Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 26, 2018

የዋልድባ መነኮሳት ምስክር ሊሰማባቸው ነው፤ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የፖለቲካ እስረኛ በእስር ቤት ህይወቱ አለፈ

በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተባቸው የዋልድባ መነኮሳት ለመጋቢት 18/2010 ዓም ምስክር ይሰማባቸዋል ተብሏል። ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የፖለቲካ እስረኛ በእስር ቤት ህይወቱ አለፈ።
በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ ተከሰው ከነበሩት 35 ተከሳሾች መካከል 32ቱ ክሳቸው ተቋርጦ የተፈቱ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ነጋ ዘላለም መንግስቴ፣ 4ኛ ተከሳሽ አባ ገ/ እየሱስ ኪ/ማርያም እና 5ኛ ተከሳሽ አባ ገ/ስላሴ ወ/ሐይማኖት ብቻ ክሳቸው ቀጥሏል።
የዛሬው የካቲት 19/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዞ የነበረው በመዝገቡ ከተጠቆጠሩት ምስክሮች መካከል ጉዳያቸው ይቀጥላል በተባሉት 3ቱ ተከሳሾች ላይ የሚቀርቡትን አቃቤ ህግ ለይቶ እንዲያስመዘግብ እና መነኮሳቱ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ነበር። በዚህም መሰረት 1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ ምስክሮች በመነኮሳቱ እና በ2ኛ ተከሳሽ አቶ ነጋ ዘላለም ላይ ይመሰክራሉ ተብሏል። የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማትም ለመጋቢት 18 ቀጠሮ ተይዟል።
በሌላ በኩል የቂሊንጦ እስር ቤት መነኮሳቱ የምንኩስና ልብሳቸውን እንዲያወልቁ እንያገደዳቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን እስር ቤቱ ለካቲት 30 መልስ እንዲሰጥ ታዟል።
4ኛ ተከሳሽ አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም እና 5ኛ ተከሳሽ አባ ገ/ስላሴ ወ/ሐይማኖት ልብሳቸውን አናወልቅም በማለታቸው ባለፉት ቀጠሮዎች ያልቀረቡ ሲሆን በአቤቱታቸው ላይ ቅጣት ቤት እንደሚገኙ መግለፃቸው ይታወሳል። የሁለቱም መነኮሳት አካል ላይ ባለፉት ጊዜያት ያልነበረ ጉስቁልና ይስተዋላል።
አሳዛኝ ዜና
ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የፖለቲካ እስረኛ በእስር ቤት ህይወቱ አለፈ
በእነ እስከዳር ይርጋ ክስ መዝገብ በ”በሽብር” ክስ አራት አመት ተፈርዶበት ይፈታል ተብሎ እየተጠበቀ የነበረው 2ኛ ተከሳሽ ገበየሁ ፈንታሁን በእስር ቤት ባጋጠመው የጤና እክል ህይወቱ አልፏል። ተከሳሹ በቂ ሕክምና ባለማግኘቱ ከደከመ በኋላ ወደ ፖሊስ ሆስፒታል ተወስዶ ትናንት የካቲት 18/2010 በፖሊስ ሆስፒታል ህይወቱ አልፏል።
ገበየሁ ፈንታሁን ማዕከላዊ 8 ቁጥር በሚባል ጨለማ ቤት ታስሮ እንደነበርና በቆይታው ድብደባ እንደደረሰበት በወቅቱ አብሮ ታስሮ የነበረው ጓደኛው ገልፆአል። በተለይ በአንድ ወቅት ከደረጃ ገፍትረው እንደጣሉትና በዚህም ምክንያት የራስ ህመም እንደነበረበት ተገልፆአል። አቶ ገበየሁ ፋንታሁን በታመመበት ወቅት በቂ ህክምና እንዳላገኘ ጓደኛው ገልፆአል።
አቶ ገበየሁ ፋንታሁን የአንድ ልጅ አባት እና ባለትደር እንደነበርና ከባህርዳር ተይዞ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ በሾፌርነት ተቀጥሮ ቤተሰቦቹን ያስተደድር እንደነበር ተገልፆአል። በክስ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ የነበረው አቶ ገበየሁ ፋንታሁን አራት አመት ተፈርዶበት የነበር ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ እስከዳር ይርጋ ጥር 9/2010 ዓም ተፈትቷል። አቶ ገበየሁ ፋንታሁን ይፈታል ተብሎ እየተጠበቀ እንደነበር ታውቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials