Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, February 25, 2018

ብአዴን ደመቀ መኮንን እና ገዱ አንዳርጋቸው በአመራርነት እንዲቀጥሉ ወሰነ | መግለጫ አወጣ – ይዘነዋል






(ዘ-ሐበሻ) ራሱን የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸውበድርጅቱና በክልሉ አመራርነት እንዲቀጥሉ ወሰነ::

በህወሓት እየተከፈላቸው የሚሰሩ ብሎገሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስልጣናቸው እንደተነሱ አድርገው ሲዘግቡ የቆየ ሲሆን የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለሕወሓት ብሎገሮች “ድሮ ብታልም…” የሚል ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም::

ከብአዴን አካባቢ የተሰሙ ምንጮች እንደሚሉት አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበር እንዲሁም አቶ ገዱ በምክትል ሊቀመንበርነትና በአማራ ክልል ር ዕሰ መስተዳደርነታቸው እንዲቀጥሉ ተወስኗል::

ይህ በ እንዲህ እንዳለ በሕወሃት በተሰጠው ተልእኮ መሰረት አቶ በረከት ስምዖን በሴራ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ለማንሳት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የብ አዴን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል::

በሌላ በኩል የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማእከላዊ ኮሚቴ ለረዥም ጊዜ በስብሰባ ላይ ከተቀመጠ በኋላ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል:: እንደሚከተለው ይነበባል::

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላ አገራችንና በክልላችን የተከሰተውን ሁኔታና ድርጅታችን ኢህአዴግ ያካሄደውን ግምግማ መነሻ በማድረግ ሰፋ ያለ ግምገማ አካሂዷል፡፡ በዚህ መሰረት ድርጅታችን፣ የክልላችን መንግስት እና ህዝብ የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር አገራችን የምትገኝበትን መሰረታዊና ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የሚታዩ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በመገምገም መሰረታዊ ለውጦችን ለማምጣት የሚያስችሉ በዝርዝር በመመልከት ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን በስኬት አጠናቋል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችንና የአገራችን ህዝቦች
የተከበራችሁ የብአዴን አባላትና የትግላችን ደጋፊዎች

ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው አገራችን እና ክልላችን ላለፋት ሃያ ሰባት ዓመታት በከፍተኛ የለውጥ እንቅሰቃሴ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ድርጅታችን ብአዴን ለዴሞክራሲ፣ ለልማትና ለሰላም የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የህይወት መስኮች ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ የህዝባችንን የዘመናት የለውጥ ጥማት ለማርካት በተካሄደው በዚህ እንቅስቃሴ የአገራችንም ሆነ የክልላችን ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት ተመዝግቦበታል፡፡ መድረኩ የፈቀደውን ያህል የህዝባችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ተችሏል፡፡ ድርጅታችንና መንግስት ከምንም ነገር በፊት እና በላይ የአርሶ አደሩን የአመራረት ዘይቤ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻልና ለመቀየር ከፍተኛ እንቀሰቃሴ አካሂደዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ አገራዊ እድገታችንን ከመደገፍ በተጨማሪ የክልላችን አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እና የምርታቸው ነፃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

በከተሞችም ፈጣንና ህዝብን ተጠቃሚ ያደረገ ልማት እውን እንዲሆን ከአነስተኛና ጥቃቅን ጀምሮ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ጥረት ተደርጐ መልካም ውጤት ተገኝቷል፡፡ ብአዴንና ክልላዊ መንግስታችን ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት የክልላችን ከተሞች ትንሳኤም ተበስሯል፡፡

እነዚህና ሌሎችም መልካም ጅምሮች እንደተጠበቁ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ግጭቶችና ልዩ ልዩ ችግሮች መፍትሔ የሚሹ ሆነው እንደሚገኙ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በግምገማው አይቷል፡፡

በክልላችን በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና ሁከቶች ተፈጥረው ውድ የሆነውን የሰዎችን ህይወት የቀጠፉና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ያስከተሉ አደጋዎች መፈጠራቸውን አስመልክቶ በመንስኤዎቻቸው እና መፍተሄዎቹ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በጥልቀት ተወያይቷል፡፡ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በዚህ አጋጣሚ በተፈጠሩት አደጋዎች በጠፋው የሰው ህይወት ጥልቅ ሃዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጸ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል፡፡ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም እና በችግሩ ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ የመውሰድ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ብአዴን ፀረ-ዴሞክራሲያዊውን እና አምባገኑን ስርአት በማስወገድ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር የህዝቦችን ትግል በመምራት በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ የድርሻውን የተወጣ በባህሪው ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ቢሆንም የውስጠ ድርጅት ትግሉ እና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጃ በማሳደግም ይሁን የነበረውን ማስጠበቅ እንዳልቻለ አረጋግጧል፡፡ ልዩ ልዩ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ስርነቀል በሆነ መንገድ ለማስተካከል ባለመቻሉ ምክንያት የድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ ህይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱንም ገምግሟል፡፡ ብአዴንን የመሰለ በሃሳብ ብልጫ መምራት የሚገባው ድርጅት በሃሳቦች ነጻ ዝውውር ላይ ገደብ የሚያደርጉ ዝንባሌዎች ታይተውበታል፡፡ድርጅቱና መንግስት የነደፉትን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አጥብቆ ይዞ ዝንባሌዎችን እየገመገሙ የለውጥ አመራር አለማረጋገጥና ህዝብን የሚያረካ አመራር የመስጠት ጉድለትም እንደታየ ተገምግሟል፡፡

በድርጅታችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ መድረኩ እየጠበበ መሄዱ በድርጅት ብቻ የማይታጠር ውጤት የነበረው ነው፡፡ ችግሩ እየሰፋ በሄደ ቁጥር በህብረተሰቡ ላይ ልዩ ልዩ ጉዳቶች አስከትሏል፡፡ በህገ መንግስታችን መሰረት የተለያዩ አስተሳሰቦች በነፃነት የሚራመዱበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና ይህንኑ በመተግበር ረገድ ጉድለት እንዳለ በዝርዝር ተገምግሟል፡፡ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ህብረተሰቡን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የሠብአዊ መብት አያያዝ ጉድለት፣የኑሮ ውድነት ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ችግር ፣ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንተሮባንድ ፣ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ መሆን በሚችለው ደረጃ እንዲሆን አለማድረግ እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ መፍታት ጊዜ የማይሠጠው ጉዳይ መሆኑን በመገምገም መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ዝርዝር አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
በክልላችን ሙስና እና ብልሹ አሠራር እየሰፋ እንደመጣ የተገመገመ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተፈጠሩ የህዝብ እና የድርጅት መድረኮች ላይ በየደረጃው በሚገኙ ኃላፊዎች ላይ የተነሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ እርምጃ የተወሰደ ቢሆንም አሁንም የመንግስትን አገልግሎት በእጅ መንሻ ማግኘት ያልተቀረፈ ችግር በመሆኑ ህብረተሰቡን ያማረረ ችግር መሆኑ ተገምግሟል፡፡ ሙስናን ለመታገል መላውን የክልላችንን ህዝብ በማሳተፍና የትግሉ ባለቤት በማድረግ በኩል እጥረት ያለ መሆኑንም ተገምግሟል፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት በተሰሩ ስራዎች የተለያዩ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ቁጥሩ ያለሆነ ህዝብ በድህነት ውስጥ ይኖሯል፡፡ የወጣቱን የራስ ጥረትና ተነሳሽነት በሚያሳድግ አኳኋን የሰራነው ስራ ከችግሩ ስፋት ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ወጣቶቻችን ለተስፋ መቁረጥ የተዳረጉ መሆኑን ፣ እንዲሁም ሴቶች የህዝባችንን ግማሽ ያህሉን ቁጥር ይዘው እያለ በሁሉም ዘርፎች እነሱን ከችግር የሚያወጣ በቂ ስራ እንዳልሰራን በዝርዝር ገምግመናል፡፡

በመጨረሻም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉም ሆነ ከፌደራል ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመገምገም የሚከተሉትን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
1ኛ. ዴሞክራሲን ማስፈን ለክልላችንም ሆነ ለአገራችን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በህበረተሰቡ ደረጃ ብአዴን የሚታገልለት አንዱ መሰረታዊ አላማ ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥም ሆነ በህዝቡ የሚታዩ የጸረ ዴሞክራሲ ተግባራትን በጽናት መታገል ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ማእከላዊ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ የድርጅቱን ህዝባዊነት እና አብዮታዊነት የሚፈታተኑትን የፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ተግባራት በጽናት መታገል የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ችግሮችን ለማረም ቀጣይነት ያለው ትግል መካሄድ እንደሚገባው ማእከላዊ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ከዚህ አኳያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተቋማት ማለትም የህዝብ ምክር ቤቶች፣ ሚዲያዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ የእምባ ጠባቂ ፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፣ የፍትህ አካላት፣ ተፎካካሪ ፖርቲዎችና አባሎቻቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ እንዲወጡ በማስቻል በኩል ያሉብን ጉድለቶች በዝርዝር ታይተው መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

2ኛ. የክልላችንና የሀገራችን ሰላም እና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በህዳሴ ጉዟችን ላይ ያጋጠመውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ በክልላችንም ሆነ በአገር ደረጃ እያጋጠሙ ያሉ ሰላማችንን የሚያደፈረሱ ችግሮች መሰረታዊ ምንጫቸውን በመፍታት አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ምልአተ ህዝቡን በማሳተፍ ሰላምን የሚያውኩና የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ ማናቸውም ህገ ወጥ ተግባራት ማስቆም የሚያስችል ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባውም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

3ኛ. ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከስር መሠረቱ ማድረቅ የሚቻለው ህብረተሰቡን የትግሉ አካል በማድረግ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት ህብረተሰቡን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች፣ የፍትህ መዛባት፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እና ስርጭት ችግር ፣ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ፣የመሬት ወረራ እና ከግብር ስርዓቱ ጋር የሚታዩ ችግሮችነ ህዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል፡፡

4ኛ. ሀገራችን የምትከተለው የፌደራል ስርዓት ህዝቦች እኩል የመልማትና የመጠቀም እድል እንዲረጋገጥላቸው ህገ-መንግስታዊ እውቅና ያገኘ መሆኑና በዚህ ረገድ ብዙ የተጓዝን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ብአዴን እንደሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች ሁሉ የአማራ ክልል ህዝቦችም ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋጋጥ እንዳለበት እና ከዚህ ያፈነገጡ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያጓድሉ ማናቸውም ተግባራት አገራዊ አንድነታችንን እንደሚጐዱ ያምናል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በግምገማው የፌደራል ስርዓታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የህዝባችንን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚጐዱ ማናቸውንም ዝንባሌዎችና ተግባራት ያለምንም ማመንታት መታገል እንደሚገባ አፅንኦት ሠጥቶ ተወያይቷል፡፡ በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ የፍትሃዊነት መጓደል የሚታይባቸውን ማናቸውም ዘርፎች የማስተካከል ስራ እንዲሠራና ለወደፊቱም ጥርጣሬ የሚያነግሱ መሰል ተግባራት እንዲታረሙ ተገቢ ትግል እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

የፌደራል ተቋማት የሰው ሃይል አደረጃጀት ብቃትንና ብሄራዊ ተዋጽኦን ማእከል በማድረግ እንዲደራጅ እና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ተቋማቱን ሪፎርም የማድረግ ስራ እንዲሰራም የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚገባው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀርና በመከባበር የሚኖሩበት ክልል ሲሆን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው የፌደራል ስርዓታችን መሰረት በቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘትና ባህልና ወጋቸውን የማሣደግ መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበት ክልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ይህንን አኩሪ እሴቱን የሚያጐድፉ ማንነትን፣ ከባቢያዊነትንና ፖለቲካዊ አቋምን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ ስህተቶች የሚከሰቱበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ይህንን ስህተት ድርጅታችንና መላው የክልላችን ህዝቦች የሚያወግዙት ተግባር እንደሆነ በመገንዘብ ከዚህ አኳያ አብሮነትንና መቻቻልን የሚያጎለብቱ ስራዎችን በተከታታይ መስራት እንደሚገባ እና ክልላችን የጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሁሉም ክልሎች በማስፋት ጠንካራ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

5ኛ. የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን እና የጸረ ድህነት ትግሉን በተመለከተ በክልላችን የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ለውጦች ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየውን አስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት በመቀየር ረገድ ተጨባጭ የእድገትና የለውጥ ጉዞ ውስጥ መሆናችንን ያሳያሉ፡፡ በእስካሁን ጉዟችን የተመዘገቡ ውጤቶች በህዝባችን ዘንድ ያጫሩት ተስፋ እንዳይጨልም ይበልጥ ለመስራትና ለመታገል ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ሊያላብሱ የሚችሉና የሚያጓጉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል የተጀመረውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ስራዎቻችንን የሚፈታተኑ ችግሮች እያገጠሙን መሆኑ ተገምግሟል፡፡ ስለሆነም የተጀመረውን የጸረ ድህነት ትግልና ፈጣን ልማት አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረገገጥ ጉዳይ ከምንጊዜውም በላይ የሞት ሽረት ርብርብ እንደሚደረግበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በተለይም የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እንደሚደረግ ተወስኗል፡፡ ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግና ልዩ የወጣቶች ፈንድ በማቅረብ ጭምር ርብርብ መደረግ እንደሚገባው አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች፣

ባለፉት አመታት በብአዴን አመራር ሁለንተናዊ የለውጥ ፍላጎታችሁ እንዲረጋገጥላችሁ ያሳደራችሁት ተስፋና ድርጅታችን ከድክመቶች እንዲወጣ የነበራችሁ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ማዕከላዊ ኮሚቴያችን ይገነዘባል፡፡ አሁንም ብአዴን የክልላችን ህዝቦች የሚጠብቁትን ለውጥ ለማምጣት በተለይም በክልሉ ኢንዱስትሪ የሚመራው ኢኮኖሚ ከመገንባት አኳይ ጠቃሚ ሚና በመጫወት ረገድ የነበሩበትን ጉድለቶች ገምግሞ በአዲስ የለውጥ መንፈስ ለመታገል ልዩ ልዩ አቅጣጫዎችንና የመፍትሄ ሀሳቦችን አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም የክልላችን ህዝቦች የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተሳትፏችሁን ይበልጥ በማጠናከር ተጠቃሚነታችሁ እንዲረጋግጥ ከብአዴን ጎን እንድትሰለፉ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣

የአማራ ህዝብ በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጪ በአስቸጋሪ ወቅቶች ሳይቀር ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በመከባበርና በአንድነት የመኖር አኩሪ ባህል ያዳበረ ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ በቀደሙት ጊዜያት እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች ሁሉ አስከፊ ድህነት ያጎሳቆለው ሲሆን ባለፉት የለውጥ አመታት ከድህነት ለመውጣት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ በአገራችንና በክልላችን ለተረጋገጡ ለውጦች በብአዴን የሚመራው የአማራ ክልል መንግስት እና ህዝብ የበኩላችንን ድርሻ ያበረከትን መሆኑን እናምናለን፡፡ አሁንም በጋራ ለምንገነባት ኢትዮጵያ ሀገራችን ብአዴንና የአማራ ክልል ህዝቦች የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅን አብሮነታችንን እንድናጠናክር እና አንድነታችንን የሚያላሉ ማናቸውንም ተግባራት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንድንታገል የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የብአዴን አባላት፣
ድርጅታችን ብአዴን አንግቦ የተነሳውን ህዝባዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አላማ ሊያሳካ የሚችለው ምልአተ ህዝቡን በማሳተፍ የድርጅቱ አባላት ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሲወጡ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት መድረክ የድርጅታችን አባላት ፅናት፣ ቁርጠኝነት እና ህዝባዊ ወገንኝነት በእጅጉ የሚፈለግበት ነው፡፡ በመሆኑም በግምገማው በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት የህዝባችንን አንገብጋቢ ችግሮች በመፍታት የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ትግል ግንባር ቀደም ሚናችሁን እንድትጫወቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪውን ሲያቀርብ በሙሉ እምነት እና ከታላቅ አደራ ጋር ነው፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን አርሶ አደሮች

በድርጅታችሁ ብአዴን እና በክልሉ መከንግስት መሪነት እና ድጋፍ ባለፉት አመታት ምርት እና ምርታመነታችሁን በማሳደግ ክልላችንን እና አገራችንን ከድህነት ለማውጣት ባደረጋችሁት ርብርብ ድህነትን መረታት እንደሚቻል አስምክራችኋል፡፡ ይህን እንጂ ድህነት አሁንም አሁንም ዋናው ጠላታችን በመሆኑ ብአዴን ምርት እና ምርታመነታችሁን በማሳደግ የጀመርነው የለውጥ ጉዞ እውን እንዲሆን ከአሁን ቀደሙም በላይ ጠንካራ አመራር ለመስጠት ተዘጋጀ መሆኑን እያረጋጋጠ የተለመደውን ታታሪነታችሁ እንድትቀጥሉ ብአዴን ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን የመንግስት ሠራተኞች እና ምሁራን
በብአዴንና በልማታዊ መንግስታችን አመራር የክልላችን ህዝቦች የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ተሳታፊና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስት ሰራተኞች እና የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በክልላችን ለተመዘገቡ ለውጦች የበኩላችሁን ድርሻ የተወጣችሁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት ተቋሞቻችን ህዝቡን የሚያማርሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዳሉ በግምገማችን አረጋግጠናል፡፡ ያለንበት ወቅት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ በክልላችንና በአገራችን ሁለንተናዊ የለውጥ አጀንዳ ላይ የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ ቢሆንም የክልላችንን ምሁራን ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ የሰራነው ሥራ አጥጋቢ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ አኳያ የክልላችንን ህዝቦች የሚያስመርሩ ችግሮችን በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ሚናችሁን እንድትወጡ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን እና የክልላችን የፀጥታ አካላት፣
ባለፉት አመታት መንግስትና ህዝብ የጣለባችሁን የክልሉን ሠላም የማስከበር ተልዕኮ ለመወጣት ያደረጋችሁትን ጥረትና በአስቸጋሪ ወቅቶችም የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር በክልላችን ሠላም እንዲከበርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለተጫወታችሁት አኩሪ ሚና ድርጅታችን ከፍተኛ አክብሮት እና አድናቆት አለው፡፡በመሆኑም በክልላችንና በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ህዝቡን አክብራችሁ ለህዝቡ ሰላምና ደህንነት የሚጠብቅባችሁን ሙያዊ ግዴታ እንድትወጡ እና ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋእትነት ለመክፈል ህዝባዊ ወገንተኛነታችሁና ዝግጁነታችሁን በድጋሜ እንድታረጋግጡ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ወጣቶች

ብአዴን የነገ አገር ተረካቢና የለውጡ ዋና ሀይል መሆናችሁን ያምናል፡፡ ብአዴንና እሱ የሚመራው የክልላችን መንግስት ባለፋት አመታት የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም ተፈላጊው ለውጥ እንዳልመጣ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የተጀመሩ የልማት ውጤቶችን በመጠበቅ፣ ተገቢ ጥያቄዎቹ በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ ብቻ በመጠየቅ፣ ድርጅትና መንግስት ያስቀምጧቸው የችግር መፍቻ አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በግንባር ቀደምነት በመሳተፍ ጥቅማችሁ እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ሚናችሁን እንድትጫወቱ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ በየደረጃው የምትገኙ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትና የህዝብ ማህበራት፣
ድርጅታችን ብአዴን በክልላችን እና በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት ለዴሞክራሲ ተቋማት እና የህዝብ ማህበራት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ተቋማዊ ነፃነታችሁን በመጠበቅ በክልላችንና በአገራችን የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ፣የህዝባችን ዲሞክራሲያዊ አንድነት በማጠናከርና አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን እንዲሁም ህብረተሰቡ የሚጠቀምበት ፈጣን ልማት እንዲረጋገጥ፣ የክልላችን ህዝብ የጣለባችሁን አደራ በመወጣት የሚጠበቅባችሁን ሚና እንድትጫወቱ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ ከክልላችን ውጭ የምትኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣
በአገራችን ከክልላችን ውጭ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት አመታት ብአዴን ህገ-መንግስታዊ የፌደራል ሥርአቱ በፈጠረልን መልካም ዕድል በመጠቀም አገራዊ አንድነት እንዲጠናከርና ከእህትና አጋር ድርጅቶችና ከክልላዊ መንግስታት ጋር በመተባበር በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መንገድ ልዩ ልዩ የመደጋገፍ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከክልላችን ውጭ የሚገኙ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጥቅም በዋናነት የሚረጋገጠው ክልሎቹን በሚመሩ እህትና አጋር ድርጅቶችና ክልላዊ መንግስታት መሆኑን ብአዴን በጥብቅ ያምናል፡፡ለዚህ ጥቅም መረጋገጥም ብአዴን የአማራ ብሔር ተወላጆች ከሚኖሩባቸው ክልሎች እና እህትና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ከክልላዊ መንግስታት ጋር በመተባበር የሰራው ሥራ በቂ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ጠንካራ መደጋገፍ መፍጠርና የዜጎች መሠረታዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶች እንዲረጋገጡ በተሻለ ሁኔታ መስራት እንዳለበትም ተገንዝቧል፡፡ በዚህ መሠረት በመደጋገፍ ላይ በመመስረት ከክልላችን ውጭ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ከክልላችን ውጭ የምትኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከምትኖሩባቸው ክልሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በዴሞክራሲያዊ አንድነት መንፈስ በመተባበር የጋራ ጥቅሞቻችሁ እንዲከበሩ እና ፀንቶ የኖረው አንድነታችሁ እንዲጎለብት የሚጠበቅባችሁን ሚና እንድትጫወቱ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ በውጪ አገራት የምትኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች፣
በውጭ አገር ያካበታችሁትን እውቀትና ልምድ እዲሁም ያፈራችሁትን ሀብት በመጠቀም በቻላችሁት ሁሉ የራሳችሁንና የክልላችሁን ህዝቦች ጥቅም የሚያረጋግጥ ተሳትፎ እንድታደርጉ ብአዴን ከምንጊዜውም የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ስለሆነም ወደ ክልላችሁና አገራችሁ መጥታችሁ የአገራችንን እና የህዝባችንን ጥቅም ማዕከል በማድረግ በቻላችሁት ሁሉ እንድትሳተፉ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ እህትና አጋር ድርጅቶች፣

በአገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትና የፌደራል ሥርአቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተደረገው ጥረት ብአዴን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለነበረን የትግል አንድነትና መደጋገፍ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ አሁንም ድርጅታችን እና አገራችን የገጠማቸውን ችግር ፈትተን የህዝቦቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ለህዳሴ ጉዟችን መሠረት የሚጥሉ ለውጦችን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ርብርብ እንደ ወትሮው ሁሉ የትግል አንድነታችሁን በማጠናከር ከጎናችን እንድትሰለፉ እና ለአገራችን ህዳሴ ስኬት በጋራ እንድንረባረብ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች እና አባላት፣

ብአዴን በክልላችንና በአገራችን የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እንዲገነባ የመድብለ ፖርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ፍቱን መድሀኒት እንደሆነ ያምናል፡፡ ስለሆነም የአመለካከት ልዩነታችን ሳይገድበን ዘለቄታ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል፡፡በመሆኑም ከብአዴንና ከክልላችን መንግስት ጋር ተባብራችሁ ለክልላችን እና ለሀገራችን ህዝቦች ለውጥ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ማዕከል በማድረግ አብራችሁን እንድትሰሩ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የተከበራችሁ የክልላችንና የአገራችን ህዝቦች
ከመላ ህዝባችን ጋር በመሆን ለዴሞክራሲ ፣ለልማት እና የህዝብ ተጠቃሚነት ባካሄድነው ትግል ሀገራችን ከማሽቆልቆል ሂደት ተላቃ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በእድገት ጎዳና ተራምዳለች፡፡በድርጅታችን ኢህአዴግ መሪነት መላ የአገራችን ህዝቦች ባካሄዱት ትግል ኢትዮጲያ እጅግ በሚያስጎመጅ የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡
ይህንን ተከትሎ ማንኛውም በለውጥ ላይ ያለ ህብረተሰብ እንደሚያጋጥመው ሁሉ አዳዲስ ፈተናዎች አጋጥመዋታል፡፡ድርጅታችን ብአዴን ባካሄደው ግምገማ የመድረኩን ፈተናዎች የተገነዘበ እና ለመፍታትም የተዘጋጀ በመሆኑ ሁሌም እንደምታደርጉት በፅናት እና በትዕግስት የለውጥ ትግላችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን ስናቀርብ አገራችን ከማንኛውም አደጋ ተጠብቃ ውጤት እንደምታመጣ በመተማመን ነው፡፡
ከህዝባችን ጋር ሆነን የማነፈታው ችግር የለም !!!!!
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ
የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም
ባህር ዳር

No comments:

Post a Comment

wanted officials