ኦህዴድ “ሶስቱን ከፍተኛ ስልጣኖች አላመነባቸውም”በረከት ስምዖን ደመቀ መኮንን ጠ/ሚ እንደሚሆኑ አመላከቱ፣ ዶክተር አብይን አናናቁ፤ ኦህዴድ መልስ ይሰጣል?
በኩርፊያ ” በቃኝ” ብለው የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ወደ ስራ ከተመለሱ በሁዋላ በአንዳንድ ጉዳዮች ድምጻቸው ቢሰማም የብአዴንን ግምገማ ከመሩና ያለ አንዳች ለውጥ እንዲጠናቀቅ ካደረጉ በሁዋላ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ በሚል ስማቸው በሚነሳው ዶክተር አብይን ክፉኛ አጣጣሉ። ኦህዴድ ገምግሞ ላባረራቸው ሙክታር ጥብቅና በመቆም አቶ ደመቀን የማንገስ ፍላጎት መኖሩን አመላከቱ።
ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር የቀድሞውን የኢትዮጵያ ወታደራዊ መዋቅርና ማሰልተኛ ተቋሞች ከነሙሉ ባለሙያዎቻቸው አፍርሶ እንደነበር በዘነጋ መልኩ ዶክተር አብይን ብሄር ለማመጣጠን ሲባል ወደ ውትድርና የገቡ፣ “ሃምሳ አለቃ የሪዲዮ ኦፕሬተር ነበር” ሲሉ አቶ በረከት ገልጸዋል። “በአጋጣሚ” ሲሉ የመቶ አለቃነት ሹመት እንደነበረው እንደሚያውቁም ገልጸዋል።
አቶ በረከት አክለውም “ከመቶ አለቃ ወደ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ መድረሱ ያጠራጥረኛል። የሌተናል ኮሎኔል ማእረግ ከተሰጠውም ሊሆን የሚችለው የብሄር ተዋጽኦ ማመጣጠን በሚባለው አካሄድ ነው። የብሄር ተዋጽኦ የማመጣጠን አሰራራችን ህገመንግስታዊና ትክክለኛ ቢሆንም በዚህ አካሄድ ፈጣን እድገት ያገኙ አባላት አላማውን በመገንዘብ ሰራዊቱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ይገለገሉበታል እንጂ ከሰራዊቱ ከወጡ በኋላ ለማስታወቂያ ፍጆታ አያውሉትም ” ሲሉ የሌሎች ብሄር ወታደራዊ መኮንኖች በብሄር ማመጣጠን ስም በጅምላ ያለብቃት የተሾሙ እንደሆኑ አድርገው ተዋንያን መሆናቸውን በመርሳት እንደ ታዛቢ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ሌሎች ጡረታ ከወጡ በሁዋላም ቢሆን በወታደራዊ ማዕረጋቸው ሲጠሩ ተቃውሞ ያላሰሙት አቶ በረከት ዶክተር አብይ በማዕረግ ዶክተር ሆነው ሳለ በማይጠሩበት የወትድርና ማዕረግ እንደ ነገዱ አድርገው ስለዋቸዋል።
በዚህ ብቻ አላበቁም በመላው የአማራ ህዝብ ፍጹም የማይወደዱና ” ካሃጂ” በሚል ስያሜ የሚጠሩትን አቶ ደመቀን ” ጽኑ” ሲሉ ከሌሎች የተሻሉ አድርገው ስለዋቸዋል። በራሱ በብአዴን አባላትና አመራሮች የተተፉትን አቶ ደመቀን ወደ አመራር ለማምጣት እቅድ መኖሩን ያሳበቁት አቶ በረከት፣ የኢንሳ መስራች ” ጓድ መለስ ነው” ሲሉ አክለዋል። የአገላለጽ ስህተት ካልሆነ በስተቀር ዶክተር አብይ ኢንሳ ሲመሰረት ጀምሮ በማዋቀር፣ በማደራጀት፣ በመምራት አቶ በረከት የሚምሉባቸው መለስ ራሳቸው ለዶክተር አብይ እውቅናና ክብር ይሰጡዋቸው እንደነበር ሰፊ ምስክሮች አሉ።
“ተላላኪ” በሚል የሚታወቁትን አቶ ደመቀን ወደ አመራር ለማምጣት ተብሎ ሳይሆን፣ ዶክተር አብይ በእርግጥም የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃና ማእረግ አቅርበው ከሆነ ሊጣራና ወንጀል ሆኖ ከተገኘ ሊያስጠይቃቸው የሚገባ ጉዳይ እንደሚሆን ብዙዎች ያምናሉ። የህግም ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛው የኢህአዴግ ባለስልጣኖች “የዲግሪና የዲፕሎማ ወፍጮ ቤቶች” የተመረቁ ስለመሆናቸው በተለያዩ ወቅቶች የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይህ በንዲህ እንዳለ ኦህዴድ ለምን የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ ለመያዝ ፈለገ? ለሚለው ስሙን መጠቀስ ያልፈለገ በትምህርት ውጪ አገር የሚገኝ የኦህዴድ አባል ለዛጎል ይህንን ብሏል። “ፐሬዚዳንቱ ከኦህዴድ ናቸው ግን አቅም አልባ ቦታ በመሆን ለኦሮሞ ህዝብ አይመጥንም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን የያዘው ኦህዴድ ቢሆንም በቦታው ያሉት ሰው በኦሮሞነታቸው ጉዳይ ጥያቄ ስላለባቸው ህዝብ ቦታው ለኦሮሞ እንደተሰጠ አይቆጥረውም፣ አፈ ጉባኤው ከኦህዴድ ቢሆኑም እሳቸውም በተመሳሳይ የሚጠቀሙበት ሃላፊነት ስለሌላቸው የኦሮሞ ህዝብ ከብዛቱ፣ ከቆዳ ስፋቱ፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሃብት ስርጭትና አስተዋጾ አንጻር የሚታይ ነው”
በሌላ በኩል ዶከተር አብይም ሆኑ ኦህዴድ አቶ በረከት ላቀረቡት አላማ ያለው የማጣጣል ዘመቻ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪው ተናገረዋል። አያይዘውም ስልጣንን የግል ዝና መገንቢያ የማድረግ ዝንባሌ በድርጅታቸው እንደሌለ አድርገው አቶ በረከት ያቀረቡትን ” ሰው ከሞተም በሁዋላ እስኪመለክ ድረስ ዝና ሲገነቡ የነበሩት እነሱ ናቸው፤ አሁን ድረስ የሞተ ሰው ዝና ለማገናብት ከቆሙት በላይ በጀት እየተመደበ መሆኑ የዚህ ማሳያ ነው ” ብለዋል። የአቶ በረከት ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል። አንዳንዶች ጽሁፉ የአቶ በረከት አይደልም ቢሉም እሳቸው ግን አላስተባበሉም
ከኣቶ በረከት ስምኦን
“ሰላም የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች።
ልባዊ ሰላምታዬን ባላችሁበት አቀርባለሁ።
የውስጥ ድክመቶቻችን ያስከተሉት የህዝብ ቅሬታና ክፍተት እንዲሁም አጋጣሚውን የተጠቀሙበት ሀይሎች አፍራሽ ሚና ተዳምሮ አሳሳቢ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ድርጅታችን ጥልቅ ተከታታይና ዙሪያ መለስ የተሀድሶ ስራዎችን እያካሄደ እንደሆነ ይታወቃል። የዚህ አካል የሆነው የብአዴን ጥልቅ ግምገማ መጠናቀቁንና የአቋም መግለጫውን ከሚዲያ ሰምታችኋል።
የተሀድሶ ሂደታችንን በሰፊው ህዝብ ዘንድ ለማስረጽ በተለይም ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይን እና የህዝበኝነት ዝንባሌዎችን የሚተነትኑ ጽሑፎች በአዲስ ራዕይ መጽሔት በኩል በማውጣት ህዝቡ እንዲወያይበት አድርገናል።
በነዚህ ሁለት ቁልፍ ችግሮች ዙሪያ በቀጣይም በሚመለከታቸው የኢህአዴግ መዋቅሮች አማካኝነት ሰፋፊና ጥልቅ ውይይቶችን የሚደረጉ ይሆናል።
ይሁን እንጂ የድርጅታችን ሊቀመንበር የስራ መልቀቂያ ማስገባት እና የአመራሮች በተለያዩ ስራዎች መጠመድን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለስልጣን ባለ የተዛባ አተያይ የተመሰረተ አደገኛና ትርምስ የሚጋብዝ ህዝበኛ አካሄድ እየታየ በመሆኑ የተወሰኑ ነጥቦችን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ታይቶኛል።
በድርጅታችን ባህል ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እና የማህበረሰብ ለውጥ ማምጫ የልማት መሳሪያ እንጂ የግለሰብ ዝና (personality cult የሚባለው) የሚገነባበት አይደለም። ከሊቀመንበር ጀምሮ በየትኛውም ቦታ ላይ የሚደረግ ምደባ የግለሰቡን ጽናት ልምድ የግምገማ ውጤት የመሳሰሉትን ነገሮች መሰረት ያደረገ ብቻና ብቻ ነው። እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟላው እጩ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ጓድ ደመቀ መኮንን ቢሆንም ሌሎች የተሻሉ ካሉ በአመራር ስብሰባ ላይ ቀርቦ የምንነጋገርበት እንጂ እንደኒዎ ሊበራል ድርጅቶች በየሶሻል ሚዲያው ቅስቀሳ የሚደረግበት አሰራር የለም።
በክልል ቴሌቪዥን የአንድን እህት ድርጅት የአመራር አባል ማስታወቂያ የሚሰራበት እና ህዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚደረግበት አካሄድም ከድርጅታችን ባህል ያፈነገጠ ነው። በተለይ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ አንዱ ምክንያት የሆነው ዛሬ በኦሮሚያ ቴሌቪዥን በአማርኛ የቀረበው ዶኩመንታሪ ከአብዮታዊ ባህል ያፈነገጠ የድርጅትን ስልጣን በህዝበኝነት ለመቆጣጠር የተደረገ እና ህዝቡን ለተሳሳተ ግንዛቤ ብሎም ግርግር ሊሚመራ የሚችል ነው።
ዶኩመንታሪውን አስደንጋጭ የሚያደርገው ከድርጅታችን ባህል ማፈንገጡ ብቻ ሳይሆን ከእውነት የራቁ መረጃዎችን የያዘ መሆኑን ነው።
የደርግ ስርአትን በሚገረሰስበት ወቅት በየቦታው የኦህዴድን መዋቅር ስናደራጅ ጓድ አብይ አህመድ ድርጅቱን እንዲቀላቀል እንዳደረግን እና በክፍለ ህዝብ ክንፍ ተመድቦ የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የቅስቀሳና ማደራጀት ስራዎችን እንዲያግዝ ማድረጋችን ትዝ ይለኛል። በ1987 የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ጸድቆ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲደራጅ የሰራዊቱን ተዋጽኦ ለማመጣጠን ወደ ሰራዊቱ እንዲገቡ ከተደረጉ የድርጅት አባላት አንዱ ነበር። ሻዕቢያ በወረረን ወቅት በሀምሳ አለቃ ማዕረግ በራዲዮ ኦፕሬተርነት ይሰራ እንደነበር የሰራዊቱን ዝግጅት ለመጎብኘት በሄድኩበት ወቅት ተረድቻለሁ።
በ1997ቱ ምርጫ ማግስት ከሰራዊቱ ጋር በነበሩ ስራዎች አጋጣሚ አግኝቸው መቶ አለቃ ደርሶ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዛ በኋላ ሰራዊቱ ውስጥ በቆየባቸው ጥቂት አመታት ከመቶ አለቃ ወደ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ መድረሱ ያጠራጥረኛል። የሌተናል ኮሎኔል ማእረግ ከተሰጠውም ሊሆን የሚችለው የብሄር ተዋጽኦ ማመጣጠን በሚባለው አካሄድ ነው። የብሄር ተዋጽኦ የማመጣጠን አሰራራችን ህገመንግስታዊና ትክክለኛ ቢሆንም በዚህ አካሄድ ፈጣን እድገት ያገኙ አባላት አላማውን በመገንዘብ ሰራዊቱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ይገለገሉበታል እንጂ ከሰራዊቱ ከወጡ በኋላ ለማስታወቂያ ፍጆታ አያውሉትም።
ለስልጣን ያለንን የተዛባ አተያይ የሚያመለክቱ በርካታ ግነቶች በዶክመንታሪው ላይ መታየታቸው የድርጅታችንን ጤንነት ቆም ብለን መመርመር ማየት እንዳለብን የሚጠቁም ነው። የኢንሳ መስራች ነው ተብሎ የቀረበው ግራ የሚያጋባ ነው። ይህን ዘመናዊ ሀሳብ ያፈለቀው ጓድ መለስ ዜናዊ ነው። ሲከተል ደግሞ ኢንሳ መስራች አለው ከተባለ መስራቹ መንግስት ነው። በመሰረቱ ኢንሳ ቀድሞ ሲግናል ሬጅመንት ሲባል ከነበረው አሀድ ያደገ ተቋም ነው። እዚያ የነበሩ ዋነኛ ሞተሮች ደግሞ የብአዴን ፍሬዎች የሆኑት እነ አህመድ ሀምዛ እነ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። ለጓድ አብይ የኢንሳ ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመበት አጋጣሚ የነበረ አይመስለኝም። የመስሪያ ቤቱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመሆኑ ጓድ መለስ የዳይሬክተር ለውጥ ሹመት ሰጥተው ቢሆን ያሳውቁን ነበር።
ከግል ህይወት ታሪክ ወይም ሲቪ ጋር በተያያዘ ጓድ ሃይለማሪያም በሰጡት መመሪያ መሰረት የአመራሮችን የትምህርት ማስረጃዎች ማሰባሰብና ማደራጀት ሲካሄድ ጓድ አብይ በውጭ ሀገር የማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝቻለሁ በሚለው መረጃው ምክንያት ከጓድ ሙክታር ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር አስታውሳለሁ። የሰነድ አደራጅ ኮሚቴ የተጠቀሰውን ዩኒቨርሲቲ ሆነ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ አለመቻሉን ለማዕከል ሪፖርት ሲያደርግ ጓድ ሙክታር ስልጣኑን ተጠቅሞ ባለማስቆሙ ከጓድ አብይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደቀረበ ይታወሳል። ይህም ለስልጣን ያለ የተዛባ አተያይን የሚያመለክት መሆኑ ተግልጾለት ሂሱን የዋጠ ሲሆን አጠቃላይ ጉዳዩ በእናት ድርጅት ተገምግሞ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቶ ነበር። ዛሬ ዶኩመንታሪው ላይ ተደግሞ ሳየው የስንት አመታት ግምገማና ውይይት ምን ወንዝ ወሰደው የሚያስብል ነበር።
የግለሰቦች ጉዳይ በተገቢው የድርጅት መድረክ ይታያል። እነዚህን መረጃዎች እዚህ ለማቅረብ ያስገደደው ምክንያት ህዝብ የተሳሳተ ግንዛቤ ተፈጥሮበት ወደውዥንብርና ግርግር እንዳይገባ ከወዲሁ እርማት መስጠት ግዜ የማይሰጥ ድርጅትንና ሀገርን የማዳን ተግባር በመሆኑ ነው። አመራሮች በተለያዩ ስራዎች በመያዛቸው የተለመደውን መዋቅር ሳልጠብቅ የድርጅታችንን አባላትና ደጋፊዎች በቀጥታ እና በፍጥነት ማስገንዘብ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
መላው የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች በየአቅጣጫው በሚታዩ ነገሮች ሳይደናገሩ የኢህአዴግና የብአዴን አመራሮች ስልጣንን የለውጥ መሳሪያ እንጂ የግል ጥቅም ማራመጃ አድርገው እንደማያዩት እምነት ሊያሳድሩ ይገባል። አንዳንድ በየቦታው የሚታዩ ጤናማ ያልሆኑ ዝንባሌዎችም በዙሪያ መለስ ግምገማ የሚስተካከሉ ናቸው። በአመራር ረገድ የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም። ጓድ ኃይለማርያም በስራ ላይ ናቸው። እሳቸው ፈጥነው መልቀቅ ቢያስፈልጋቸው እንኳን የኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ እስከሚያደርግ ድረስ በህገ-መንግስቱ መሰረት ምክትላቸው ስራውን እየሸፈኑ ይቆያሉ።
ከህዝባችን ጋር ሆነን የማንፈታው ችግር የለም!
የህዳሴ ጉዟችን ይሳካል!”
No comments:
Post a Comment