Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, June 13, 2019

ጎንደር በመሄድ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት አለኝ የሚለው ኬንያዊ

ጎንደር በመሄድ የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት አለኝ የሚለው ኬንያዊ ቢላ ይዞ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ጥሶ ለመግባት ሲሞከር በጠባቂዎቹ ተተኩሶበት ቆስሎ ተይዟል።
በፌስቡክ ገጹ ላይ በኬንያ መሪዎች ስር ከመተዳደር ጎንደር ውስጥ የቤት ውስጥ አገልጋይ ሆኖ መኖርን እንደሚመርጥ የሚናገረው ብሪያን ኪቤት ቤራ ሰኞ እለት ነበር ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለመግባት የሞከረው።
በጆሞ ኬንያታ የግብርናና የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የአምስተኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ብራያን ሊገባ ሲባል ግራ ትከሻው ላይ በጥይት ከቆሰለ በኋላ ሆስፒታል ገብቷል።
ፖሊስ እንዳለው የ25 ዓመቱ ብሪያን ኪቤት ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመግባት ሲሞክር የተመለከተው የጥበቃ መኮንን ግለሰቡ የአእምሮ ህመምተኛ ሊሆን ይችላል በሚል ለሞት በማያበቃው ቦታ ላይ በጥይት እንደመታው ፖሊስ ገልጿል።
ብሪያን በተደጋጋሚ በፌስቡክ ገጹ ላይ ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ “ሌባ” የሚላቸውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን እንደሚገድል ይጽፍ ነበር። ሰሞኑንም ይህንን ዛቻውን ለመፈጸም ሙከራ አድረጓል።
የ25 ዓመቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በተደጋጋሚ መንግሥትን የሚጻረሩ በተለይ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በማጥላላት የተሞሉ ሃተታዎችን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፍር ነበር። አቋሙን ለመደገፍም የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያጣቅስ እንደነበር የተለያዩ የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የተለያዩ የታሪክ መጽሃፍትን እንዳነበበ የሚገመተው ብሪያን ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ጎንደር ውስጥ መኖር እንደሚፈልግ ጠንከር ባለ ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲጽፍ እንደነበረም ተነግሯል።
በአንድ ጽሁፉ ላይም “ይህ መልዕክት መሬቴንና ርስቴን ለዘረፉኝ ለፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ለህዝባቸው እንዲደርስ ይሁን። ኬንያ ውስጥ መሪ ከምሆን ኢትዮጵያ ውስጥ አገልጋይ ብሆን ይሻለኛል” ሲል አስፍሯል።
ወደጎንደር የመሄድ ፍላጎቱን በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ተማሪው “ከጠላቶቼ ጋርም ጦርነት አውጃለሁ። ምክንያቴ ደግሞ ወደ ጎንደር የምሄድበትን ገንዘብ ለማግኘት ነው” ብሏል።
“ሞኝ (ጨቋኝ) መሪ ከመሆን የብልሆች ባሪያ መሆንን እመርጣለሁ” የሚለው ብሪያን ጎንደር በመሄድ ብልህ ለሆኑት ህዝቦች አገልጋይ መሆን እንደሚፈልግ ጠቅሶ ለጉዞው የሚያስፈልገውን ገንዘብ አለማግኘቱ እንዳዘገየው አስፍሯል።
ስለጎንደርና ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በማህበራዊ ገጹ ላይ እንደሚጽፍ የተነገረው ይህ ወጣት በእያንዳንዱ ጽሁፉ ማብቂያ ላይ “ከኢትዮጵያዊው ልዑል፤ ቀድሞ ብሪያን ኪቤት ቤራ ተብሎ ይጠራ የነበረው” ሲል ያሰፍራል።
ብራያን ወደ ቤተመንግሥቱ ለመግባት ካደረገው ሙከራ ቀደም ብለው ጽሁፎቹ በመመልከት በርካቶች የተለያዩ ሃሳቦች የሰነዘሩ ሲሆን በርካቶች ድርጊቱን የተቃወሙ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የአእምሮ ጤንነቱን ተጠራጥረዋል።
BBC AMHARIC

No comments:

Post a Comment

wanted officials