Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 10, 2019

ከወለደች ከ30 ደቂቃዎች በኋላ የ10ኛ ክፍል ፈተና የወሰደችው እናት



የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ አልማዝ ደረሰ ዛሬ የጀመረውን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፤ ከወለደች ከ30 ደቂቃዎች በኋላ እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ሳለች ተፈትናለች።
የኢሉ አባ ቦራ ዞን መቱ ከተማ ነዋሪ የሆነችው አልማዝ ደረሰ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን ዛሬ ሰኞ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ የመጀመሪያ ልጇን ከተገላገለች በኋላ 2፡30 ላይ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅያ ፈተና መፈተኗን ለቢቢሲ ተናግራለች።
''የፈተናው ቀን እንዲራዘም መደረጉ ከምወልድበት ቀን ጋር እንዲጋጭ ሳያደርገው አልቀረም'' የምትለው አልማዝ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች።
ነብሰ ጡር ሆና የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ስትከታተል እንደነበረች የምታስታውሰው አልማዝ፤ እርግዝናዋ በትምህርቷ ላይ ያሳደረው ጫና እንዳልነበረ ትናገራለች።
ፈተናው ላይ ለመቀመጥ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የምታስረዳው አልማዝ፤ ዛሬ ፈተና በሚጀምርበት ዕለት ጠዋት ምጥ ሲይዛት ባለቤቷ ወደ ሆስፒታል ከወሰዳት በኋላ ለትምህርት ቢሮ ሰዎች ጉዳዩን በማሳወቅ ሆስፒታል ድረስ መጥተው እንደፈተኗት ታስረዳለች።
''ፈተናውን ለመፈተን ተጣድፌ ስለነበረ፤ ምጡ ምንም አልከበደኝም። ምንም ሳይመስለኝ ነው የወለድኩት''
''ፈተናውም በጣም ጥሩ ነበር'' ብላለች አልማዝ።
''መጀመሪያ ላይ ሊፈትናት የሚችል ሰው የለም ብለውኝ ነበር'' የሚለው ባለቤቷ አቶ ታደሰ ቱሉ ''መደበኛ ተማሪ መሆኗን ሲረዱ ግን በፍጥነት ሆስፒታል ድረስ ፈተና እንድትወስድ አመቻቹልን'' በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።
የኢሉ አባ ቦራ ኮሚኒኬሽንአልማዝ እና ታደስ
አጭር የምስል መግለጫ አልማዝ በሆስፒታል ውስጥ ፈተናውን ስትወስድ በፌደራል ፖሊስ ታጅባ ነበር።
አልማዝ እና ታደስ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት በፍቅር አብረው መኖራቸውን ይናገራሉ።
ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ ባይራዝም ኖሮ ነብሰ ጡር እያለች ነበር የምትወልደው ይላል አቶ ታደሰ።
አልማዝ በመምህሮቿ ዘንድ ተወዳጅ ተማሪ መሆኗን እና መምህሮቿም በእርግዝናዋ ምክንያት ፈተናው እንዳያመልጣት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበረ ሰምተናል።
''ነብሰ ጡር ስለነበረች ወደ መጨረሻ ላይ ሆዷ እየገፋ ሲሄድ ከበዳት እንጂ ጎበዝ ተማሪ ነች'' ይላል ባለቤቷ አቶ ታደሰ።
አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና በቀጣዮቹ ቀናት መሰጠቱ የሚቀጥል ሲሆን፤ አልማዝም ''የተቀሩትን ፈተናዎች እዛው ትምህርት ቤት ሄጄ እፈተናለሁ'' እያለች ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials