Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, February 27, 2018

የፖለቲካ እስረኛው ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ በእስር ቤት እንዳለ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።


(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2010)
የፖለቲካ እስረኛው ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ በእስር ቤት እንዳለ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።
በሽብር ወንጀል ተከሶ የአራት አመት እስር ፍርደኛ የነበረው ገበየሁ ፈንታሁን እስርቤት ውስጥ በሕመም ምክንያት መሞቱ ታውቋል።
እስረኛው ገበየሁ ፈንታሁን ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሮ እንደነበርና በቆይታውም ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበር ከሐገር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክሳቸው ተቋርጦ ሊፈቱ ነው የተባሉት የዋልድባ መነኮሳት ምስክር ሊሰማባቸው በፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱ ተሰምቷል።
ገበየሁ ፈንታሁን የአንድ ልጅ አባትና ባለትዳር ነበር።ከመታሰሩ በፊት ይተዳደር የነበረውም በሹፌርነት ነው።ከባህርዳር ከተማ ተይዞ በሽብር ወንጀል የተከሰሰው ገበየሁ ፈንታሁን ማዕከላዊ 8 ቁጥር በሚባል ጨለማ ቤት ታስሮ በነበረበት ጊዜ ድብደባና ሰቆቃ ተፈጽሞበት እንደነበር ይነገራል።
በተለይ በአንድ ወቅት ከደረጃ ገፍትረው እንደጣሉትና በዚህም ምክንያት የራስ ሕመም እንደነበረበት ነው የተገለጸው።አቶ ገበየሁ ፈንታሁን በታመመበት ወቅት በቂ ሕክምና እንዳላገኘም አብሮት ታስሮ የነበረው ጓደኛው ይፋ አድርጓል።
በመጨረሻም በእነ እስከዳር ይርጋ የክስ መዝገብ በሽብር ተከሶ የአራት አመት እስራት ተፈርዶበት ቆይቷል።በዚሁ የክስ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ እስከዳር ይርጋ ጥር 9/2010 ሲፈታ እርሱ ግን ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል።
ገበየሁ ፈንታሁን በቅርቡ ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ ግን የሞት ዜናው ነው የተሰማው።ተከሳሹ በቂ ሕክምና ሳያገኝ ከደከመ በኋላ ወደ ፖሊስ ሆስፒታል ቢወሰድም ትላንት የካቲት 18/2010 በዚሁ ሆስፒታል ሕይወቱ ማለፉን ከሃገር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የዋልድባ መነኮሳት በተከሰሱበት የሽብር ክስ ለመጋቢት 18/2010 ምስክር ይሰማባቸዋል ተብሏል።2ቱ ተከሳሽ መነኮሳት አባ ገ/ኢየሱስ ኪዳነማርያምና አባ ገ/ስላሴ ወ/ሃይማኖት ሲሆኑ እነዚሁም ክሳቸው ተቋርጦ ሊለቀቁ መሆኑን ቀደም ሲል በጠበቃቸው በኩል ተነግሮላቸው የነበሩ ናቸው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials