Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 10, 2019

''ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም'' የቶቶ አስጎብኚ ድርጅት TOTO tours Homosexuals tour in Ethiopia

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሰንደቅ


ትናንት ከ120 በላይ የኦርቶዶክስ ማህበራት ስብስብ የሆነው ሰልስቱ ምእት የማህበራት ህብረት በቅርቡ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን በኢትዮጵያ ሊያደርጉ ያሰቡትን ጉብኝት በማስመልከት የተቃውሞ ድምጹን ለማሰማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል የጉብኝቱ አዘጋጅ በኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ አንሰርዝም እያሉ ነው።
የማህበራት ህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ ለቢቢሲ እንደገለፁት ''ቶቶ የሚባል አስጎብኚ ድርጅት በቅዱስ ላሊበላ እና ሌሎች መዳረሻዎች ላይ መጥተው ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፋለን የሚሉትን በመቃወም፤ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ የሃይማኖት አባቶች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ እና ህዝቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው መግለጫውን መስጠት ያስፈለገን'' ብለዋል።

ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የጉብኝት ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚታወቀው ቶቶ ቱርስ በኢትዮጵያ ከአራት ወራት በኋላ ለ14 ቀናት የሚዘልቅ የጉብኝት መርኃ ግብር አውጥቶ ጎብኚዎችን እየመዘገበ ይገኛል።
በአንድ ሰው 7 ሺህ 900 የአሜሪካን ዶላር የሚጠየቅበት ይህ የጉብኝት ፕሮግራም በሁለት ሳምንት ቆይታው አርባ ምንጭ፣ ደቡብ ኦሞ፣ የጣና ገዳማት፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምን እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማስጎብኘት መርሃ ግብር ቀርጿል።
ሊቀ ትጉሃን ደረጀ የማህበራት ህብረቱ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የለባቸውም የተባለበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ''በሃገሪቱ ህግ ድርጊቱ ወንጀል ነው። ከቀላል እስከ ከፍተኛ እስራት ያስቀጣል። ስለዚህ የኢትዮጵያን ሕግ ተላልፎ መምጣት አይችሉም። ሁለተኛ ድርጊቱ በሃይማኖት የተወገዘ ነው። በባህልም ጸያፍ ነው።'' ብለዋል።
''አርማቸውን ይዘው ላሊበላ ላይ እንገናኝ በማለት የዋጋ ተመን አውጠተው መንቀሳቀሳቸው የድፍረት ድፍረት ነው'' ሲሉም አክለዋል።
ይህ "እኩይ ተግባር" ከሃገራችን መውጣት አለበት የሚሉት ሊቀ ትጉሃን ደረጀ፤ ''ሕጉ ተሻሽሎ መጥበቅ አለበት። የግብረ-ገብ ትምህርት መሰጠት አለበት" ብለዋል፤ አክለውም ይህን ጉብኝት ተቃውመን አናቆምም።'' በማለት 'ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም' የሚባል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነትን የሚቃወም ከኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የተውጣጣ ሃገራዊ ማህበር እንደሚቋቋም ጨምረው ተናግረዋል።

የቶቶ አስጎብኚ ድርጅት መስራች እና ባለቤት ዳን ዌር በበኩላቸው ''በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለሁ። ወደ ኢትዮጵያ የምናደርገውን ጉዞ ግን አንሰርዝም'' ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
''የየትኛውም የሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያስፈራው ነገር ያለ አይመስለኝም። የማንንም ሃይማኖት ልንጋፋም ሆነ የራሳችንን አስተሳሰብ በሰዎች ላይ ለመጫን አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምንሄደው። እንዳውም ባህሉን ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ለማድነቅ ነው የምንፈልገው።''
ጉብኝቱን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተመለከቱት ምላሽ በጣም እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት ዳን፤ "የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተለው ማሳሰብ እፈልጋለሁ" ብለዋል።
የአስጎብኚ ድርጅቱ ባለቤት በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንደማይሰርዙ አስረግጠው ተናግረዋል። ''ወደ ኢትዮጵያ እንሄዳለን። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለደህንነታችን እንሰጋለን'' ይላሉ።

ዳን ጉዳዩን ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚያሳውቁ፤ በተጨማሪም ስለ ጉብኝቱ ግዙፍ የዜና ተቋማት እንዲያውቁ እናደርጋለን ይላሉ።
''ወደ ኢትዮጵያ ስንሄድ አደጋ ቢደርስብን ዓለም በሙሉ ይመለከተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እና ሃይማኖት መጥፎ ስም እንዳይሰጠው መጠንቀቅ አለባቸው።'' ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጉዳዩ ላይ የባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤት አስተያየት ማካተት አልቻልንም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials