Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, June 26, 2019

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አስክሬን ላሊበላ ገባ



የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን አስክሬን ላሊበላ አየር ማረፊያ እንደደረሰ በሥፍራው የሚገኙት የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለቢቢሲ ገለፁ።

ትናንት የብ/ጄነራል አሳምነው መገደል ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቻቸው አስክሬናቸው በክብር እንዲሰጣቸው ለወረዳው ጥያቄ በማቅረባቸው መንግሥት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ አስክሬናቸውን እንደሸኘ አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።
ዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ የብ/ጀኔራሉ አስክሬን ከባህር ዳር ወደ ትውልድ ቀያቸው እንደሚላክ በስልክ እንደተነገራቸው የገለፁት ምክትል ከንቲባው አስክሬናቸውን በክብር ለመቀበል በአየር ማረፊያ እንደተገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጄነራሉ ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የአካባቢው የመንግሥት አመራር አካላት፣ የፀጥታ ኃይሎችና የቤተክርስቲያን ቀሳውስት በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተዋል።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር ገና ስላልተነጋገሩ የብ/ጄነራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት የትና መቼ እንደሚፈፀም በእርግጠኝነት መግለፅ እንደማይችሉ የገለፁልን ምክትል ከንቲባው፤ ሕብረተሰቡ ኃዘኑን የሚገልፅበት በከተማ አደባባይ ትልቅ ድንኳን የተዘጋጀ መሆኑንና አስክሬናቸውም በዚሁ ድንኳን ውስጥ እንደሚያርፍ አስረድተዋል።
በዚያው ሥፍራ ሌሊቱን የፀሎተ ፍትሃት ሥነ ሥርዓት እየተደረገ እንደሚያድር መረጃ እንዳላቸው ገልፀውልናል።
ምክትል ከንቲባው ብ/ጄነራል አሳምነው ለአገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በደማቅ ሁኔታ ለመፈፀም ኮሚቴ መዋቀሩን አክለዋል።
በዚህም መሠረት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በዲስፕሊንና በፕሮቶኮል ለመምራት የክብር ተመላሽ ጄነራሎች በአካባቢው ላይ በመኖራቸው በእነርሱ ይመራል ብለዋል።
በሌላ በኩልም የፀጥታ ሂደቱን የሚመራ ቡድን፣ የወጣቱ ሰላምና ደህንነት የሚከታተል ሌላ በወጣቶች የሚመራ ቡድን እንዲሁም የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቱን የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሯል።
ጄኔራል አሳምነው ፅጌ
አቶ ማንደፍሮ እንደገለፁልን ትናንት ብ/ጄነራሉ መገደላቸውን ከተሰማ አንስቶ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተዘበራራቀ ስሜት እንደሚታይ እንዲሁም በክልሉ አመራሮች ሞት ምክንያት ድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።
የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት አመራርና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጎን በመሆን ቤተሰባቸውን በማፅናናትና ህዝቡንም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዳሜ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ባህር ዳር ውስጥ ተሞክሯል የተባለውን "መፈንቅለ መንግሥት" መርተዋል ተብለው ሰማቸው የተጠቀሰው የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋድየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ መገደላቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials