Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, February 25, 2018

ለ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን



ብርሃን ፈይሳ
የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር ቀናት ብቻ የሚቀሩት ሲሆን፤ ሀገራትም ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ። በተለያዩ ርቀቶች ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ እየተመራ በርኒንግሃም ላይ እንደሚገኝ፤ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አስታውቋል።
17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በእንግሊዟ በርኒንግሃም የዛሬ ሳምንት የሚጀመር ይሆናል። ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ ሻምፒዮና ላይም በተለያዩ ርቀቶች በስፖርቱ የታወቁ አትሌቶች ለአሸናፊነት ይፋለማሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በሻምፒ ዮናው የሚሳተፉትን አትሌቶች ከሳምንት በፊት አስታውቋል። በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ በሁለቱም ጾታ በሦስት ርቀቶች ላይ ተሳታፊ ይሆናል።
በቤት ውስጥ ሻምፒዮና ስኬታማነቷን ያስመሰከረችው የመካከለኛ ርቀት አትሌቷ ገንዘቤ ዲባባ በሁለት ርቀቶች ትካፈላለች። የ27 ዓመቷ ገንዘቤ በዚህ ውድድር ያላትን ብቃት ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየችው እ.አ.አ 2012 በኢስ ታንቡል ሲሆን፤ በተካፈለችበት 1ሺ500ሜትር አሸናፊ በመሆንም ነበር ያጠናቀቀችው። እ.አ.አ 2014 በሶፖት እንዲሁም በ2016ቱ የፖርትላንድ ሻምፒዮና ደግሞ በ3ሺ ሜትር ውድድር የበላይነቱን መያዝ ችላለች። በዘንድሮው ሻምፒዮና ደግሞ ስኬታማ በሆነችባቸው በሁለቱም ርቀቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን እንደምትሮጥ ታውቋል።
በ800 ሜትር እ.አ.አ የ2013 የዓለም ሻምፒዮናው መሃመድ አማን በወንዶች እንዲሁም አትሌት ሀብታም አለሙ በሴቶች ምድብ ሀገራቸውን የሚወክሉ ይሆናል። በወንዶች 1ሺ500 ሜትር ውድድር ሳሙኤል ተፈራ እና አማን ወጤ፤ በሴቶች በኩል ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ስዩም እና ጉዳፍ ጸጋዬ በውድድሩ ላይ ተካፋይ የሚሆኑ አትሌቶች ናቸው። ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ሃጎስ ገብረህይወት እና ዮሚፍ ቀጄልቻ በወንዶች በ3ሺ ሜትር የሚሳተፉ ሲሆን፤ ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ስዩም እና ፋንቱ ወርቁ በሴቶች ምድብ ለአሸናፊነት የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials