Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, April 16, 2018

በኤች አር 128 የተገኘው ድል ለሚቀጥለው ስራ ብርታት የሚሰጥ ነው ተባለ



በኤች አር 128 የተገኘው ድል ለሚቀጥለው ስራ ብርታት የሚሰጥ በመሆኑ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለወሳኙ ትግል እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀረበ።
ትላንት ኤች አር 128 የተሰኘውን ረቂቅ ሰነድ የአሜሪካን ኮንግረስ በሙሉ ድምጽ ካሳለፈው በኋላ ለኢሳት ቃልመጠይቅ የሰጡት የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል አመራር አባላት እንደገለጹት በኤች አር 128 የተገኘው ድል የመጨረሻው አይደለም፡ ቀሪ ተግባር የሚጠብቀን በመሆኑ በሞራልና አሸናፊነት መንፈስ ወደፊት መራመድ አለብን ብለዋል።
በኤች አር 128 መጽደቅ ኢትዮጵያውያን ከመላው ዓለም ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
በኢሬቻ በዓል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ እንቅስቃሴው የተጀመረው የኤች አር 128 የህግ ረቂቅ ትላንት ዋናውን መሰናክል አልፏል።
የትላንቱ የአሜሪካን ኮንግረስ የሚሰጠው ድምጽ ለኢትዮጵያውያን በጉጉት የሚጠበቅ ነበር።
ረቂቅ ህጉ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን የህወሀት አገዛዝ በሰብዓዊ መብት ረገድ ተጠያቂ የሚያደርግ በመሆኑ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ናፋቂዎች የደስታ፡ ለአገዛዙና ደጋፊዎቹ ደግሞ የሀዘን ቀን ሆኖ አልፏል።
ረቂቅ ህጉ ያለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምጽ ማለፉ ደግሞ ክስተቱን የተለየ አድርጎታል።
ከ130 በላይ የምክር ቤት አባላት ሙሉ ድጋፍ ያገኘው፣ በተቀረው የምክር ቤቱ አባላት ያለተቃውሞ ያለፈው ረቂቅ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት፡ ለፍትህና እኩልነት ለሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ትግል የሚያግዝ በመሆኑ ክፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ረቂቅ ህጉ የምክር ቤቱን አባላት ይሁንታ አግኝቶ እንዳያልፍ የህወሀት አገዛዝ በወር ከ150ሺህ ዶላር በመመደብ ጎትጓቾችን ቀጥሮ በዲፕሎማሲው ረገድ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ያደረገ ቢሆንም ሊሳካለት አልቻለም። ይህ መሆኑ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር በልዩ የደስታ ስሜት የኮንግረሱን ውጤት ተቀብለውታል።
ይህ ረቂቅ ህግ በኮንግረሱ በሙሉ ድምጽ እንዲያልፍ ካደረጉት የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች አንዱ የሆነ የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ለዚህ ስኬት የሚቻላቸውን ላበረከቱት ሁሉ ምስጋናውን በማቅረብ ለቀጣዩ ስራ እንዘጋጅ ሲል ጥሪ አድርጓል።
የካውንስሉ አመራር አባላት ከኢሳት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት የኤች አር 128 መጽደቅ ትልቅ ድል ቢሆንም የመጨረሻው ነው ማለት አይደለም።
በሴኔት ደረጃ የረቀቀው ኤስ አር 168 የተሰኘ ሌላም ተመሳሳይ ረቂቅ ህግ በመኖሩ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ የካውንስሉ አመራር አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተገኘው ውጤት ሳያዘናጋን ወደ ዋናው ድል ለመድረስ እንረባረብ ብለዋል የካውንስሉ አመራሮች።
የሴኔት ረቂቅ ህጉ እስከአሁን ከ100 ሴናተሮች የ25 ሴናተሮችን ድጋፍ ማግኘቱን መረጃዎች ያመልክታሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም HR 128 በአሜሪካ ምክር ቤት መጽደቁ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይን  መንግስትን አስቆጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፓርቲና ለመንግስት መገናኛ በላከው መግለጫ ውሳኔው ወቅቱን ያልጠበቀና ተገቢ ያልሆነ ነው ሲልም  ተቃውሟል።
የሁለቱን ሃገራት ግኑኝነት ግምት ውስጥ ያላስገባ አፍራሽ ድርጊት  ነው ሲልም ገልጾታል።
ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንዲሁም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን  ከፍተኛ ጥረት በምናደርግበት ወቅት እንዲህ ያለ ወሳኔ መተላለፉ ተገቢ አይደለም ሲልም ተቃውሟል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ያሳለፈው ውሳኔ  የኢትዮጵያ መንግስት እስረኞችን በመፍታት፣ የፖለቲካ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማካሄድ እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ሉዓላዊነታችንንም ያላከበረ ነው ሲልም አውግዟል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials