Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 26, 2018

*ስለ ሶርያ እንማልዳለን***መ/ር ታሪኩ አበራ



**ስለ ሶርያ እንማልዳለን***

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህን ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም የምሕረት እጅህን ዘርጋላቸው።

የነበርህ ፣ያለህና የምትኖር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ በሰላም ውለን እንድናድር፣ በሰላምም ወጥተን እንድንገባ ስለ ረዳኽን ክብርና ምሥጋና ለታላቅ ስምህ ይሁን።


ቅዱስ አባት ሆይ ምንም እንኳ የእኛም ሀገር በችግርና በመከራ ውስጥ ብትሆንም ከእኛ በባሰ ሁኔታ በሶርያ ምድር ላይ የአዳም ዘር እንደ ቅጠል እየረገፈ ደማቸውም ከምድር አፈር ጋር እየተቀላቀለ ነውና ጌታ ሆይ ቀኝህን ዘርጋላቸው።እረፍትና ሰላምንም አንተ አብዛላቸው።በሶርያ ምድር ላይ የሰው ደም ጠምቶት ከጥልቁ የወጣው የአጋንንት ሠራዊት ሁሉ በመለኮታዊ እሳት ተቃጥሎ ወደ ሲዖል ይወርወር።

ጌታ ሆይ በፈሰሰው ደምህ፣በአማኑኤል ስምህ እንማጸናለን የንጹሐን ሕጻናትን እልቂት በታላቅ ክንድህ አቁመው፣እሮጠው ያልጠገቡ እግሮች በከባድ መሳሪያ እየተቆረጡ ነው፣ አባ እማ ብለው የሚኮለተፋ አንደበቶች በረጋ ደም እየተቆለፋ ነው፣አንዳችም ነውርና ኃጢአት የሌለባቸው ጨቅላ ህጻናት በግፍ ደማቸው እንደ ጅረት እየፈሰሰ በሞት እየተነጠቁ ነው ፣ወላጆች ልጆቻቸውን በመሪር ሞት እየተነጠቁ የወላድ መኻን ሆነዋል፤ ልጆችም የወላጆቻቸውን አስከሬን እያዩ በምድረ በዳ እንደ ሚቅበዘበዝ ግልገል ሆነዋል። ጌታ ሆይ የሶርያ ምድር አኬልዳማ ሆናለችና በምህረት ዓይንህ ተመልከታቸው የሀገራቸውን እንቆቅልሽ በመለኮታዊ ጥበብህ አንተው ፍታላቸው።

መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ ሆይ ምንም እንኳ ዛሬ ላይ ኢጥሙቃን ቢበዙባትም ሶርያ የታላቁ አባት የቅዱስ ኤፍሬም ሀገር ናት።የአንተ አዳኝነት የእናትህ ክብርና ምሥጋና የተነገረባት የክርስቲያኖች ምድርናት ዛሬም ስለ ስምህና ስለ ክርስትናቸው ዋጋ የሚከፍሉ አማኞች ያሉባት ምድርናትና እባክህ ጌታ ሆይ በእነርሱ ላይ የተነሳውን የጦርነት እሳት በቅዱስ መንፈስህ አብርድላቸው።
እምባቸውንም አብስላቸው።ዳግም እግዚአብሔር ታላቅ ነው ብለው ስለ አዳኝነትህ የሚዘምሩበትን የንስሐ እድሜ ስጣቸው።

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ በፊትህ ዝቅ ብለን እንማፀንሃለን በሶርያም በኢትዮጵያም ላይ አንተ ከፍ ብለህ ታይ ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔር ረዳን ብሎ አንተን ያክብር ።ጦርነቱን በሰላም ቀይረህ ወጀብ ማእበሉን በታላቅ ክንድህ ገስፀህ ለሕዝብህ እረፍትና መረጋጋትን አምጣ።የሆነው ችግርና መከራ ሁሉ አንተን መፍራትና አንተን ማምለክን አስተምሮን ይለፍ እንጂ ከአንተ የሚለየን እልኽኞችና ከሀዲዎች አያድርገን።ጌታ ሆይ በኢትዮጵያም በሶርያም ምድር እኛ የማናውቀው አንተ የምታውቀው በድብቅ የተሰራ ኃጢአትና ግፍ ይኖራል ነገር ግን ጌታ ሆይ በቃ በለን በቀራንዮ ስለ ፈሰሰው ደም ብለህ ይቅርበለን ።በዝሙት፣በግብረ ሰዶም፣ጽንስ በማስወረድ፣በጣዖት አምልኮ፣በጥንቆላ፣በዘረኝነትና በአድመኝነት አንተን የበደልንበትን ያለፈውን ዘመን ይቅርበለን።

በእግዚአብሔር ፊት የጽድቅን ታጋድሎ በድል አጠናቃችሁ የጽድቅን አክሊል ያገኛችሁ ቅዱሳን ሁላችሁ የሶርያ ምድር እንድትፈወሰ ኢትዮጵያም እንድትባረክ ምልጃችሁ ይርዳን።

ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ሆይ የባለሟልሽ የቅዱስ ኤፍሬም ሀገር ሰላምና ምሕረት ከልጅች እንደ ሰማይ ጠል እንዲወርድላት ምልጃሽ አይለያት።አሜን።

እባካችሁ ሁላችን በጸሎት እናግዛቸው ዘንድ ይህንን ጸሎት ለሰው ሁሉ ሼር አድርጉት::

መ/ር ታሪኩ አበራ

እባካችሁ ኮሜንት መስጫ ላይ የአሻንጉሊት ምስል አትለጣጥፋ አንዲት የጸሎት ቃል ብቻ ከልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩላቸው።
Image may contain: 2 people, people standing, beard and outdoorImage may contain: 2 people, people sitting

No comments:

Post a Comment

wanted officials