የጃፓን ሚኒስትር ሴቶችን ታኮ ጫማ እንዲጫሙ የሚያስገድደው የሥራ ቦታ የአለባበስ ስርዓትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናገሩ።
የጃፓን
ጤናና ሰራተኛ ሚኒስትር የሆኑት ታኩሚ ኔሞቶ፣ ይህንን አከራካሪ ልምድ " በሥራ ቦታ ላይ አስፈላጊና ተገቢ የሆነ
ነገር እንዲሁም ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው" በማለት ደግፈው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።ይህንን አስተያየት የሰጡት የሕዝብ እንደራሴዎች ኮሚቴ ረቡዕ ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት ነው።
ወዲያውኑ አንድ ሕግ አውጪው አባል የሆኑ ግለሰብ እንዲህ አይነት ሕጎች "ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው" ሲሉ የሚኒስትሩን ሀሳብ አጣጥለውታል።
ሚኒስትሩ በጃፓን በአንዲት ተዋናይት ስለተጀመረውና በሥራ ቦታ ላይ አግላይ የሆነ የአለባበስ ስርዓትን የሚያዘው ደንብ እንዲሻር ስለሚጠይቀው የፊርማ ማሰባሰብ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር ይህንን ያሉት።
ተዋናይቷ ታኮ ጫማ በሥራ ቦታ ላይ መጫማትን የሚያዘውን ደንብ እንዲነሳ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመረችው የቀብር አስፈፃሚዎች ደንቡን እንዲያከብሩ ከታዘዙ በኋላ ነው።
የፊርማ ማሰባሰቡ ዘመቻ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቶላታል።
የተሰበሰበው 18 ሺህ 800 ፊርማም ለጃፓን ሰራተኛ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ገቢ የተደረገ ሲሆን ደጋፊዎቹም የትዊተር ዘመቻ ጀምረዋል።
የዚህ ዘመቻ መሪዎች እንደሚናገሩት በጃፓን አንዲት ሴት ለሥራ ስታመለክት ታኮ ጫማ ማድረግ እንደ ግዴታ ይቀርብላታል።
"ይህ ዘመቻ ማህበራዊ ቅቡልነት ያለውን ይህ ተግባር አስወግዶ ሴት ልጅ እንደ ወንድ ማንኛውንም ጫማ አድርጋ በሥራ ገበታዋ ላይ እንድትገኝ ይፈቅዳል የሚል እምነት አለኝ" ብላለች የዘመቻው መሪ ኢሺካዋ።
ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ አንዲት ሴት በጊዜያዊነት በተቀጠረችበት የፋይናንስ መሥሪያ ቤት ታኮ ጫማ ካላደረግሽ ተብላ መገደዷ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን በማግኘቱ ብቻ ድርጅቶች ሴቶች የፈለጉትን መጫማት እንደሚችሉ ገልፀው ነበር።
እ.ኤ.አ በ2017 በአንዲት የካናዳ ግዛት ሴቶች ታኮ ጫማ እንዲጫሙ የሚያዝዘውን ደንብ ከሥራ ውጪ ማድረጋቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ተራው የጃፓን ይመስላል።
No comments:
Post a Comment