Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 10, 2019

በአመት አንዴ ብቅ የምትለው ከውሃ በታች ያለችው የህንድ መንደር


የሳሉሊም ግድብ

ብቅ ጥልቅ ስለምትለው የህንድ መንደር ምን ያህል ያውቃሉ? በአመት ውስጥ ለአንድ ወር ብቻ የምትታየው የህንዷ ጎዋ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ከርዲ ከውሃ በታች ያለች መንደር ናት።
ለ11 ወራት ከውሃ በታች የምትቆየው መንደር ከውሃዋ ወጥታ ብቅ ስትል የቀድሞ ነዋሪዎቿ በደስታ ሊቀበሏት ከሚኖሩበት ቦታ ተሰባስበው ይመጣሉ።

መንደሯ በሁለት ኮረብታማ ቦታዎች ስር የምትገኝ ሲሆን በውስጧም ሳሉሊም የተባለ ወንዝ ያልፍባታል።
እንዲህ በውሃ ከመሸፈኗ በፊት በጎዋ ግዛት ሞቅ ያለች ከተማ ነበረች። በአካባቢው መንግሥት ግድብ መስራቱን ተከትሎ ከተማዋ በውሃ የተዋጠች ሲሆን፤ ከሰስት አሰርት አመታትም በፊት መኖሪያ መሆኗ በይፋ አቆመ።
ነገር ግን በየአመቱ ግንቦት ወር ላይ ውሃው ይሸሽና መንደሯ ትገለጣለች። የተሰነጣጠቀው መሬት፣ የዛፍ ቁጥቋጦዎች፣ የቤት ፍርስራሾችና የተሰባበሩ የቤት እቃዎችም በአንድ ወቅት ከተማነቷን ለማሳበቅ ይታያሉ።

ሶስት ሺ የሚሆኑ ነዋሪዎች ይኖሩባት የነበረችው መንደር መሬቷ ለም የነበረ ሲሆን፤ በኮኮዋ ዛፍ፣ ኦቾሎኒና በሌሎች ዛፎች የተሸፈነች ነበረች። ነዋሪዎቿም በእምነታቸው የተሰባጠሩ ሲሆኑ የሂንዱ፣ እስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች አንድ ላይ ይኖሩባት ነበር።
የተለያዩ የእምነት ቦታ ማምለኪያ ስፍራዎች የነበሯት ይህች መንደር የታዋቂው የክላሲክ ሙዚቀኛ ሙግባይ ኩርዲካር የትውልድ ስፍራ ናት።

የጎዋ ግዛት ከስድስት አስርት አመታት በፊት ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ስር ነፃ ስትወጣ ነው ብዙ ነገሮች መቀየር የጀመሩት። የመጀመሪያው የግዛቱ አስተዳዳሪ ግድብ ቢሰራ በከፍተኛ ሁኔታ ህዝቡን የሚጠቅም መሆኑን ለነዋሪዎቿ በማሳመን ግድቡ እንዲሰራ መገፋፋት ጀመሩ።
የኩርዲ መንደር
"ምንም እንኳን ግድቡ ሲሰራ መንደሯ ሙሉ በሙሉ በውሃ ልትሸፈን ብትችልም፤ ይህ መስዋዕትነት ግን ሁላችንም የሚጠቅምና ለትልቅ አላማ ነው" በማለት የግዛቱ አስተዳዳሪ መናገራቸውን የ75 አመቱ ጋጃናና ኩርዲካር ያስታውሳሉ።
እሳቸው እንደሚናገሩት ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ አባወራዎች በቅርብ ወደ ምትገኝ መንደር እንዲዘዋወሩ ተደርገው መሬትና ካሳ ተሰጣቸው።

የሳሉሊም የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ ፕሮጀክት በከፍተኛ ሁኔታ የተለጠጠ ነበር። መሰረቱንም በሳሉሊም ወንዝ ላይ አድርጎ ለመጠጥ የሚሆን ውሃን፣ መስኖንና አንዳንድ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችንም አጠቃሎ የያዘ ነበር። ለነዋሪዎቹም 400 ሚሊዮን ሊትር የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንም አቅዶ ነበር።
"ወደ አዲሷ መኖሪያችን ስንመጣ ምንም ነገር አልነበረንም" በማለት ከሶስት አስርት አመታት በፊት ወደ ሌላ መንደር ከተዛወሩት ቀደምት ከሆኑት አንደኛው ኢናሲዮ ሮድሪገስ ይናገራሉ። ቤታቸውንም እስከሚገነቡ ድረስ በጊዜያዊ መጠለያ የቆዩ ሲሆን ለአንዳንዶቹም አምስት አመታትን ያህል ፈጅቶባቸዋል።

ከአካባቢው ተነሱ ሲባል ጉራቻራን ኩርዲካር የአስር አመት ልጅ ነበር።
"ቤተሰቦቼ በጭነት መኪና እቃቸውን ጠቅልለው እንዲሁም እኔ፣ ወንድሜና አያቴም ተጭነን ስንሄድ ትንሽ፣ ትንሽ አስታውሳለሁ። ቤተሰቦቼም እያለቀሱ ነበር" በማለት በአሁኑ ሰአት የ42 አመት የሆነው ጉራቻራ ይናገራል።

እናቱ ማምታ ኩርዲካር እለቱን ትናንት የተፈጠረ ያህል በደንብ ታስታውሰዋለች። " የዛን እለት በፊት ምሽት በከፍተኛ ሁኔታ ዘንቦ ቤታችን አረስርሶት ነበር። በፍጥነት ከቤታችንም ወጥተን መሄድ ስለነበረብን፤ የዱቄት መፍጫየን አልወሰድኩም" በማለት ታስታውሳለች።

ነገር ግን ቃል እንደተገባላቸው የግድቡ ውሃ ለመንደሪቷ ነዋሪዎች አልደረሳቸውም።
ኩርዲካር በሚኖርበት አካባቢ ትልልቅ የውሃ ጉድጓዶች የሚገኙ ሲሆን በሚያዝያና ግንቦት ላይ ግን ይደርቃሉ። በዚህም ወቅት መንግሥት የሚለግሳቸውን የውሃ ታንከሮች መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።

አሁንም ቢሆን የጥንት መንደራቸው ትዝታ ሊለቃቸው ስላልቻለ ውሃው ሲሸሽ ተሰባስበው ወደ መንደሯ ይመጣሉ።
በጎዋ የሚኖር የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪው ቬኒሻ ፈርናንዴዝ ስለዚህ ቁርኝት የሚለው አለ " ለኩርዲ ነዋሪዎች ማንነታቸው ከመሬቱ ጋር በፅኑ የተሳሰረ ነው። ለዛም ነው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስታውሱት፤ ቦታው በውሃ ቢሸፈንም ይመላለሳሉ"

No comments:

Post a Comment

wanted officials