Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, April 20, 2018



 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጎንደር ሕዝብ ዛሬም አዲስ ታሪክ ይሰራል ሲሉ  ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር  አብይ አህመድ ይህንን የተናገሩት ዛሬ በጎንደር ስታዲየም ለጎንደር ሕዝብ ባደርጉት ንግግር  ነው።
በፕሮግራሙ  ላይ የታደሙት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የአማራ ክልል ሕዝብ ከዶክተር አብይ ጎን የተሰለፈው ለውጥ ስለሚፈልግ ነው ብለዋል።
“ ጎንደር የድንቅ ታሪክ ባለቤት- የዘመነዊቷ ኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት- የጥበብ እና ውበትም ቤት- የእምነት እና የድል ተምሳሌት ናት፡፡” በማለት ንግግራቸውን ያሰሙት  ዶክተር አብይ አህመድ
“ ከሁላችንም በፊት ትላንት ላይ ሆኖ ዛሬን ያየውና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውጥን በምናቡ የጠነሰሰው የመይሳው ልጆች ናችሁና በተለመደው ትእግስታችሁና አርቆ አሳቢነታችሁ ከጎናችን እስካላችሁ ድረስ በምንችለው ፍጥነት እና መጠን ተረባርበን በመስራት በጥበብ የማናቋርጠው የህይወት እክል በፍጹም ሊኖር እንደማይችል አጥብቄ አምናለሁ፡፡” በማለት ለጎንደር ሕዝብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ  የጎንደር ሕዝብ ዛሬም ታሪክ ይሰራል ሲሉ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።
“ የጎንደር ህዝብ አዲስ ታሪክ እንደሚሰራ አምናለሁ፡፡ ጎንደር ማለት ባለፈው ታሪክ የበቃው፣ የደከመና የነጠፈ ሳይሆን ብርቱ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በመተባበር ዛሬም በስራ ላይ ያለ፣ አኩሪ ገድል የሚፈጽም የጀግና ህዝብ ሀገር ነው፡፡” በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በስታዲየም ለተሰበሰበው የጎንደር ሕዝብ ንግግር እንዲያደርጉ የጋበዙት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ሕዝብ በዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት  መደሰቱን ገልጸዋል።
ይህም ደስታ የመነጨው የአማራ ክልል ሕዝብ ለውጥ በመፈለጉ እንደሆነ አመልክተዋል።
“የአማራ ህዝብ በአጠቃላይ በተለይም የክልላችን ህዝብ እርስዎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ ለምን ዳር እስከ ዳር በደስታ ሃሴት ተሞላ? ለምንስ ከሞላ ጎደል ይህን ያህል ከጫፍ ጫፍ በአንድ ጊዜ የሚበዛው ህዝብ በሚያስደንቅ ሁኔታ የእርስዎን መመረጥ ተቀበለው?” በማለት የጠየቁት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  “መልሱ፣ ይህ ህዝብ ለውጥ በመፈለጉ እርስዎን የለውጥ ምልክትና ተስፋ አድርጎ በመመልከቱ ነው።” በማለት  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል 
              አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለጎንደር ሕዝብ በሰጡትም ምስክርነትም
“ይህ ዛሬ በደመቀ ሁኔታ በአክብሮት የተቀበለዎት የጎንደር ህዝብ ከጥንት እስከ ዛሬ ለፍትህ መስዋዕትነት እየከፈለ የመጣ ህዝብ ነው ። ለፍትህ ሺዎችን የገበረ ህዝብ ነው ። አሁንም እርስዎ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነፃነትን ለማስፈን በሚያደርጉት ትግል የጎንደር ህዝብ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የማያቅማማ መሆኑን በሙሉ እምነት በታላቅ ኢትዮጵያዊ አክብሮትና ኩራትም ጭምር ነው ፡፡” ብለዋል ።

No comments:

Post a Comment

wanted officials