Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 10, 2019

አምስት ጂ ኢንተርኔት ምን አዲስ ነገር አለው? 5 G Internet and HUWAEI campany

ሁዋዌ


በኢትዮጵያ 3ጂ ኢንተርኔት ትግል ሲሆን ሌሎች ሃገራት ደግሞ ፈር ቀዳጅ ያሏቸውን የቴክኖሎጂ ውጤታቸውን እያስተዋወቁ ነው፤ እንግሊዝም ከሰሞኑ አምስት ጂ ኔትወርኳን አስተዋውቃለች።
ደንበኞች ለረጅም ጊዜ ከመጓጓታቸው አንፃር ብዙዎች የተደሰቱበት ቢሆንም ግራ መጋባቱ እንዳለም ተገልጿል።
በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ቴክኖሎጂው አዲስነት ዋጋው ብዙ የሚቀመስ አልሆነም፤ ኔትወርኩ በሁሉም አይነት ተንቀሳቃሽ ስልክ ስለማይሰራ ለዚህ ቴክኖሎጂ የሚሆን ስልክ ለመግዛት በአንድ ጊዜ የሚከፈል 7650 ብር ከዚያም በየወሩ 2430 ብር መክፈል ደንበኞች ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ክፍያ ግን በየወሩ 10 ጊጋ ባይት ዳታ ብቻ የሚጠቀሙ ከሆነ ነው እንጂ እንዲያው ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እጭናለሁ ካሉ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ ያስፈልጋል።
የአምስት ጂ ኔትወርክን በመጀመር ፈር ቀዳጅ የሆነው የእንግሊዙ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ቢቲ አካል የሆነው የተንቀሳቃሽ ስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪው ኢኢ የተባለው ድርጅት ነው።
ቮዳፎን የተሰኘው ድርጅትም በቅርቡ የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል። ነገር ግን ብዙዎች አገልግሎቱን ለመጠቀም አልተቻኮሉም፤ መጠበቅን መርጠዋል።

የተንቀሳቃሽ ስልኮችን የውስጥ ቁስ አምራች የሆነው ኳልኮም የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎት የሚሰጡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የባትሪ ቆይታቸው ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚሆን ቃል ገብቷል።

ምን ያህል ፈጣን ነው?
የእንግሊዝ ኮሚዩኒኬሽን ተቆጣጣሪው ድርጅት ኦፍ ኮም እንደሚለው የአምስት ጂ ኔትወርክ ፍጥነት በሰከንድ 20 ጊጋ ባይት እንደሚሆን ነው።
የአንድ ፊልም ጭብጡን እስኪያነቡ በሚወስደው ጊዜ ከፍተኛ ጥራት ያለውን ፊልሙን ዳውንሎድ አድርገው መጨረስ ይችላሉ እንደ ማለት ነው።

ነገር ግን ለአሁኑ ደንበኞች ብዙ እንዳይጠብቁ ድርጅቱ ያስጠነቅቃል፤ ምክንያቱም አገልግሎቱን የሚሰጠው ኢኢ የአምስት ጂ ኔትወርክ ለመዘርጋት የሚጠቀመው መስመር በሰከንድ ያለው ፍጥነት አስር ጊጋ ባይት ብቻ ሲሆን ይህ ለአንድ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎችም የሚጋራ ይሆናል።
በዚህም መሰረት በአማካኝ አንድ ደንበኛ የሚያገኘው የፍጥነት መጠን በሰከንድ 150-200 ሜጋ ባይት ሊሆን እንደሚችልና፤ ብዙ ሰው በማይጠቀምበት ወቅት ለአንዳንድ እድለኞች እስከ አንድ ጊጋ ባይት ሊደርስ ይችል ተብሏል።
ፈጣን ኢንተርኔት ብቻ ይሆን?
ምንም እንኳን ደንበኞችን ለመሳብ ለጊዜው የአምስት ጂ ኔትወርክ እየተዋወቀ ያለው ከፈጣን ኢንተርኔት ጋር በተያያዘ መልኩ ቢሆንም ለዘላቂው ግን አምስት ጂ ኔትወርክ ያላቸው ስልኮች በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ስልኮች በላይ መገናኘት የሚያስችል ኔትወርክ ተዘርግቶላቸዋል።
ነገር ግን ይህንን ሁሉ ለማከናወን ከአውቶብስ ማረፊያ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች አዳዲስ አንቴናዎች መትከል ያስፈልጋል ተብሏል።

ከግለሰቦች በተጨማሪ የደንበኞችን መረጃ በመሰብሰብ ለንግድም ሆነ እንዲሁም ለደህንነት ሥራ ለሚጠቀሙበት ለመንግሥትም ሆነ ለተለያዩ ድርጅቶችም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ደንበኞች በሚፈልጉት መጠን ኔትወርክ የሚያከፋፍል ሲሆን ለምሳሌ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ደንበኞችም ዩቲዩብና ሌሎች ዳታን የሚጨርሱ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ምንም እንዳይደናቀፉ ይደረጋል። ይህ ከጥቂት ዓመታትም በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

የሁዋዌስ ነገር እንዴት ነው?

ከደህንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የቻይናው ኩባንያ ሁዋዌ የአምስት ጂ ኔትወርክ እቅዱ እገዳ ይገጥመዋል ተብሏል።
ባለፈው ወር ኩባንያው ለአምስት ጂ ኔትወርኩ አንቴናና ሌሎችም ቁሶች ፍቃድ ሊሰጠው የሚመስሉ ፍንጮች ቢታዩም የጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን መልቀቅ ተከትሎ የማይሆን ነው ተብሏል።
የኩባንያውን መሰረተ ልማት ማገዱ ለአገልግሎት ሰጪዎቹ ራስ ምታት እንደሚሆን እየተነገረ ነው። ኢኢና ቮዳፎን ይጠቀሙባቸው የነበሩ የሁዋዌ የውስጥ አካላትን እንዳይጠቀሙ ከተገደዱ ሥራቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያከብደ እየተነገረ ነው።

ሁለቱም ድርጅቶች እንደገለፁት የሁዋዌ መገለገያዎችን የውስጥ ክፍሎች መሀንዲሶቻቸው ለመተካት ከተገደዱ የአምስት ጂ ኔትወርክ አገልግሎታቸውን ሊያዘገየው እንደሚችል ነው።
የአገሪቱ ስልክ አምራቾችም ሆነ ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሁዋዌ ጋር በመነካካታቸው ብዙ ነገሮች ሊወሳሰቡ ይችላሉ እየተባለ ነው።
ምንም እንኳን አምስት ጂ ኢንተርኔትን ለመጀመር ከአውሮፓ ሃገራት እንግሊዝ ፈር ቀዳጅ ብትሆንም ከሁዋዌ ጋር በተያያዘ ለመላው አገሪቷ ሽፋን ለመስጠት እንቅፋት እንደሚሆንና ሌሎቹም ሊቀድሟት ይችላሉ እየተባለ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials