ስጋቶች አሉብኝ በተለይ መንገድ በምንወጣበት ወቅት በጣም ከባድ አደጋዎች ናቸው የሚገጥሙን። ነገር ግን በጸጋ ነው የምቀበለው። በማህበራዊ ሚዲያዎች በቪዲዮ ጭምር የሚሆነውን ታያለህ በሌሎች አጋጣሚዎችም ከፍተኛ የሆነ ስጋት አለኝ። በርግጥ ልጅና ሚስት አለኝ፤ ለቤተሰቤ ብየ ለህይዎቴ ዋጋ እሰጣለሁ፤ ከዚያ ባለፈ ግን ጥበቃ አያስፈልገኝም።
ቢቢሲ፦ምናልባት እንቅስቃሴህን መገደብ እንዳለብህ ይሰማሃል?
እስክንድር፦ ምን አጠፋንና ነው ረገብ ማለት የሚያስፈልገን? ወደ ሃይል እርምጃ አልገባን? ወይም ሰላም የሚያደፈርስ ነገር አልሰራን? አቋም መወሰድ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ግን አቋም እንወስዳለን። ከእውነት ጋር እንሞግታለን። ከዚህ በፊትም እኮ ከእውነት ጋር ወግነን ነው ዋጋ የከፈልነው። አሁንም ከእውነት ጋር መወገን ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነ ዋጋ እንከፍላለን። ቀይ መስመር አለ፤ እሱን አናልፍም። እንኳን የሃይል ርምጃ ልንወስድ ጠጠር እንኳ አንወረውርም።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አስክሬን ላሊበላ ገባ



የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን አስክሬን ላሊበላ አየር ማረፊያ እንደደረሰ በሥፍራው የሚገኙት የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለቢቢሲ ገለፁ።

ትናንት የብ/ጄነራል አሳምነው መገደል ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቻቸው አስክሬናቸው በክብር እንዲሰጣቸው ለወረዳው ጥያቄ በማቅረባቸው መንግሥት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ አስክሬናቸውን እንደሸኘ አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።
ዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ የብ/ጀኔራሉ አስክሬን ከባህር ዳር ወደ ትውልድ ቀያቸው እንደሚላክ በስልክ እንደተነገራቸው የገለፁት ምክትል ከንቲባው አስክሬናቸውን በክብር ለመቀበል በአየር ማረፊያ እንደተገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጄነራሉ ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የአካባቢው የመንግሥት አመራር አካላት፣ የፀጥታ ኃይሎችና የቤተክርስቲያን ቀሳውስት በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተዋል።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር ገና ስላልተነጋገሩ የብ/ጄነራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት የትና መቼ እንደሚፈፀም በእርግጠኝነት መግለፅ እንደማይችሉ የገለፁልን ምክትል ከንቲባው፤ ሕብረተሰቡ ኃዘኑን የሚገልፅበት በከተማ አደባባይ ትልቅ ድንኳን የተዘጋጀ መሆኑንና አስክሬናቸውም በዚሁ ድንኳን ውስጥ እንደሚያርፍ አስረድተዋል።
በዚያው ሥፍራ ሌሊቱን የፀሎተ ፍትሃት ሥነ ሥርዓት እየተደረገ እንደሚያድር መረጃ እንዳላቸው ገልፀውልናል።
ምክትል ከንቲባው ብ/ጄነራል አሳምነው ለአገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በደማቅ ሁኔታ ለመፈፀም ኮሚቴ መዋቀሩን አክለዋል።
በዚህም መሠረት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በዲስፕሊንና በፕሮቶኮል ለመምራት የክብር ተመላሽ ጄነራሎች በአካባቢው ላይ በመኖራቸው በእነርሱ ይመራል ብለዋል።
በሌላ በኩልም የፀጥታ ሂደቱን የሚመራ ቡድን፣ የወጣቱ ሰላምና ደህንነት የሚከታተል ሌላ በወጣቶች የሚመራ ቡድን እንዲሁም የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቱን የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሯል።
ጄኔራል አሳምነው ፅጌ
አቶ ማንደፍሮ እንደገለፁልን ትናንት ብ/ጄነራሉ መገደላቸውን ከተሰማ አንስቶ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተዘበራራቀ ስሜት እንደሚታይ እንዲሁም በክልሉ አመራሮች ሞት ምክንያት ድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።
የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት አመራርና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጎን በመሆን ቤተሰባቸውን በማፅናናትና ህዝቡንም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዳሜ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ባህር ዳር ውስጥ ተሞክሯል የተባለውን "መፈንቅለ መንግሥት" መርተዋል ተብለው ሰማቸው የተጠቀሰው የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋድየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ መገደላቸው ይታወሳል።

የራሱን ዘር ተጠቅሞ ታካሚዎቹን ያስረገዘው ዶክተር የሕክምና ፈቃድ ተከለከለ

የራሱን ዘር ተጠቅሞ ታካሚዎቹን ያስረገዘው ዶክተር


ካናዳዊው የርቢ [ፈርቲሊቲ] ዶክተር የራሱን ወንዴ ዘር ተጠቅሟል በመበሏ የሕክምና መስጫ ፈቃዱን ተነጥቋል።
ካናዳውያውያን ፈቃድ ሰጭዎች 'እጅግ ኃላፊነት የጎደለው' ሲሉ የራሱን የወንዴ ዘር ለሕክምና የተጠቀመውን ዶክተር ወቅሰውታል።
ዶክተሩ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሕክምና ሲሰጥ የነበረ [በግሪጎሪ አቆጣጠር] የ80 ዓመት፤ ዕድሜ ጠገብ እና ታዋቂ ሰው ነበር ተብሏል።

የፈቃድ ሰጭ እና ነሺው አካል ሠራተኛ የሆኑት ዶክተር ስቲቨን ቦድሊ የቅጣታችን ልኩ ፈቃድ መንጠቅና ቀላል የገንዘብ ቅጣት ብቻ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል ሲሉ ቁጭታቸውን ገልፀዋል።
በግሪጎሪ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ሰጥተቅ የማየውቁት የርቢ ዶክተሩ ባርዊን ቅጣታቸውን ለመቀበል ጠበቃቸውን ይላኩ እንጅ ብቅ አላሉም።
በክሱ መሠረት ዶክተር ባርዊን ቢያንስ 13 ታካሚዎቻቸውን የራሳቸውን ወይንም ባለቤትነቱ ያልታወቀ የወንዴ ዘር ተጠቅመው አስረግዘዋል ተብሏል።
ከ50-100 ያሉ ሕፃናት ዶክተሩ ለእናቶቻቸው በሰጡት የወንዴ ዘር አማካይነት ተወልደዋል ቢያንስ 11 ሕፃናት ደግሞ የዶክተሩ ልጆቸ መሆናቸው ታውቋል።
ዶክተሩ እስካሁን ድረስ ክሳቸው እየታየ ያለው በሕክምና ፈቃድ ሰጭ እና ነሽ አካል እንጂ በፍርድ ቤት አይደለም።

Thursday, June 20, 2019

ከሰባት ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አንዱ የወሲብ ፊልምን ለማየት ሲል ድረ-ገጾችን ያስሳል


ኢንተርኔትን የሚሾፍረው የወሲብ ፊልም ይሆን?
ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ከሰባት ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አንዱ የወሲብ ፊልምን ለማየት ሲል ድረ-ገጾችን ያስሳል። በእርግጥ ጉዳዩን ማንኳሰስ ባይሆንም ስድስቱ ተጠቃሚዎች ሌላ መረጃ ፈላጊዎች ናቸው።
በጣም ዝነኛው የወሲብ በይነ መረብ - Pornhub - ከእነ ኔትፍሊክስና ሊንክደን ጋር እኩል ተመልካች አለው። የወሲብ ፊልም ዝነኛነቱ በዓለም ላይ 28ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ውድና ተዓማኒነት የሚጎድላቸው ናቸው። ቴክኖሎጂውን በቀላሉ መረዳት የሚችሉ ደንበኞችን ለመያዝ ለገበያው የሚመጥን ስራ ያቀርባሉ። አንድ ጊዜ ዋጋው ከወረደና ተዓማኒነት ካገኘ ግን ተጠቃሚና ትልቅ ገበያ ያገኛል።
የወሲብ መረጃዎች ለኢንተርኔት እድገት አዎንታዊ ሚና መጫዎታቸውን የሚገልጽ ጽንስ ሃሳብ አለ። ለሌሎች ቴክኖሎጂዎችም እንዲሁ።

ዘመናዊ ምጣኔ ሃብትን የሚያመጡ ሌሎች ጉዳዮች
ጥበብ ሲወለድ ጀምሮ ወሲብ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። የቀደምት ስልጣኔ የዋሻ ላይ ስዕሎች እንደሚያሳዩት መቀመጫ (ቂጥ)፣ ጡት፣ የሴት ብልትን አካባቢ የሚያሳዩና ትልቅ የወንድ ብልት ዋነኛ የጥበብ መገለጫዎች ናቸው።
ከ11 ሺህ አመታት በፊት የአይሁድ እረኞች በዋሻ ላይ ወሲብ ሲፈጽሙ የሚያሳይ ስዕል ቀርጸዋል። ከ4 ሺህ ዓመት በፊት በሜሶፖታሚያ ስልጣኔ ሁለት ጥንዶች በሸክላ ግድግዳ ላይ ወሲብ ሲፈጽሙና ሴትዮዋ ቢራ ስትጎነጭ ያሳያል። በሰሜን ፔሩም ከብዙ አመታት በፊት በሴራሚክስ ላይ የተሰራ ወሲብ የሚፈጽሙ ጥንዶችን አስቀምጧል።
ነገር ግን የጥበብ ውጤቶች እነዚህን ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ይዘው ቢወጡም ዋነኛ ጥበቡን ለመስራት ያነሳሳቸው ቀዳሚ ምክንያት ወሲብ ነው ማለት ግን አይቻልም።
እንደዚህ ለማሰብ የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም። የጉተንበርግን የህትመት ማሽን ማሰብ ይቻላል። በዋናነት ወሲብ ቀስቃሽ መጽሃፍት የሚታተሙበት ቢሆንም መነሻው ግን የሃይማኖት መጽሃፍት እንዲታተሙበት ነበር።
በሚገርም ሁኔታ ደግሞ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፋሽን ፎቶ የነበረው ከንፈርን ማዕከል ያደረገ ፎቶ ነበር።
በፈረንሳይ ፓሪስ የፎቶ ስቱዲዮን መገንባት መቻል ትልቅ የንግድ ስኬት ተደርጎ ይወሰድ ነበር። መንግስትም ክልከላ ስለሚያደርግበት ጭምር። በወቀቱ ደንበኞች ለዚህ አይነቱ ፎቶ የተጠየቁትን ይከፍሉ ነበር። በጊዜው ዋጋ ወሲብ አነሳሽ ፎቶን ለመግዛት የሚያወጡት ዋጋ በወሲብ ስራ የተሰማራችን ሴት ለማግኘት ከሚያስፈልገው ገንዘብ በላይ ነበር።

ተንቀሳቃሽ ምስል ሲጀመር ደግሞ ውድ በመሆኑ ፊልም የሚያሳዩ ሰዎች ገንዘባቸውን ለማካካስ ሲሉ ብዙ ተመልካች ይፈልጉ ስለነበር በዚህ ምክንያት ወሲብ ነክ ፊልሞችን በአደባባይ አያሳዩም ነበር። እየቆየ ሲመጣ ግን አንዳንዶች በቤታቸው ሲመለከቱት በአደባባይ ከህዝብ ጋር የሚያዩ ወጣቶችም ነበሩ።
በ1960ዎቹ ደግሞ ሳንቲም ተጨምሮበት ማንም ሊያይ በማይችልበት ሁኔታ ለብቻ የወሲብ ፊልሞችን ማየት የሚያስችሉ አነስተኛ ቤቶች ተፈጠሩ።
አንዷ ቤትም በሳምንት ብዙ ሸህ ዶላር ትሰበስብ ነበር። በግል ሳይሳቀቁ ማየት የሚቻልበት እድል ሙሉ በሙሉ የተፈጠረው ግን የቪዲዮ መቅረጫ መሳሪያ (VCR) ሲመጣ ነው። ሰው በጣም በግሉ ማየትን ይሻ ስለነበርም መመረት እንደተጀመረም ጠጥሩ ገበያ አግኝቷል።
ቤት ተቀምጠው ፊልሙን ማየት የሚሹ ወጣቶች ደግሞ ይህን መሳሪያ በመግዛት ቀዳሚ ናቸው። በ1970ዎቹ አብዛኛዎቹ የቪዲዮ ቴፖች የሚሸጡት የወሲብ ፊልሞችን ነበር። በጥቂት አመታት ውስጥ ደግሞ የቤተሰብ ፊልም የሚመለከቱ ሰዎች በመበራከታቸው በአንጻሩ የወሲብ ፊልሙ መቀዛቀዝ ታይቶበታል።
በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት ላይም እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ታሪክ ነው። በ1990ዎቹ በተጠቃሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት ኢንተርኔት ላይ ከሚጋሩ ስድስት መረጃዎች አንዱ ከወሲብ ጋር የተያያዘ ነው።
በቅርቡ በኢንተርኔት ላይ የተደረጉ ወሬዎች (chats) ውጤት የሚያሳየውም ተመሳሳይ ነው። በአሁኑ ወቅትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ አጥኝዎች የሚሰጡት ሃሳብ ስህተት ሊሆን የሚችልበት እድል የለውም። የወሲብ መረጃዎች ፍላጎት በመኖሩ ፈጣንና አቅም ያለው ኢንተርኔት እንዲኖርም ምክንያት ሆኗል።

በሌሎች ዘርፎችም ግኝቶችን አስገኝቷል። በድረ-ገፆች የሚቀርቡ የወሲብ ፊልሞችን ለማቅረብ የበይነ መረብ ቴክኖሎጂን ወደፊት ለማራመድ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።
ለምሳሌ የቪድዮ ፋይሎችን ለእይታ እንዲቀርቡ ማሳነስ፣ ለተጠቃሚው ቀለል ያሉ በበይነ መረብ የመክፈያ ዘዴዎችን በመፈየድ እና የማርኬቲንግ ፕሮግራሞችና ሌሎችም ንግዶች ማስተዋወቂያ በገፃቸው እንዲያሳዩ በማድረግ ረገድ ማለት ነው።
እነዚህ ሁሉ ሰፊ ተደራሽነትን ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። ኢንተርኔት በመስፋፋቱም በሌሌች ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩና ወሲብ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲቀንስ ያደርጋል።
በአሁኑ ወቅት የወሲብ ፊልምን ሞያዬ ብለው ለሚሰሩት ሰዎች ፈተና ሆኗል። ጋዜጦችንና ሙዚቃዎችን የሚያቀርቡ ሰዎች ገበያው በኢንተርኔት ተወስዶባቸው ገዥ እንዳጡት ሁሉ የወሲብ ሰራተኞችም ቪዲዮውን እነ ፖርን ሃብ (Pornhub) በበየነ መረብ በበቂ ሁኔታ ቀድመው በማቅረባቸው እነርሱ ገዥ የላቸውም።
ጆን ሮንሰን The Butterfly Effect በሚለው ተከታታይ ገለጻው እነዚህን የተዘረፉ የወሲብ ፊልሞች መመለስና ገበያውን ነጻ ለማድረግ ሙከራ ቢኖርም ከባድ መሆኑን ገልጸዋል። በጣም እያደገ የመጣው ዘርፍ 'ካስተም' ማለትም እያንዳንዱ በፍላጎቱ የሚስተናገድበት ዘርፍ ነው።
ለምሳሌ ብዙዎች እንደሚያደርጉትና አንድ ግለሰብ ኬሲ ካልቨርት የተሰኘችውን ወሲብ ፊልም ተዋናይ የቴምብር ስብስቦቹን በፊልም እንድታወድም እንደከፈላት ማለት ነው።

በርግጥ ይዘቱን ለሚፈጥሩት ሰዎች መጥፎ ቢሆንም እንደ አጠቃላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በማሳደግ ረገድ ግን አዎንታዊ ተጽዕኖ አለው። ምክንያቱም ከብዙ ተጠቃሚዎች ገንዘብ በመሰብሰብና ማስታወቂያ በመስራት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለመሰብሰብ አስችሏል።
በወሲብ ፊልም በአሁኑ ወቅት የፖርን ሃብንና ሌሎች ሰባት የወሲብ በይነ መረቦችን በባለቤትነት የሚመራው ማይንድጊክ ከአስሩ ቀዳሚዎች አንዱ ነው።
በኪው ጎዳና (Avenue Q) የሚታየው ኀሳይ መሲሁ ድርጅት ቀኑን ሙሉ ምንም አይሰራም። የወሲብ ፊልም ብቻ። በመጨረሻ ግን ሌሎች ገጸ ባህሪያት እርሱ ሚሊኒየር ሲሆን ይገረማቸዋል።
በመሆኑም ኀሳይ መሲሁ እውነት ባይሆንም ለእውነት የቀረበ ነው። በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ወሲብ ላይ ገንዘብ አለው።
ይህን ለማድረግ የተሻለው ነገር ግን ይህን መተካት የሚችል ቴክኖሎጂ መስራት ነው። ምናልባትም ሮቦቶችን ለወሲብ ፊልም መጠቀም ሊሆን ይችላል። በየጊዜው በሚፈጥነው የቴክኖሎጂ ግኝት ግን የወሲብ ጉዳይ መቋጫ ሊያገኝ አልቻለም

Friday, June 14, 2019

የጠ/ሚ አብይ አህመድ መንግስት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የሚያካሂደውን አፈና በጽኑ እናወግዛለን



Addis Ababa police interapted press conference.
የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ከዚህ ቀደም በጋዜጠኛ/የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የባለአደራ ምክርቤት በራስ ሆቴል ሊያካሂድ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ በህገወጥ መንገድ እንዲታገድ አድርጓል። በተመሳሳይ እስክንድር ነጋ የሚገኝበት ሰናይ መልቲ ሚዲያን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እንዳይካሄድ ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ ክልከላ አድርጓል።
ይህ በእስክንድር ነጋ ላይ ያነጣጠረ መንግስታዊ የማፈን ተግባር ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት የሌለውና በስልጣን ላይ ባለው መንግስት እየተካሄደ ያለ የመብት ረገጣና ህገወጥ ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።
ይህ በእስክንድር ነጋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚካሄደው አፈና በዚህ አይነት የሚቀጥል ከሆነ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ነገ ተነገወዲያ አፈናው በሌሎችም ላይ የሚፈጸምና የአምባገነንት ሥርዓት እግር አውጥቶ መራመድ መጀመሩን ማሳያ ነው ብለን እናምናለን።
በመሆኑም ይህን አምባገነናዊ የአፈና ተግባር ማንኛውም ነጻነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲያወግዘው ብሎም እንዲታገለው ጥሪ እናስተላልፋለን።

Thursday, June 13, 2019

በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይም ሆነ ሌሎች ላይ እየቀረበ ያለው ክስ ‹‹በዓለም ላይ አሳፋሪ የሚባል›› ነው፡፡

‹‹ሕዝቡ የመገንጠል ስሜት ውስጥ ገብቷል›› ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል
በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይም ሆነ ሌሎች ላይ እየቀረበ ያለው ክስ ‹‹በዓለም ላይ አሳፋሪ የሚባል›› ነው፡፡
አቶ ጌታቸው አሰፋን በሚመለከት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ድረስ ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳይ አለ፡፡
በመንግስት እውቅና ሆን ተብሎ ህዝቡን ለማስራብና ለማስጠማት መንገድ እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ እየተፈጸመ ባለ የዘር ጥቃት ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጋር አብሮ ከመቀጠል ይልቅ መገንጠል ስሜት ውስጥ እንደገባ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ‘ሕዝቡ በሚደርስበት ዘር ተኮር ጥቃት ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግሥታት ጋር አብሮ በአንድነት መቆየት ላይ ተስፋ ቆርጧል’ ፤ ‘ሆን ተብሎ በሚፈጸም ጥቃት ሕዝቡ ከዚህ ሥርዓት ጋር አብሮ መቀጠል እንደማይቻል እየገለጸ ነው’ ፤ ‘ከራስህ መንግሥት የማትጠብቀው የዘር ጥቃት ዘመቻ ተከፍቷል’ ብለዋል፡፡
በዘር እና በማንነት ያነጣጠረ ጥቃት በትግራይ ላይ እየተፈጸመ ለመሆኑ ማሳያ ብለው በመካከለኛና በታችኛው የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተመደቡ የትግራይ ተወላጆች በሙሉ በአቅም ማነስ ሰበብ ከስራቸው እንዲሰናበቱ እየተደረጉ ነው ሲሉ ጠቅሰወል፡፡
‹‹በአገር ደረጃ የዕብደት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ‹‹ሰላም እንዲያስከብር በበላይነት ኃላፊነቱን የወሰደው አካል ሲያበላሽ እኛ እያስተካከልንለት ነው፡፡
የእኛ ሥራ ማቀጣጠል አይደለም፡፡ ከክልላችን በላይ ኃላፊነት ደጋግመን በመውሰድ ሰላም ለማስፈን ችለናል፡፡ ግን ለጥቃትና ለማበጣበጥ ኃይል እየተላከብን ነበር፡፡ ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ወታደር እየተላከብን ለማበጣበጥ ተሞክሯል፤›› በማለት በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ከባድ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አጎራባች በሆነው የአማራ ክልል የመንግሥት ኃላፊዎችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው በሚመስል አድራጎት፣ የፌዴራል መንግሥት ንብረት የሆነው አውራ መንገድ እየተዘጋ ጭምር ሕዝብ እንዲራብና እንዲጠማ ለማድረግ ተሞክሯል ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹መንገድ እየተዘጋ ሕዝብ ሆን ተብሎ እንዲራብና እንዲጠማ ለማድረግ የሚፈጸም ወንጀልን የአማራ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ዝም ማለታቸው ሆን ተብሎ ጫና ለመፍጠር መንግሥት ፈቅዷል እንላለን፡፡ ሕዝብ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ዝም ያለው መንግሥት ተጠያቂ ነው›› ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የአቶ ጌታቸው አሰፋን ጉዳይ በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ መጠየቅ ያለበት፣ ያጠፋ ይጠየቅ ካሉ በኋላ፣ ‹‹ደማቅ ፊርማ ያለው ቀላል ፊርማ ያለው የሚባል ነገር የለም፡፡ ብሔሩ ትግራይ ስለሆነ ብቻ ከእየ ኮሚቴው እየተመረጠ የሚታሰር ብዙ ነው፡፡ ሊገመት የማይችል ወደ ታች መውረድ እየታየ ነው፡፡
ይኼ የእኛ መንግሥት ነው እንዴ የሚያስብል ዝቅጠት እየታየ ነው፤›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ እንደ መንግሥትና እንደ ሕግ አግባብ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆኖ በግሉ ያጠፋ ካለ ‹‹ይንጠልጠል ብያለሁ›› በማለት በሕግ አግባብ የሚወሰድ ዕርምጃን እንደሚደግፉ፣ ሆኖም በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይም ሆነ ሌሎች ላይ እየቀረበ ያለው ክስ ግን ‹‹በዓለም ላይ አሳፋሪ የሚባል›› ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሕጋዊና ትክክለኛ ዕርምጃ ቢሆን ኖሮ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጭምር የሚጠየቁበት አግባብ እንደሚኖር፣ ሆኖም በግላቸው አቶ ኃይለ ማርያምም ሆኑ አቶ ጌታቸው፣ እንዲሁም ሌሎች የታሰሩ ሰዎች ለመንግሥትና ለሕዝብ በማገልገላቸው መታሰር እንደማይገባቸው፣ በተጨማሪም ከደኅንነት ሥራ ጋር ከተያያዘ የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር

ሕወሓትና ሻዕቢያን ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ ተጠየቀ።


ሕወሓትና ሻዕቢያን ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ ተጠየቀ።
የኤርትራ ገዥ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ/ሻዕቢያ እና የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረውን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን/ሕወኋት ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥቱ ዕገዛ ተጠይቋል፡፡
‹‹ዳስ ዕርቂ አሕዋት ውድባት››/የዕርቅ ዳስ በሚል በሴሌብሪቲ ኢቨንትስ ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በተዘጋጀው የዕርቅ መድረክ፣ ሁለቱን ፓርቲዎች ለማስታረቅ፣ ድርጅቱ ማዕከላዊ መንግሥት ዕገዛ እንዲያደርግለትና ለእንቅስቃሴውም ዕውቅና እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ሰላም በሕወሓትና በሻዕቢያ መካከል አለመፈጠሩን የሚናገሩት የሴሊብሪቲ ኢቨንትስ መሥራች ወንድማማቾቹ አቶ አብርሃምና አቶ ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ፣ በሁለቱ ድርጅቶች ውስጥ የሚታየው ጥላቻና እልህ የአገርን ደኅንነት ሥጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች እስከ መፈጸም መድረሱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የተደረጉ ጥናቶችም እንደሚያሳዩት፣ ሕወሓትን ያገለለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረውን መጠራጠርና ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንዲከር ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአየር ትራንስፖርት መግባትና መውጣት ቢቻልም ድንበር አካባቢ ምንም የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው ድባብም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት እንደሆነ የሚናገሩት ወንድማማቾቹ፣ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለው እልህ ዕርቁ መሬት እንዳይወርድ እንቅፋት መሆኑን ገልፀዋል ሲል የዘገበው ሪፖርተር ነው።
ዐማራ ሚዲያ ማዕከል/ዐሚማ

የዲሲ ግብረ ሃይል በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዝምታ እንደማያልፋቸው አስታወቀ

የዲሲ ግብረ ሃይል በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዝምታ እንደማያልፋቸው አስታወቀ
በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከዚህ በኋላ በዝምታ እንደማያልፍ የዲሲ ግብረ ሃይል አስታወቀ።
ግብረ ሃይሉ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ለረጅም ጊዜ የተቆመለትና ትግል ሲደረግ የቆየበት የሃሳብ ልዩነትን የማክበር ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲጣስ ቆይቷል።-አሁንም በመጣስ ላይ ነው።
በተደጋጋሚ እንደ ሃገር ለሚከሰቱ ችግሮች ስልጣን ላይ ያለው አካልም ምንም አይነት ምላሽ መስጠት አለመቻሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ እያሳጣው መምጣቱን ይገልጻል መግለጫው።
እንደ ቀድሞው አስተዳደር በሃገር ውስጥ ባሉ ተቋማት ብቻ ሳይሆን በውጭ ኤምባሲዎች ጭምር ያለው ምደባ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲሞላ መደረጉ አሳሳቢና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ሲል የዲሲ ግብረ ሃይል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
መንግስት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት የቅድመ መከላከል ስራ አለመስራቱ ብሎም ችግሮች ሲከሰቱ አስቸኳይ መፍትሄ አለመወሰዱ የለውጡን ሒደት ግራ የሚያጋባ አድርጎታል ብሏል።
በሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰው ወከባና እንግልት፣እንዲሁም የአደባባይ የግድያ ዛቻ ግብረ ሃይሉ በፍጹም የማይቀበለው ተግባር መሆኑን ገልጿል።
በአንጻሩ ደግሞ ከ17 ጊዜ በላይ የህዝብ ባንክ የዘረፉ፣ህዝብን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶችም ሆኑ ቡድኖች በዝምታ ሲታለፉ ሲታይ መንግስት ሆን ብሎ በራሱ ላይ ጫና እንዲፈጠር ያደረገው ነው የሚል እምነት እንዳለው የዲሲ ግብረ ሃይሉ በመግለጫው አስቀምጧል።
ይህ ህገ ወጥ ድርጊት በአፋጣኝ ካልታረመና ወንጀለኞቹ በአስቸኳይ ለፍርድ የማይቀርቡ ከሆነ ህዝብን በመንግስት ላይ ጥርጣሬ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ ግብረ ሃይሉም እንዲህ አይነቱን ዝምታ በቸልታ የማያልፈው ነው ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
ስለዚህ ሃገሪቱን እያስተዳደረ ያለው አካል እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አስቸኳይና የማያዳግም ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ግብረ ሃይሉ ለሚፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ አቅሙ እስከ ፈቀደ ድረስ ድምጹን የሚያሰማ መሆኑን ለኢትዮ 360 በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ጎንደር በመሄድ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት አለኝ የሚለው ኬንያዊ

ጎንደር በመሄድ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት አለኝ የሚለው ኬንያዊ ቢላ ይዞ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ጥሶ ለመግባት ሲሞከር በጠባቂዎቹ ተተኩሶበት ቆስሎ ተይዟል።
በፌስቡክ ገጹ ላይ በኬንያ መሪዎች ስር ከመተዳደር ጎንደር ውስጥ የቤት ውስጥ አገልጋይ ሆኖ መኖርን እንደሚመርጥ የሚናገረው ብሪያን ኪቤት ቤራ ሰኞ እለት ነበር ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለመግባት የሞከረው።
በጆሞ ኬንያታ የግብርናና የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የአምስተኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ብራያን ሊገባ ሲባል ግራ ትከሻው ላይ በጥይት ከቆሰለ በኋላ ሆስፒታል ገብቷል።
ፖሊስ እንዳለው የ25 ዓመቱ ብሪያን ኪቤት ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመግባት ሲሞክር የተመለከተው የጥበቃ መኮንን ግለሰቡ የአእምሮ ህመምተኛ ሊሆን ይችላል በሚል ለሞት በማያበቃው ቦታ ላይ በጥይት እንደመታው ፖሊስ ገልጿል።
ብሪያን በተደጋጋሚ በፌስቡክ ገጹ ላይ ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ “ሌባ” የሚላቸውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን እንደሚገድል ይጽፍ ነበር። ሰሞኑንም ይህንን ዛቻውን ለመፈጸም ሙከራ አድረጓል።
የ25 ዓመቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በተደጋጋሚ መንግሥትን የሚጻረሩ በተለይ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በማጥላላት የተሞሉ ሃተታዎችን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፍር ነበር። አቋሙን ለመደገፍም የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያጣቅስ እንደነበር የተለያዩ የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የተለያዩ የታሪክ መጽሃፍትን እንዳነበበ የሚገመተው ብሪያን ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ጎንደር ውስጥ መኖር እንደሚፈልግ ጠንከር ባለ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲጽፍ እንደነበረም ተነግሯል።
በአንድ ጽሁፉ ላይም “ይህ መልዕክት መሬቴንና ርስቴን ለዘረፉኝ ለፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ለህዝባቸው እንዲደርስ ይሁን። ኬንያ ውስጥ መሪ ከምሆን ኢትዮጵያ ውስጥ አገልጋይ ብሆን ይሻለኛል” ሲል አስፍሯል።
ወደጎንደር የመሄድ ፍላጎቱን በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ተማሪው “ከጠላቶቼ ጋርም ጦርነት አውጃለሁ። ምክንያቴ ደግሞ ወደ ጎንደር የምሄድበትን ገንዘብ ለማግኘት ነው” ብሏል።
“ሞኝ (ጨቋኝ) መሪ ከመሆን የብልሆች ባሪያ መሆንን እመርጣለሁ” የሚለው ብሪያን ጎንደር በመሄድ ብልህ ለሆኑት ህዝቦች አገልጋይ መሆን እንደሚፈልግ ጠቅሶ ለጉዞው የሚያስፈልገውን ገንዘብ አለማግኘቱ እንዳዘገየው አስፍሯል።
ስለጎንደርና ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በማህበራዊ ገጹ ላይ እንደሚጽፍ የተነገረው ይህ ወጣት በእያንዳንዱ ጽሁፉ ማብቂያ ላይ “ከኢትዮጵያዊው ልዑል፤ ቀድሞ ብሪያን ኪቤት ቤራ ተብሎ ይጠራ የነበረው” ሲል ያሰፍራል።
ብራያን ወደ ቤተመንግሥቱ ለመግባት ካደረገው ሙከራ ቀደም ብለው ጽሁፎቹ በመመልከት በርካቶች የተለያዩ ሃሳቦች የሰነዘሩ ሲሆን በርካቶች ድርጊቱን የተቃወሙ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የአእምሮ ጤንነቱን ተጠራጥረዋል።
BBC AMHARIC

የኢሳት ቦርድ በድርጅቱ ላይ የሰራውን ጥፋት የሚዘረዝር መረጃ



የኢሳት ቦርድ በድርጅቱ ላይ የሰራውን ጥፋት የሚዘረዝር መረጃ እጃን ገብቷል
በአስራ ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞች የተፈረመና ቦርዱ የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉንና ወደ ጥፋት አቅጣጨ መምራቱን በዝርዝር የሚያትትና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ደብዳቤ እጃን ገብቷል።
አበበ ገላው፣ ሲሳይ አጌና፣ መሳይ መኮንን፣ መታሰቢያ ቀጸላ፣ አፈውርቅ አግደው፣ እንግዱ ወልዴ፣ ወንድም አገኝ ጋሹን ጨምሮ በ12 ጋዜጠኞች የተፈረመው ደብዳቤ የተጻፈው ከሶስት ወራት በፊት ወደ አገር ቤት በተላከው የኢሳት የልዑካን ቡድን አባላት ሲሆን የኢሳት ማኔጅመንት፣ ሰራተኞችና ባለድርሻዎች ባልተሳተፉበትና ባላወቁበት ሁኔታ ያለምንም ጥናትና በቂ ዝግጅት ከተጣለበት ህዝባዊ አደራ ጋር በሚጻረር መልኩ ኢሳት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጿል።
“ይህም እርምጃ ያሳዘነንና የኛ በምንለው ድርጅት ውስጥ የባይተዋርነት ስሜት መፍጠሩን መካድ አይቻልም። ከዛም አልፎ ያለምንም ጥናትና ዝግጅት ፕሮግራሞችን የማጠፍ እና ስቱድዮችን የመዝጋት እቅድ ለብዙዎቻችን ሞራልን የሚነካ ክስተት ነበር፣” በማለት ሰራተኛ የመቀነስና ስቱዲዮችን የመዝጋት እቅድ በቦርዱ አስቀድሞ ታቅዶ እንደነበር ደብዳቤው አመላክቷል::
“ኢሳት ከሚጠበቅበት ደረጃ እጅግ ባነሰ መልኩ የግለሰብ መኖሪያ ቤት በደባልነት እንዲገባ ከመደረጉም በላይ ማንነታቸውን እስካሁን በማናውቃቸው ግለሰቦች የግል አክስዮን ማህበር ሆኖ ተመዝግቧል” ያለው ይሄው ደብዳቤ ምንም አይነት የሚዲያ ልምድ የሌላት ግለሰብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆና እንድትመደብ መደረጉ ኢሳት የገጠሙትን ችግሮች የበለጠ ማወሳሰቡን ጠቁሟል።
“በቦርድ ስም የተወሰደው አግባብነት የጎደለው እርምጃ ኢሳትን ወደሁዋላ ከመመለስ ባሻገር ወሳኝ የሆነው የአዲስ አበባ ስቱድዮ ተጠያቂነት የጎደለው ከደረጃ በታች የወረደ አሰራርም መንገድ መክፈቱን ተረድተናል። የኢሳት አላማ ወደ ጎን ተገፍቶ ለግል ጥቅምና እራስን የመሸጥ እሩጫ በጋራ የቆምንለትን አላማችንን ለማሳካት እንቅፋት ደቅኗል።” በማለት ጋዜጠኞቹ በቦርዱ ላይ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ ከኢሳት የለቀቁ ጋዜጠኞች ኢሳት ለገጠሙት ችግሮች ቦርዱን መወንጀላቸው ይታወሳል። የቦርዱ አባላት የሆኑት እራሴን አጥፍቻለሁ ያለው የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አዲሱ መንገሻ፣ ዘላለም ተሰማ፣ ሙሉ አለም አዳም፣ አዚዝ አህመድና ነአምን ዘለቀ መሆናቸው ታውቋል። አንዳንዶቹ የኢሳት ጋዜጠኞች የቦርዱን አፍራሽ እንቅስቃሴ ሲቃወሙ እንደ ነበርና ድርጅቱ ነጻ ህዝባዊ ሚድያ መሆን እንደሚገባው ሲሞግቱ እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል።

የደብዳቤውን ሙሉ ይዘት ለማንበብ ከታች ያለውን ተስንፈንጣሪ በመጫን ያንብቡ። እዚህ በመጫን ሙሉውን ያንብቡ

Monday, June 10, 2019

የጃፓን ሰራተኛ ሚኒስትር በስራ ቦታ ታኮ ጫማ አስፈላጊ ነው አሉ



የጃፓን ሚኒስትር ሴቶችን ታኮ ጫማ እንዲጫሙ የሚያስገድደው የሥራ ቦታ የአለባበስ ስርዓትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናገሩ።
የጃፓን ጤናና ሰራተኛ ሚኒስትር የሆኑት ታኩሚ ኔሞቶ፣ ይህንን አከራካሪ ልምድ " በሥራ ቦታ ላይ አስፈላጊና ተገቢ የሆነ ነገር እንዲሁም ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው" በማለት ደግፈው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይህንን አስተያየት የሰጡት የሕዝብ እንደራሴዎች ኮሚቴ ረቡዕ ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት ነው።
ወዲያውኑ አንድ ሕግ አውጪው አባል የሆኑ ግለሰብ እንዲህ አይነት ሕጎች "ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው" ሲሉ የሚኒስትሩን ሀሳብ አጣጥለውታል።
ሚኒስትሩ በጃፓን በአንዲት ተዋናይት ስለተጀመረውና በሥራ ቦታ ላይ አግላይ የሆነ የአለባበስ ስርዓትን የሚያዘው ደንብ እንዲሻር ስለሚጠይቀው የፊርማ ማሰባሰብ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር ይህንን ያሉት።የጃፓን ጤናና ሰራተኛ ሚኒስትር፣ ታኩሚ ኔሞቶ፣

ተዋናይቷ ታኮ ጫማ በሥራ ቦታ ላይ መጫማትን የሚያዘውን ደንብ እንዲነሳ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመረችው የቀብር አስፈፃሚዎች ደንቡን እንዲያከብሩ ከታዘዙ በኋላ ነው።
የፊርማ ማሰባሰቡ ዘመቻ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቶላታል።
የተሰበሰበው 18 ሺህ 800 ፊርማም ለጃፓን ሰራተኛ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ገቢ የተደረገ ሲሆን ደጋፊዎቹም የትዊተር ዘመቻ ጀምረዋል።
የዚህ ዘመቻ መሪዎች እንደሚናገሩት በጃፓን አንዲት ሴት ለሥራ ስታመለክት ታኮ ጫማ ማድረግ እንደ ግዴታ ይቀርብላታል።
"ይህ ዘመቻ ማህበራዊ ቅቡልነት ያለውን ይህ ተግባር አስወግዶ ሴት ልጅ እንደ ወንድ ማንኛውንም ጫማ አድርጋ በሥራ ገበታዋ ላይ እንድትገኝ ይፈቅዳል የሚል እምነት አለኝ" ብላለች የዘመቻው መሪ ኢሺካዋ።
ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ አንዲት ሴት በጊዜያዊነት በተቀጠረችበት የፋይናንስ መሥሪያ ቤት ታኮ ጫማ ካላደረግሽ ተብላ መገደዷ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን በማግኘቱ ብቻ ድርጅቶች ሴቶች የፈለጉትን መጫማት እንደሚችሉ ገልፀው ነበር።
እ.ኤ.አ በ2017 በአንዲት የካናዳ ግዛት ሴቶች ታኮ ጫማ እንዲጫሙ የሚያዝዘውን ደንብ ከሥራ ውጪ ማድረጋቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ተራው የጃፓን ይመስላል።

''ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም'' የቶቶ አስጎብኚ ድርጅት TOTO tours Homosexuals tour in Ethiopia

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሰንደቅ


ትናንት ከ120 በላይ የኦርቶዶክስ ማህበራት ስብስብ የሆነው ሰልስቱ ምእት የማህበራት ህብረት በቅርቡ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን በኢትዮጵያ ሊያደርጉ ያሰቡትን ጉብኝት በማስመልከት የተቃውሞ ድምጹን ለማሰማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል የጉብኝቱ አዘጋጅ በኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም እያሉ ነው።
የማህበራት ህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ ለቢቢሲ እንደገለፁት ''ቶቶ የሚባል አስጎብኚ ድርጅት በቅዱስ ላሊበላ እና ሌሎች መዳረሻዎች ላይ መጥተው ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፋለን የሚሉትን በመቃወም፤ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ የሃይማኖት አባቶች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ እና ህዝቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው መግለጫውን መስጠት ያስፈለገን'' ብለዋል።

ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የጉብኝት ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚታወቀው ቶቶ ቱርስ በኢትዮጵያ ከአራት ወራት በኋላ ለ14 ቀናት የሚዘልቅ የጉብኝት መርኃ ግብር አውጥቶ ጎብኚዎችን እየመዘገበ ይገኛል።
በአንድ ሰው 7 ሺህ 900 የአሜሪካን ዶላር የሚጠየቅበት ይህ የጉብኝት ፕሮግራም በሁለት ሳምንት ቆይታው አርባ ምንጭ፣ ደቡብ ኦሞ፣ የጣና ገዳማት፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምን እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማስጎብኘት መርሃ ግብር ቀርጿል።
ሊቀ ትጉሃን ደረጀ የማህበራት ህብረቱ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የለባቸውም የተባለበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ''በሃገሪቱ ህግ ድርጊቱ ወንጀል ነው። ከቀላል እስከ ከፍተኛ እስራት ያስቀጣል። ስለዚህ የኢትዮጵያን ሕግ ተላልፎ መምጣት አይችሉም። ሁለተኛ ድርጊቱ በሃይማኖት የተወገዘ ነው። በባህልም ጸያፍ ነው።'' ብለዋል።
''አርማቸውን ይዘው ላሊበላ ላይ እንገናኝ በማለት የዋጋ ተመን አውጠተው መንቀሳቀሳቸው የድፍረት ድፍረት ነው'' ሲሉም አክለዋል።
ይህ "እኩይ ተግባር" ከሃገራችን መውጣት አለበት የሚሉት ሊቀ ትጉሃን ደረጀ፤ ''ሕጉ ተሻሽሎ መጥበቅ አለበት። የግብረ-ገብ ትምህርት መሰጠት አለበት" ብለዋል፤ አክለውም ይህን ጉብኝት ተቃውመን አናቆምም።'' በማለት 'ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም' የሚባል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነትን የሚቃወም ከኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የተውጣጣ ሃገራዊ ማህበር እንደሚቋቋም ጨምረው ተናግረዋል።

የቶቶ አስጎብኚ ድርጅት መስራች እና ባለቤት ዳን ዌር በበኩላቸው ''በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለሁ። ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ ግን አንሰርዝም'' ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
''የየትኛውም የሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያስፈራው ነገር ያለ አይመስለኝም። የማንንም ሃይማኖት ልንጋፋም ሆነ የራሳችንን አስተሳሰብ በሰዎች ላይ ለመጫን አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምንሄደው። እንዳውም ባህሉን ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ለማድነቅ ነው የምንፈልገው።''
ጉብኝቱን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተመለከቱት ምላሽ በጣም እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት ዳን፤ "የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተለው ማሳሰብ እፈልጋለሁ" ብለዋል።
የአስጎብኚ ድርጅቱ ባለቤት በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንደማይሰርዙ አስረግጠው ተናግረዋል። ''ወደ ኢትዮጵያ እንሄዳለን። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለደህንነታችን እንሰጋለን'' ይላሉ።

ዳን ጉዳዩን ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚያሳውቁ፤ በተጨማሪም ስለ ጉብኝቱ ግዙፍ የዜና ተቋማት እንዲያውቁ እናደርጋለን ይላሉ።
''ወደ ኢትዮጵያ ስንሄድ አደጋ ቢደርስብን ዓለም በሙሉ ይመለከተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እና ሃይማኖት መጥፎ ስም እንዳይሰጠው መጠንቀቅ አለባቸው።'' ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጉዳዩ ላይ የባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት አስተያየት ማካተት አልቻልንም።

በአመት አንዴ ብቅ የምትለው ከውሃ በታች ያለችው የህንድ መንደር


የሳሉሊም ግድብ

ብቅ ጥልቅ ስለምትለው የህንድ መንደር ምን ያህል ያውቃሉ? በአመት ውስጥ ለአንድ ወር ብቻ የምትታየው የህንዷ ጎዋ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ከርዲ ከውሃ በታች ያለች መንደር ናት።
ለ11 ወራት ከውሃ በታች የምትቆየው መንደር ከውሃዋ ወጥታ ብቅ ስትል የቀድሞ ነዋሪዎቿ በደስታ ሊቀበሏት ከሚኖሩበት ቦታ ተሰባስበው ይመጣሉ።

መንደሯ በሁለት ኮረብታማ ቦታዎች ስር የምትገኝ ሲሆን በውስጧም ሳሉሊም የተባለ ወንዝ ያልፍባታል።
እንዲህ በውሃ ከመሸፈኗ በፊት በጎዋ ግዛት ሞቅ ያለች ከተማ ነበረች። በአካባቢው መንግሥት ግድብ መስራቱን ተከትሎ ከተማዋ በውሃ የተዋጠች ሲሆን፤ ከሰስት አሰርት አመታትም በፊት መኖሪያ መሆኗ በይፋ አቆመ።
ነገር ግን በየአመቱ ግንቦት ወር ላይ ውሃው ይሸሽና መንደሯ ትገለጣለች። የተሰነጣጠቀው መሬት፣ የዛፍ ቁጥቋጦዎች፣ የቤት ፍርስራሾችና የተሰባበሩ የቤት እቃዎችም በአንድ ወቅት ከተማነቷን ለማሳበቅ ይታያሉ።

ሶስት ሺ የሚሆኑ ነዋሪዎች ይኖሩባት የነበረችው መንደር መሬቷ ለም የነበረ ሲሆን፤ በኮኮዋ ዛፍ፣ ኦቾሎኒና በሌሎች ዛፎች የተሸፈነች ነበረች። ነዋሪዎቿም በእምነታቸው የተሰባጠሩ ሲሆኑ የሂንዱ፣ እስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች አንድ ላይ ይኖሩባት ነበር።
የተለያዩ የእምነት ቦታ ማምለኪያ ስፍራዎች የነበሯት ይህች መንደር የታዋቂው የክላሲክ ሙዚቀኛ ሙግባይ ኩርዲካር የትውልድ ስፍራ ናት።

የጎዋ ግዛት ከስድስት አስርት አመታት በፊት ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ስር ነፃ ስትወጣ ነው ብዙ ነገሮች መቀየር የጀመሩት። የመጀመሪያው የግዛቱ አስተዳዳሪ ግድብ ቢሰራ በከፍተኛ ሁኔታ ህዝቡን የሚጠቅም መሆኑን ለነዋሪዎቿ በማሳመን ግድቡ እንዲሰራ መገፋፋት ጀመሩ።
የኩርዲ መንደር
"ምንም እንኳን ግድቡ ሲሰራ መንደሯ ሙሉ በሙሉ በውሃ ልትሸፈን ብትችልም፤ ይህ መስዋዕትነት ግን ሁላችንም የሚጠቅምና ለትልቅ አላማ ነው" በማለት የግዛቱ አስተዳዳሪ መናገራቸውን የ75 አመቱ ጋጃናና ኩርዲካር ያስታውሳሉ።
እሳቸው እንደሚናገሩት ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ አባወራዎች በቅርብ ወደ ምትገኝ መንደር እንዲዘዋወሩ ተደርገው መሬትና ካሳ ተሰጣቸው።

የሳሉሊም የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ ፕሮጀክት በከፍተኛ ሁኔታ የተለጠጠ ነበር። መሰረቱንም በሳሉሊም ወንዝ ላይ አድርጎ ለመጠጥ የሚሆን ውሃን፣ መስኖንና አንዳንድ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችንም አጠቃሎ የያዘ ነበር። ለነዋሪዎቹም 400 ሚሊዮን ሊትር የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንም አቅዶ ነበር።
"ወደ አዲሷ መኖሪያችን ስንመጣ ምንም ነገር አልነበረንም" በማለት ከሶስት አስርት አመታት በፊት ወደ ሌላ መንደር ከተዛወሩት ቀደምት ከሆኑት አንደኛው ኢናሲዮ ሮድሪገስ ይናገራሉ። ቤታቸውንም እስከሚገነቡ ድረስ በጊዜያዊ መጠለያ የቆዩ ሲሆን ለአንዳንዶቹም አምስት አመታትን ያህል ፈጅቶባቸዋል።

ከአካባቢው ተነሱ ሲባል ጉራቻራን ኩርዲካር የአስር አመት ልጅ ነበር።
"ቤተሰቦቼ በጭነት መኪና እቃቸውን ጠቅልለው እንዲሁም እኔ፣ ወንድሜና አያቴም ተጭነን ስንሄድ ትንሽ፣ ትንሽ አስታውሳለሁ። ቤተሰቦቼም እያለቀሱ ነበር" በማለት በአሁኑ ሰአት የ42 አመት የሆነው ጉራቻራ ይናገራል።

እናቱ ማምታ ኩርዲካር እለቱን ትናንት የተፈጠረ ያህል በደንብ ታስታውሰዋለች። " የዛን እለት በፊት ምሽት በከፍተኛ ሁኔታ ዘንቦ ቤታችን አረስርሶት ነበር። በፍጥነት ከቤታችንም ወጥተን መሄድ ስለነበረብን፤ የዱቄት መፍጫየን አልወሰድኩም" በማለት ታስታውሳለች።

ነገር ግን ቃል እንደተገባላቸው የግድቡ ውሃ ለመንደሪቷ ነዋሪዎች አልደረሳቸውም።
ኩርዲካር በሚኖርበት አካባቢ ትልልቅ የውሃ ጉድጓዶች የሚገኙ ሲሆን በሚያዝያና ግንቦት ላይ ግን ይደርቃሉ። በዚህም ወቅት መንግሥት የሚለግሳቸውን የውሃ ታንከሮች መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።

አሁንም ቢሆን የጥንት መንደራቸው ትዝታ ሊለቃቸው ስላልቻለ ውሃው ሲሸሽ ተሰባስበው ወደ መንደሯ ይመጣሉ።
በጎዋ የሚኖር የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪው ቬኒሻ ፈርናንዴዝ ስለዚህ ቁርኝት የሚለው አለ " ለኩርዲ ነዋሪዎች ማንነታቸው ከመሬቱ ጋር በፅኑ የተሳሰረ ነው። ለዛም ነው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስታውሱት፤ ቦታው በውሃ ቢሸፈንም ይመላለሳሉ"

የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ፡ ኤስፔራንስ ዋንጫና ሜዳልያ እንዲመልስ ታዟል

የካዛብላንካ ተጨዋቾች 'ቫር' እንዲታይላቸው ሲማፀኑ ነበር

 አጭር የምስል መግለጫ የካዛብላንካ ተጨዋቾች 'ቫር' እንዲታይላቸው ሲማፀኑ ነበር 
 
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ካፍ የአህጉሪቱ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ ድጋሚ እንዲካሄድ አዟል፤ ዋንጫውን ያነሳውን ኤስፔራንስም ዋንጫውን ካነሳበት ያስቀምጥ ብሏል።
በአፍሪካ ክለቦች መካከል የሚደረገው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ የዘንድሮው በቱኒዚያው ኤስፔራንስ እና በሞሮኮው ካዛብላንካ መካከል ነበር የተካሄደው።
ጨዋታውን ኤስፔራንሶች 1 - 0 እየመሩ ሳለ ካዛብላንካዎች 1 በማስቆጠር አቻ ይሆናሉ። ነገር ግን የዕለቱ ዳኛ ጎሉን ይሽሩታል። ይህ ይልተዋጠላቸው ካዛብላንካዎች ሜዳውን ለቀው ይወጣሉ።

በዕለቱ ቫር [ረዳት የቪዲዮ ዳኛ] ቢኖርም 'ሲስተሙ' ባለመሥራቱ ምክንያት አጨቃጫቂዋን ጎል ድጋሚ ማየት አልተቻለም።
ዳኛው እስከ 95ኛው ደቂቃ ድረስ ከጠበቁ በኋላ ድሉ የኤስፔራንስ ነው ሲሉ አውጀዋል።
ተበደልን ያሉት ካዛብላንካዎች ፕሬዚዳንት 'የእግር ኳስ ቅሌት ሲሳይ' ሆነናል ሲሉ አማረሩ፤ ካፍም አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ 'እውነትም ተበድለዋል' ብሏል።
ካፍ ኤስፔራንስ የወሰደውን ዋንጫ እና ሜዳሊያ ከመለሰ በኋላ ድጋሚ ጨዋታ እንዲካሄድ አዟል፤ ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ ይሁንም ብሏል።

ጨዋታው ለሐምሌ 12 ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ከግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ።
ካፍ በመግለጫው 'የጨዋታ ሕግ እና ደንብ አልተከበረም' ስለዚህ ጨዋታው ድጋሚ ይካሄድ ዘንድ ግድ ነው የሚል አንቀፅ አስፍሯል።
የቢቢሲ ስፖርቱ ማኒ ጃዝሚ ኤስፔራንሶች ለካፍ ድክመት ነው እየተቀጡ ያሉት ይላል፤ ምክንያቱም በዕለቱ ቫር አለመሥራቱ የካፍ ጥፋት እንጂ የባለድሎቹ አልነበረም።

ከወለደች ከ30 ደቂቃዎች በኋላ የ10ኛ ክፍል ፈተና የወሰደችው እናት



የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ አልማዝ ደረሰ ዛሬ የጀመረውን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፤ ከወለደች ከ30 ደቂቃዎች በኋላ እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ሳለች ተፈትናለች።
የኢሉ አባ ቦራ ዞን መቱ ከተማ ነዋሪ የሆነችው አልማዝ ደረሰ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን ዛሬ ሰኞ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ የመጀመሪያ ልጇን ከተገላገለች በኋላ 2፡30 ላይ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅያ ፈተና መፈተኗን ለቢቢሲ ተናግራለች።
''የፈተናው ቀን እንዲራዘም መደረጉ ከምወልድበት ቀን ጋር እንዲጋጭ ሳያደርገው አልቀረም'' የምትለው አልማዝ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች።
ነብሰ ጡር ሆና የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ስትከታተል እንደነበረች የምታስታውሰው አልማዝ፤ እርግዝናዋ በትምህርቷ ላይ ያሳደረው ጫና እንዳልነበረ ትናገራለች።
ፈተናው ላይ ለመቀመጥ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የምታስረዳው አልማዝ፤ ዛሬ ፈተና በሚጀምርበት ዕለት ጠዋት ምጥ ሲይዛት ባለቤቷ ወደ ሆስፒታል ከወሰዳት በኋላ ለትምህርት ቢሮ ሰዎች ጉዳዩን በማሳወቅ ሆስፒታል ድረስ መጥተው እንደፈተኗት ታስረዳለች።
''ፈተናውን ለመፈተን ተጣድፌ ስለነበረ፤ ምጡ ምንም አልከበደኝም። ምንም ሳይመስለኝ ነው የወለድኩት''
''ፈተናውም በጣም ጥሩ ነበር'' ብላለች አልማዝ።
''መጀመሪያ ላይ ሊፈትናት የሚችል ሰው የለም ብለውኝ ነበር'' የሚለው ባለቤቷ አቶ ታደሰ ቱሉ ''መደበኛ ተማሪ መሆኗን ሲረዱ ግን በፍጥነት ሆስፒታል ድረስ ፈተና እንድትወስድ አመቻቹልን'' በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።
የኢሉ አባ ቦራ ኮሚኒኬሽንአልማዝ እና ታደስ
አጭር የምስል መግለጫ አልማዝ በሆስፒታል ውስጥ ፈተናውን ስትወስድ በፌደራል ፖሊስ ታጅባ ነበር።
አልማዝ እና ታደስ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት በፍቅር አብረው መኖራቸውን ይናገራሉ።
ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ ባይራዝም ኖሮ ነብሰ ጡር እያለች ነበር የምትወልደው ይላል አቶ ታደሰ።
አልማዝ በመምህሮቿ ዘንድ ተወዳጅ ተማሪ መሆኗን እና መምህሮቿም በእርግዝናዋ ምክንያት ፈተናው እንዳያመልጣት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበረ ሰምተናል።
''ነብሰ ጡር ስለነበረች ወደ መጨረሻ ላይ ሆዷ እየገፋ ሲሄድ ከበዳት እንጂ ጎበዝ ተማሪ ነች'' ይላል ባለቤቷ አቶ ታደሰ።
አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና በቀጣዮቹ ቀናት መሰጠቱ የሚቀጥል ሲሆን፤ አልማዝም ''የተቀሩትን ፈተናዎች እዛው ትምህርት ቤት ሄጄ እፈተናለሁ'' እያለች ነው።

አምስት ጂ ኢንተርኔት ምን አዲስ ነገር አለው? 5 G Internet and HUWAEI campany

ሁዋዌ


በኢትዮጵያ 3ጂ ኢንተርኔት ትግል ሲሆን ሌሎች ሃገራት ደግሞ ፈር ቀዳጅ ያሏቸውን የቴክኖሎጂ ውጤታቸውን እያስተዋወቁ ነው፤ እንግሊዝም ከሰሞኑ አምስት ጂ ኔትወርኳን አስተዋውቃለች።
ደንበኞች ለረጅም ጊዜ ከመጓጓታቸው አንፃር ብዙዎች የተደሰቱበት ቢሆንም ግራ መጋባቱ እንዳለም ተገልጿል።
በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ቴክኖሎጂው አዲስነት ዋጋው ብዙ የሚቀመስ አልሆነም፤ ኔትወርኩ በሁሉም አይነት ተንቀሳቃሽ ስልክ ስለማይሰራ ለዚህ ቴክኖሎጂ የሚሆን ስልክ ለመግዛት በአንድ ጊዜ የሚከፈል 7650 ብር ከዚያም በየወሩ 2430 ብር መክፈል ደንበኞች ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ክፍያ ግን በየወሩ 10 ጊጋ ባይት ዳታ ብቻ የሚጠቀሙ ከሆነ ነው እንጂ እንዲያው ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እጭናለሁ ካሉ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ ያስፈልጋል።
የአምስት ጂ ኔትወርክን በመጀመር ፈር ቀዳጅ የሆነው የእንግሊዙ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ቢቲ አካል የሆነው የተንቀሳቃሽ ስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪው ኢኢ የተባለው ድርጅት ነው።
ቮዳፎን የተሰኘው ድርጅትም በቅርቡ የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል። ነገር ግን ብዙዎች አገልግሎቱን ለመጠቀም አልተቻኮሉም፤ መጠበቅን መርጠዋል።

የተንቀሳቃሽ ስልኮችን የውስጥ ቁስ አምራች የሆነው ኳልኮም የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎት የሚሰጡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የባትሪ ቆይታቸው ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚሆን ቃል ገብቷል።

ምን ያህል ፈጣን ነው?
የእንግሊዝ ኮሚዩኒኬሽን ተቆጣጣሪው ድርጅት ኦፍ ኮም እንደሚለው የአምስት ጂ ኔትወርክ ፍጥነት በሰከንድ 20 ጊጋ ባይት እንደሚሆን ነው።
የአንድ ፊልም ጭብጡን እስኪያነቡ በሚወስደው ጊዜ ከፍተኛ ጥራት ያለውን ፊልሙን ዳውንሎድ አድርገው መጨረስ ይችላሉ እንደ ማለት ነው።

ነገር ግን ለአሁኑ ደንበኞች ብዙ እንዳይጠብቁ ድርጅቱ ያስጠነቅቃል፤ ምክንያቱም አገልግሎቱን የሚሰጠው ኢኢ የአምስት ጂ ኔትወርክ ለመዘርጋት የሚጠቀመው መስመር በሰከንድ ያለው ፍጥነት አስር ጊጋ ባይት ብቻ ሲሆን ይህ ለአንድ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎችም የሚጋራ ይሆናል።
በዚህም መሰረት በአማካኝ አንድ ደንበኛ የሚያገኘው የፍጥነት መጠን በሰከንድ 150-200 ሜጋ ባይት ሊሆን እንደሚችልና፤ ብዙ ሰው በማይጠቀምበት ወቅት ለአንዳንድ እድለኞች እስከ አንድ ጊጋ ባይት ሊደርስ ይችል ተብሏል።
ፈጣን ኢንተርኔት ብቻ ይሆን?
ምንም እንኳን ደንበኞችን ለመሳብ ለጊዜው የአምስት ጂ ኔትወርክ እየተዋወቀ ያለው ከፈጣን ኢንተርኔት ጋር በተያያዘ መልኩ ቢሆንም ለዘላቂው ግን አምስት ጂ ኔትወርክ ያላቸው ስልኮች በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ስልኮች በላይ መገናኘት የሚያስችል ኔትወርክ ተዘርግቶላቸዋል።
ነገር ግን ይህንን ሁሉ ለማከናወን ከአውቶብስ ማረፊያ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች አዳዲስ አንቴናዎች መትከል ያስፈልጋል ተብሏል።

ከግለሰቦች በተጨማሪ የደንበኞችን መረጃ በመሰብሰብ ለንግድም ሆነ እንዲሁም ለደህንነት ሥራ ለሚጠቀሙበት ለመንግሥትም ሆነ ለተለያዩ ድርጅቶችም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ደንበኞች በሚፈልጉት መጠን ኔትወርክ የሚያከፋፍል ሲሆን ለምሳሌ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ደንበኞችም ዩቲዩብና ሌሎች ዳታን የሚጨርሱ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ምንም እንዳይደናቀፉ ይደረጋል። ይህ ከጥቂት ዓመታትም በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

የሁዋዌስ ነገር እንዴት ነው?

ከደህንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የቻይናው ኩባንያ ሁዋዌ የአምስት ጂ ኔትወርክ እቅዱ እገዳ ይገጥመዋል ተብሏል።
ባለፈው ወር ኩባንያው ለአምስት ጂ ኔትወርኩ አንቴናና ሌሎችም ቁሶች ፍቃድ ሊሰጠው የሚመስሉ ፍንጮች ቢታዩም የጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን መልቀቅ ተከትሎ የማይሆን ነው ተብሏል።
የኩባንያውን መሰረተ ልማት ማገዱ ለአገልግሎት ሰጪዎቹ ራስ ምታት እንደሚሆን እየተነገረ ነው። ኢኢና ቮዳፎን ይጠቀሙባቸው የነበሩ የሁዋዌ የውስጥ አካላትን እንዳይጠቀሙ ከተገደዱ ሥራቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያከብደ እየተነገረ ነው።

ሁለቱም ድርጅቶች እንደገለፁት የሁዋዌ መገለገያዎችን የውስጥ ክፍሎች መሀንዲሶቻቸው ለመተካት ከተገደዱ የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎታቸውን ሊያዘገየው እንደሚችል ነው።
የአገሪቱ ስልክ አምራቾችም ሆነ ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሁዋዌ ጋር በመነካካታቸው ብዙ ነገሮች ሊወሳሰቡ ይችላሉ እየተባለ ነው።
ምንም እንኳን አምስት ጂ ኢንተርኔትን ለመጀመር ከአውሮፓ ሃገራት እንግሊዝ ፈር ቀዳጅ ብትሆንም ከሁዋዌ ጋር በተያያዘ ለመላው አገሪቷ ሽፋን ለመስጠት እንቅፋት እንደሚሆንና ሌሎቹም ሊቀድሟት ይችላሉ እየተባለ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተሳሳተው ካርታ ይቅርታ ጠየቀ


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ለተጠቀመው የተሳሳተ ካርታ ይቅርታ ጠየቀ።
ሶማሊያን የኢትዮጵያ አካል አድርጎ በወጣው ካርታ በመላው ዓለም የሚገኙ ሶማሊያውያን ተቃውሞ አሰምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተሳሳተውን የአፍሪካ ካርታ ከድረገጹ እንዲወርድ መደረጉን ገልጸው ሁኔታው እንዴት እንደተከሰተ በማጣራት ላይ ነን ብለዋል።
ካርታው ከሶማሊያ ሌላ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም ድንበሮች በተሳሳተ መልኩ የሚያሳይ በመሆኑ ውዝግቡን አጠናክሮታል።
አቶ ነቢያት ካርታውን በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት ድረገጽ ላይ ማን እንደለጠፈ አናውቅም ማለታቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ቅዳሜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረገጽ ላይ የወጣው ካርታ ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅሏታል።
ሶማሌላንድን ደግሞ በሉአላዊ ሀገርነት ድንበርና ግዛት ያላት አድርጎ ያሳያታል።
ደቡብ ሱዳን በካርታው ላይ የለችም። ሁለቱን ኮንጎዎች ተቀላቅለው በአንድ ሀገርነት ቆመዋል።
ስዋዚላንድና ሌሴቶም ካርታው ላይ አይታዩም። ኢኳቴሪያል ጊኒም እንዲሁ።
ካርታው ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረው የዚያኑ ዕለት የሶማሊያ አክቲቪስቶች በቲውተር ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካን ሬዲዮ የሶምሊኛ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ከዚህ ካርታ ላይ ሶማሊያ የት እንዳለች ሊያሳየኝ የሚችል ማን ነው? የሚል ጥያቄ አንስቶ በቲውተር ላይ የተሳሳተውን ካርታ በመለጠፍ የጻፈው የቲውተር መልዕክት በመላው ዓለም የሶማሊያ ተወላጆችን ትኩረት በመሳቡ ተቃውሞ መነሳቱን ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስህተቱ እንዴት እንደተፈጠረ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል።
ወዲያውኑ ካርታው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ መነሳቱን ነው አቶ ነቢያት ለጋዜጠኞች የገለጹት።
በዚህም ለተፈጸመው ስህተት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይቅርታ ይጠይቃል ብለዋል።
በተሳሳተው ካርታ ምትክ ትክክለኛው እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት አቶ ነቢያት ጌታቸው የተሳሳተው ምስል በድረ ገጹ ላይ በማን እና እንዴት እንደወጣ በሚመለከተው አካል ማጣራት እየተደረገበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ካርታው ከየት እንደተገኘና ማን ድረ ገጹ ላይ እንደለጠፈው ገና አልታወቀም ብለዋል አቶ ነቢያት።
መስሪያ ቤታቸው ካርታ የሚጠቀመው ከኢትጵያ ካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ መሆኑን የገለጹት አቶ ነቢያት ይህኛውን የተሳሳተውን ለምን ዓላማ እንደተለጠፈ እያጣራን ነው ሲሉ መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጉዳዩንም አጣርተን ርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

ሳዑዲ ለኢትዮጵያውያን የሰጠችውን ቪዛ ሰረዘች


ሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ ለስራ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የሰጠችውን ቪዛ መሰረዟን አስታወቀች።
የሳዑዲ አረቢያ የስራና ሰራተኞች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቪዛው የተሰረዘው ከኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በስራ ቅጥር ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ነው።
ፋይል
ከረመዳን ጾም መግባት አስቀድሞ ሳዑዲ አረቢያ መድረስ ያለባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ስምምነት ባለመደረሱ ምክንያት መቅረታቸው ታውቋል።
ሳዑዲ አረቢያ በቅጥር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ልዩነት መኖሩን ከመግለጽ ባሻገር ዝርዝር መረጃ አላቀረበችም።
ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደርግነው ጥረት የሚመለከታቸው ሃላፊዎች የሉም የሚል ምላሽ በመሰጠቱ አልተሳካልንም።
የሳዑዲ አረቢያን የስራና የማህበራዊ ልማት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሳዑዲ ጋዜጣ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን መቅጠሯን ለጊዜው አቁማለች።
በኢትዮጵያ በኩል ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም የሚለው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በዚህም ምክንያት ቪዛ ተሰጥቷቸው ወደ ሳዑዲ ሊገቡ በዝግጅት ላይ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ቪዛቸው መሰረዙን አስታውቋል።
የረመዳን ጾም ከመግባቱ በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይገባሉ ተብለው በሳዑዲ ባለስልጣናት ፍቃድ ቪዛ የተሰጣቸው እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሁለቱ ሃገራት መካከል ይደርሳል የተባለው ስምምነት ባለመሳካቱ በታቀደው ጊዜ ሳዑዲ አረቢያ መግባት እንዳልቻሉ ነው ዘገባው የሚያመለክተው።
ሳዑዲ አረቢያ በዝርዝር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈጠረውን ልዩነት አልገለጸችም።
ልዩነቱ ግን ጥልቅና ሰፊ መሆኑን የስራና ማህበራዊ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ባለፈው ከሁለት ሳምንት በፊት በሁለቱ ሀገራት የሚመለከታቸው ባለስልጣናት መካከል ውይይት መደረጉንና ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያኑን ቪዛ ከሰረዘች በኋላ ሀገሯ ገብተው መስራት ከፈቀደችላቸው 19 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ማስወጣቷን ሳዑዲ ጋዜጣ ዘግቧል።
ጋዜጣው በኢትዮጵያ በኩል ለዜጎቿ የጤንነት ምርመራ ማዕከል ለመመስረት ፍቃደኛ አይደለችም ሲል ስምምነቱ እንዳይደረስ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ስምምነት ላለመደረሱ የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ ማድረጉም ተገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ ለስምምነቱ ያሳየችውን ቀናነት በኢትዮጵያ በኩል አልታየም ነው የሚሉት።
ጉዳዩን በተመለከተ ወደ ኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደውለን በስም ያልተገለጹልን ሃላፊ ቀርበው ስለጉዳዩ የማውቀ ነገር የለም፣ የሚመለከተው አካል ለጊዜው በቢሮው የለም ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተውናል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ክፍል በተሰጠን ስልክ በመደወል ሃላፊውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።
የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የስራ ዋስትናና ደህንነት በተመለከተ የቀደመው የስራ ኮንትራት አሰራር መቀየር እንዳለበት በማመን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተለያዩ አዳዲስ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን በደልና የደሞዝ መከልከል ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በትኩረት የተነሳ ጉዳይ መሆኑም ተመልክቷል።
በሳዑዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ለስራ የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ህገወጥ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ተገለጸ


በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ህገወጥ ተግባራትን የሚያከናውነው ኦነግ ሳይሆን በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አስታወቀ።
በኦነግ ትዕዛዝ ስር የሚተዳደር ወታደራዊ ሃይል የለኝም ሲል ግንባሩ ገልጿል።

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዘጡት ቃለመጠይቅ እንደገለጹት ኦነግ ታጣቂ ሃይሎቹን ለአባገዳዎች አስረክቦ በሰላማዊ መንገድ ትግሉ ቀጥሏል።
በኦነግ ስም በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ቡድኖች ኦነግን አይወክሉም ብለዋል አቶ ቶሌራ።
መንግስት ጉዳዩን አጣርቶ እውነቱ ላይ መድረስ አለበት ሲሉ ጥሪ ያደረጉት አቶ ቶሌራ ኦነግ ባልሰራው እየተወነጀለ ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃለአቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ኦነግ ወታደር የለውም ሲሉ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በሰሜን ሸዋ አጣዬና በወሎ ከሚሴ ግጭት በተፈጠረበትና የኦነግ ስም በተጠቀሰበት ጥቃት ድርጅታቸው ምንም ዓይነት ሰራዊት የሚያዝ እንዳልሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ መግለጫ የሰጡት አንድ የኦነግ ሰራዊት ኮማንደር ነኝ ያሉ ግለሰብ የኦነግ ፖለቲካዊ አመራር የተለየ መሆኑን በመጥቀስ ወታደራዊ ክንፉ አሁንም ትግል ላይ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህንኑ አቋማቸውን በድጋሚ የገለጹት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በአሁኑ ወቅት በኦነግ ትዕዛዝ የሚተዳደር ወታደራዊ ኃይል የለም ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ግንባሩ ቀደም ሲል ታጣቂ ኃይል ነበረው ያሉት ቃል አቀባዩ ወታደሮቹን ለአባገዳ እና ለኦሮሞ ህዝብ ካስረከበ ወዲህ ወታደሮች የሉትም ሲሉ በቃለመጠይቃቸው ላይ ገልጸዋል።
ኦነግ የመነግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሀገር ቤት የገባው በድጋሚ መሳሪያ ለማንሳት አይደለም ሲሉ የገለጹት አቶ ቶሌራ ግንባሩ በአሁኑ ወቅት የትጥቅ ትግሉን ማቆሙን በይፋ ገልጾ መሳሪያ የሚያነሳበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብለዋል።
በኦነግ ትዕዛዝ ስር የሚተዳደር ወታደራዊ ኃይል አሁን እንደሌለም አረጋግጣለሁ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
ምንም እንኳን ቃል አቀባዩ አቶ ቶሌራ ኦነግ ታጣቂዎች እንደሌሉት ቢገልጹም በተለያዩ አከባቢዎች በኦነግ ስም የሚካሄደው ጥቃት እንደቀጠለ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ጉጂ 10 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት የኦነግ ስም ተጠቅሶ ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለ መነገሩ የሚታወስ ነው።
ኦነግ በሶስት አከባቢዎች አሁንም ይንቀሳቀሳል የሚለው የነዋሪው አስተያየት በኦነግ ስም የሚፈጸሙ ጥቃቶች አለመቆማቸው አሳሳቢ ደረጃ ይገኛልም ሲሉ አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ግን በኦነግ ስም እየተንቀሳቀሱ የሚዘርፉ እንዳሉ አልሸሸጉም።
በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ቡድኖች አሉ ፣ቡድኖቹ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ እንጂ በድርጅት መልክ የሚንቀሳቀሱ አይደሉም ነው ያሉት አቶ ቶሌራ።
በዝርፊያ፣ በስርቆትና በመሰል ነገሮች የተሰማሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የኦነግን መለያ ምልክት ይዘው መንገድ ላይ ተሽከርካሪ አስቁመው የሚዘርፉ እንዲሁም በኦነግ ስም በየመንደሩ እየተዘዋወሩ በሬ፣ ገንዘብ አምጡ የሚሉ ለዝርፊያ ብቻ ተሰባስበው የሚበተኑ ቡድኖች መኖራቸውን የጠቀሱተቶ ቶሌራ ይህን መንግስት አጣርቶ እውነቱን ማሳወቅ እንዳለበት በመግለጽ ጥሪ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ኦነግ የሚያደራጀው ሲቪልን ብቻ ነው አባሎቹም ሲቪሎች ናቸው ሲሉ አቶ ቶሌራ አደባ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ የእነ አቶ ጌታቸው አሰፋን መጥሪያ ማድረስ አልቻልኩም ሲል ገለፀ

የፌደራል ፖሊስ በሌሉበት ጉዳየቸው እየታየ ያለው እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተሰጠው የመጥሪያ ትዕዛዝ በጊዜ ከፍርድ ቤት ባለመውጣቱ ማድረስ አልቻልኩም ሲል ገለፀ።

የፌደራል ፖሊስ ትዕዛዙ የተሰጠው ግንቦት ስምንት ቢሆንም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት የወጣው ግንቦት 14 በመሆኑ ትግራይ ክልል ድረስ ሄዶ ለተከሳሾች ለማድረስ የጊዜ ዕጥረት አጋጥሞኛል ብሏል።
የቀድሞው የደህንነት ሐላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች ችሎት እንዲቀርቡና መጥሪያ እንዲደርሳቸው  ፍርድ ቤት አዞ ነበር።
የፌዴራል ፖሊስ ግን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተሰጠውን ትዕዛዝ እስካሁን አላደረሰም።
ፌዴራል ፖሊስ ለዚህ የሰጠው ምክንያትም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት ሳይወጣ ስልዘገየብኝ ነው ብሏል።
እንደ ፌዴራል ፖሊስ ገለጻ ትዕዛዙ በፍርድ ቤት የተሰጠው ግንቦት ስምንት ቢሆንም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት የወጣው ግንቦት 14/2011 ዓም ነው።
እናም ትዕዛዙን ተግባራዊ ለማድረግ ፌደራል ፖሊስ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል ።
ፍርድቤቱም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ ለሰኔ 3 ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለምስክርነት ያቀረበውን የሲዲ ማስረጃ ለተከሳሾች እንዲያደርስ በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ከአንድ ሲዲ በስተቀር ሁሉንም በማድረስ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጿል።
አቃቢ ህግ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምስክርነት እየሰጡ ያሉ አካላት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ማንነታቸው ሳይታወቅ ምስክርነት እንዲሰጡ ይፈቀድለት ዘንድ የምስክርነትና የወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ 690/2003 በመጥቀስ ጠይቋል።
ፍርድቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይም ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 3 ቀጠሮ ሰጥቷል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ተከሳሾች በበኩላቸው ደሞዛቸው በመቆሙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን ጠቅሰው ለፍርድቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ግን ይህ ፍርድ ቤት ደሞዝ ክፈል አትክፈል የማለት ህጋዊ መሰረት ስለሌው ለሲቪል ሰርቪስ ወይም ለሚመለከተው አካል ማመልከት ትችለላችሁ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

wanted officials