Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, June 26, 2019

ጋዜጠኛና የመብት ታጋይ እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት እየታሰሩ እንደሆነ ተናገረ BBC


"ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም" እስክንድር ነጋ

እስክንድር ነጋ
ቅዳሜ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት እየታሰሩ እንደሆነ ጋዜጠኛና የመብት ታጋይ እስክንድር ነጋ ገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ ከእስክንድር ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፦ የባልደራስ አባላት ታስረዋል የሚባል መረጃ አለ ምን ያህል እውነት ነው?
እስክንድር፦የባላደራው ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆነው ስንታየሁ ቸኮል ጀምሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ የአመራር አባል የሆኑት ኃይሉ ማሞና መርከቡ ኃይሉ የተለያዩ የአመራር አባላት ታስረዋል፤ እስሩም ቀጥሏል። እኔም ጉዳያቸውን ለማጣራት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄጄ ሞክሬያለሁ ነገር ግን በወቅታዊ ጉዳዮች ታስረዋል ከሚል ውጭ ምንም አይነት መረጃ የሚሰጠኝ ሰው አላገኘሁም። የታሰሩት እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ነው።
ቢቢሲ፦ እስክንድር ታስሯል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነበር። የባህርዳር ቆይታህን ልትነግረን ትችላለህ  ?

እስክንድር፦ እሁድ እለት ህዝባዊ ስብሰባ ስለነበረን ወደ ባህርዳር የሄድኩት ቅዳሜ 11 ሰዓት ነበር፤ የአምሳ ደቂቃ በረራ ነው፤ አየር ላይ በነበርኩበት ሰዓት ነው ሰዓት ነው ይሄ የተከሰተው። አውሮፕላኑ ሲያርፍ ይሄ ነገር ተከስቶ ነው የጠበቀኝ፤ ወደ ውጭ መውጣትም ስላልቻልኩኝ "ለደህንነትህ" ብለው እዛው አየር ማረፊያ ነው ያደርኩት።እዚያው ያደርነውም የአዲስ አበባ ባልደራስ ምክር ቤት አባላት ብቻ ነን። እሁድ ግን ማን እንደከለከለ ባናውቅም ተመልሰን ወደ አዲስ አበባ እንዳንሄድ ተከልክለናል። እንዲያውም መመለስ ትችላለችሁ ተብለን ተጨማሪ ገንዘብ ከፍለን ትኬት ገዝተናል። ነገር ግን ሁሉን ነገር ጨርስን አውሮፕላን ልንገባ ስንል አትሄዱም ተብለን ተጠርተን ተመልሰናል።
ከዚያ በኋላ ወደ ባህርዳር ገብተን 30 ደቂቃም ሳንቆይ ተለያይተን እኔና ስንታየሁ በመኪና ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል። እኛ ከተመለስን በኋላ ግን ሌሎች ሶስት አባላት በአየር እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸው በአየር ተመልሰዋል።
22 ሰዓት መንገድ ላይ ቆይተን ነው አዲስ አበባ የገባነው።

ቢቢሲ፦ ባህርዳር አየር ማረፊያ በነበራችሁበት ወቅት አዲስ አበባና ባህር ዳር ስለሆነው ነገር መረጃ ታገኙ ነበር?
እስክንድር፦ አዎ ቴሌቪዥን ስለነበር ተከታትለናል።
ቢቢሲ፦ ጀኔራል አሳምነው ጋር አውርታችኋል ወይ ስለስብሰባው ጉዳይ?
እስክንድር፦ አላወራንም። እኔ እኮ ተጋባዥ ነኝ። አዘጋጅ ስላልሆንኩ ስለስብሰባው የማስፈቅደው ነገር የለንም። እኔንም ከእሳቸው ጋር ሊያገናኘን የሚችል ቅንጣት ነገር የለም። እዚያ ላይ የተፈጠረው ነገር ፓርቲው ላይ የተፈጠረ ነው። ይህን አሳቦ እኛን ማሳደድ ግን ተገቢም አይደለም፤ ፍትሃዊም አይደለም።
ቢቢሲ፦ መንግስት አጋጣሚውን በመጠቀም እኛን እያጠቃ ነው ብለህ ታምናለህ?
እስክንድር፦በግልጽ እየታየ ነው እኮ። እኛ ከዚህ ጉዳይ ጋር የምንገናኝበት ቅንጣት ታክል ግንኙነት የለም። አጠቃላይ ፓርቲው ጋር የተፈጠረ ነው። እኛ እንኳን አሁን እና ድሮም በጨለማው ዘመን በሰላማዊ መንገድ ነው ስንታገል የነበረው። አሁንም ተልዕኮ የሰጠን ህዝብ በዚሁ እንድንቀጥል ነው የሚፈቅድልን። ለተፈጠረው ችግር የፓርቲው ሰዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው። እነሱን ማዳመጥ ነው። የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ጉዳዩን በዝርዘር ለህዝብ አቅርበዋል፤ እነሱን መከታተል ብቻ ተጨማሪ መረጃ ሳያስፈልግ ጉዳዩን መረዳት ይቻላል።
ቢቢሲ፦እስክንድር በግልህ አደጋ ይደርስብኛል ብለህ ትሰጋለህ? በመንግስት በኩልስ ጥበቃ ይደረግልሃል ወይ?
እስክንድር፦በመንግስት በኩል ጥበቃ አይደረግልኝም፤ አልፈልግምም። ጥበቃ የሚያስፈልገኝ ሰውም አይደለሁም። እኔ ሙሉ ለሙሉ ጠባቂዬ እግዚአብሔር ነው ብየ ስለማምን። በተለያየ አጋጣሚ ስጋቶች አሉብኝ በተለይ መንገድ በምንወጣበት ወቅት በጣም ከባድ አደጋዎች ናቸው የሚገጥሙን። ነገር ግን በጸጋ ነው የምቀበለው። በማህበራዊ ሚዲያዎች በቪዲዮ ጭምር የሚሆነውን ታያለህ በሌሎች አጋጣሚዎችም ከፍተኛ የሆነ ስጋት አለኝ። በርግጥ ልጅና ሚስት አለኝ፤ ለቤተሰቤ ብየ ለህይዎቴ ዋጋ እሰጣለሁ፤ ከዚያ ባለፈ ግን ጥበቃ አያስፈልገኝም።
ቢቢሲ፦ምናልባት እንቅስቃሴህን መገደብ እንዳለብህ ይሰማሃል?
እስክንድር፦ ምን አጠፋንና ነው ረገብ ማለት የሚያስፈልገን? ወደ ሃይል እርምጃ አልገባን? ወይም ሰላም የሚያደፈርስ ነገር አልሰራን? አቋም መወሰድ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ግን አቋም እንወስዳለን። ከእውነት ጋር እንሞግታለን። ከዚህ በፊትም እኮ ከእውነት ጋር ወግነን ነው ዋጋ የከፈልነው። አሁንም ከእውነት ጋር መወገን ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነ ዋጋ እንከፍላለን። ቀይ መስመር አለ፤ እሱን አናልፍም። እንኳን የሃይል ርምጃ ልንወስድ ጠጠር እንኳ አንወረውርም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials