Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, April 11, 2018

የዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮ-ሶማሊ ጉብኝት በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥረ

Image may contain: one or more people and people standing

የዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮ-ሶማሊ ጉብኝት በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥረ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 02 ቀን 2010 ዓ/ም) አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብህ አህመድ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ጉብኝታቸውን በኢትዮ-ሶማሊ ክልል ቢጀመርም፣ ከጉብኝቱ በሁዋላ የክልሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ከጅጅጋና ሌሎችም የክልሉ ከተሞች ከ1 ሚሊዮን ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ትኩረት መስጠታቸው ተገቢ ቢሆንም፣ የአብዲ ሙሃመድ ኡመር አገዛዝ የሚፈጽመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሳያነሱ በመቅረታቸውና በኦሮሞና ሶማሊ ህዝብ ግንኙነት ብቻ ትኩረት አድርገው መመለሳቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። በክልሉ እየተፈጸመ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰት አንድ ቃል እንኳን ሳይተነፍሱ መቅረታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ዶ/ር አብይ ወደ ጅጅጋ ከማምራታቸውን ከጥቂት ቀናት በፊት ፣ በክልሉ ስለሚፈጸመው ወንጀል ያጋልጣሉ የተባሉ የአገር ሽማግሌዎች በቁም እስር ላይ እንዲሆኑና ጠ/ሚኒስትሩን እንዳያገኙት ተደርገዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ጉብኝት ባደረጉበት እለት ደግሞ ቀብሪደሃር ውስጥ እስማኤል ቃማን ባሂና ሳኢድ አህመድ ማጋን የተባሉ የአገር ሽማግሌዎች ታስረዋል።
ዶ/ር አብይ በአቶ አብዲ ኢሌ በጥንቃቄ ከተመረጡ የአገር ሽማግሌዎች ጋር ብቻ መነጋጋሩን የሚናገሩት የጅጅጋ ነዋሪዎች፣ ቢያንስ በክልሉ ከማዕከላዊ እስር ቤት በላይ ወንጀል የሚፈጸመብትን “ የኦጋዴን እስር ቤት” እንዲዘጋ ወይም ሰቆቃው እንዲቀም መልዕክት ማስተላለፍ ነበረባቸው።
ከዶ/ር አብይ ጉብኝት በሁዋላ በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል አንዳንዶች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። አጎታቸው ዱልሚዲድ በሚባል የአብዲ ኢሌን ድርጊት በሚቃወም ድርጅት ላይ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ የታሰሩት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሃሰን አብዱላሂ ባዴ በእስር ቤት ውስጥ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በደም የተጨማለቀ የዶ/ር ሃሰን ልብስ ለቤተሰቡ መሰጠቱንም የጅጅጋው ወኪላችን ካደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል።
ከጉብኝቱ በሁዋላ አቶ አብዲ ኢሌ የህወሃት ጄኔራሎች ስልጣን አሁንም እንዳልተነካና ከእነሱ ጋር ያለው ግንኙነት የጠበቀ መሆኑን፣ አሁን ደግሞ ኦሮሞዎች ነፍጠኛውን አማራ አምነው አብረው እንዳይሰሩ ምክር በመለገስ እንደሚሰሩ ለአገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል። አቶ አብዲ ኢሌ ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ እንደማይወደቅ ይልቁንም ኦሮሞና አማራ አብረው እንዳይሰሩ ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልጻል። ኢሳት በ2013 ባቀረበው አንድ ቪዲዮ ላይ አቶ አብዲ አማራ እና ኦሮሞ አብረው ለመስራት እንደማይችሉ፣ የሶማሊ ህዝብ ትግሬን ብቻ መደገፍ እንዳለበት መናገራቸው ይታወቃል።
ምንም እንኳ አቶ አብዲ ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ጋር ያላቸውን ግንኙኑት “ይቅር በሉኝ” በማለት እንዳደሱት ቢገልጹም፣ የክልሉ ልዩ ሃይል እንደሚፈርስ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ፍንጭ መስጠታቸው ለአቶ አብዲ የሚዋጥ አልሆነም። የሶማሊ ክልል ህዝብ ልዩ ሃይል እንደማያስፈልገውና አካባቢውን በፖሊስና በወታደሮች ማስተዳደር እንደሚበቃ ዶ/ር አብይ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ አቶ አብዲ እሳቸው የሚመሩት ጦር ከሌለ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በመናገር ልዩ ሃይሉ እንዳይበተን ለማድረግ ያደረጉት ሙከራ ለጊዜው ዶ/ር አብይን ያሳመነ እንደማይመስል ምንጮች ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አንዳንድ ወገኖች እንደገለጹት የልዩ ሃይሉ የመበተን ሃሳብ አብዲ ኢሌን በሂደት ለመምታት የተወጠነ ነው። ልዩ ሃይሉ ከተበተነ አብዲ ኢሌ የሚያስፈራራበት ጦር ስለማይኖረው እና ብቻውን ተነጥሎ ስለሚቀር፣ በእሱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይቀላል ሲሉ እነዚህ ወገኖች አስተያየቶቻቸውን ይሰጣሉ።
ዶ/ር አብይ የብአዴንን፣ ኦህዴድንና ደኢህዴንን ተወካዮች ይዘው ሲሄዱ የህወሃት ባለስልጣናት ባለመካተታቸው ለምን የሚል ጥያቄ አስነስቷል። የተወሰኑ ወታደራዊ አዛዦች የተገኙ ቢሆንም እነሱም የምስራቅ እዝ አባላት ነበሩ።
በሌላ በኩል ከሶማሊ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ክልሉ እንዲመለሱ ለማድረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተፈናቃዮች ተቃውመዋል። ተፈናቃዮቹ ካሳ እንዲከፈላቸው፣ በህዝቡ ላይ ይህን ድርጊት የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ለወደመባቸው ንብረትም አስፈላጊው ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሳይመቻቹ ወደ ሶማሊ ክልል ተመለሱ መባሉት ተፈናቃዮች እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials