(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2010)
ባለፉት አምስት አመታት በአዲስ አበባ ከ12 ሺ በላይ አባወራ/እማወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ።
በተያዘው አመትም ከ2ሺ በላይ አባወራና እማወራዎች ከ700 ሔክታር መሬት ላይ ይፈናቀላሉ።
ከአመታዊ በጀቱና ገቢው ከፍተኛ ድርሻውን ከመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ እንዲያተኩር ያደረገው የከተማው መስተዳድር ባለፉት አምስት አመታት ከ12ሺ በላይ አባወራና እማወራዎችን የመኖሪያ ቤት በማፍረስ ማፈናቀሉን የቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ዘግቧል።
በዘገባው መሰረት ተፈናቃዮች የተከፈላቸው ካሳ አነስተኛ መሆን፣ምትክ የመኖሪያ ቤት አለመስጠት፣ የስራ እድል አለማመቻቸትና ወደ ጎዳና መውደቅ ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም በተለይም የአዲስ አበባ አርሶ አደሮች መፈናቀል ከባህልና ማንነት መነቀል ጋር እንደሚያያዝ ተገልጿል።
ነዋሪዎች የሚፈናቀሉበት መሬት ሲሸጥ በካሬ ሜትር እስከ 300ሺ ብር ቢደርስም እነሱ ግን ተገቢ ካሳ አያገኙም።የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ግርማ ለአንድ ካሬ ሜትር ካሳ 62 ብር ያህል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ለተፈናቃዮች የሚሰጠው ካሳና አስተዳደሩ በሊዝ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት የተጠየቁት የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ግርማ ከአርሶ አደሩ የሚወሰደው መሬት ለመሰረተ ልማት ግንባታ ለሕዝቡ ጥቅም ስለሚውል በዛ መልኩ መታየት አለበት ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማዋ አስተዳደር የሼህ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሜድሮክ ኢትዮጵያ አጥሮ የያዛቸውን ቦታዎች ውል ለማቛረጥ መወሰኑን ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ብቻ በሜድሮክ ኢትዮጵያ በ55ሺ ካሬ ሜትር የተያዙ ሁለት ይዞታዎች ውላቸው ተቋርጧል።
እነዚህ ውላቸው የተቋረጡ ሁለት ይዞታዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለበርካታ አመታት ታጥረው የተያዙ ቦታዎች ናቸው።
በቀጣይ ቀናትም በሜክሲኮ፣በሰሚት፣በቦሌ ወሎ ሰፈር፣በየካ፣በቂርቆስ በአጠቃላይ ከ104 ሺ በላይ ካሬ ሜትር የታጠሩ ቦታዎች ውላቸው ይቋረጣል።
እንዲሁም ሜድሮክ ኢትዮጵያ አጥሮ የያዛቸው የሸራተን ማስፋፊያና በፒያሳ ለበርካታ አመታት የታጠረው ይዞታ በቀጣይ ጊዜ እንደሚታይ ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment