Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, April 21, 2018

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት ይፈታል ሲሉ ዶ/ር አብይ አህመድ ተናገሩ


የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት ይፈታል ሲሉ ዶ/ር አብይ አህመድ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ/ም) አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ጎንደር ከተማ ተገኝተው ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ስብሰባ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ በህግ ሊፈታ እንደሚችል ህዝቡ ማመን አለበት ብለዋል ፡፡ “ህገ መንግስቱ ይህን ጉዳይ ሊፈታ ይችላል፡፡ በቀጣይም ከወልቃይት ኮሚቴዎች ጋር ውይይት አደርጋለሁ ‘ማለታቸውን የክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ዶ/ር አብይ የአማራ ክልል ህዝብ በዚህ ጉዳይ መቀሌ ላይ በሰጡት መልስ በማዘኑ ወደ ጎንደር እንዳይሄዱ ተጠይቀው እንደነበር፣ እርሳቸው ግን ባጠፋም የጎንደር ህዝብ ቆንጥጦ ያስተምረኝ ብለው መምጣታቸውን እንደተናገሩም፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የስብሰባውን ተሳታፊዎች በመጥቀስ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ዘግቧል።
ዶ/ር አብይ የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላቱን ይቅርታ መጠየቃቸውንም ጋዜጠኛው ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልቃይት ማንነት አስተባባሪ የኮሚቴ አባላት ከሆኑት መካከል አቶ አታላይ ዛፌን፣ጌታቸው አደመን፣ ተሻገር ወ/ሚካኤልና ወረታው አዛናውን ጠርተው ያናገሩ ሲሆን፣ የኮሚቴ አባላቱን ከወንበር ተነስተው ይቅርታ መጠየቃቸውን ጋዜጠኛው አስነብቧል።
በውይይቱ ወቅት አቶ አታላይ ዛፌ “ወንድ ልጅ ራሱን ይዞ ያለቀሰበት ጊዜ ቢኖር እርስዎ መቀሌ ላይ በወልቃይት ጉዳይ ከተናገሩ በኋላ ነው። ወልቃይት ብዙ ስቃይ ይፈፀማል። በአማርኛችን እንኳ መዝፈን አንችልም። አስከሬን በወጉ መቅበር አንችልም። አሁንም በወልቃይት ጉዳይ እስር ቤት የሚገኙ አሉ። በወልቃይት ጉዳይ 9 ወጣቶች በቅርቡ ተከሰዋል። እኛ ትግሬ አንጠላም፣ እነሱ ግን አሁንም ያሳድዱናል። ለምን ያሳድዱናል? የወልቃይትን ጥያቄ ያነሳው ዲያስፖራ አይደለም። ዳያስፖራም ቢሆን ከባህር አሳ፣ ከኮንቴነር ሞት ተርፎ የተሰደደ ወገናችን ነው፣ ሲሞት አስከሬኑ ታሽጎ የሚላክልን ወገናችን ነው። ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱልም እንፈልጋለን። ነገር ግን እኛ በዳያስፖራ አንመራም” ሲል ለዶ/ር አብይ ቅሬታው አቅርበዋል።
ዶክተር አብይም ወደፊት ከኮሚቴዎቹ ጋር እንደሚወያዩ፣ መቀሌ የመለሱትም ጥያቄ ከማንነት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ሳይሆን አንድ ሰው “ዳያስፖራ እያፋጀን ነው” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጡት መልስ እንደሆነ ገልጸውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የወልቃይት ጉዳይ በእኔ በአንድ ሰው፣ በስብሰባ አዳራሽ የሚፈታ አይደለም” እንዳሉም ተዘግቧል።
ዶ/ር አብይ በወልቃይት ጉዳይ የሰጡት መልስ ከህወሃት አቋም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጭ ነው ተብሏል። ህወሃት የወልቃይት ጉዳይ ህገመንግስታዊ መልስ አግኝቷል በማለት ጥያቄው ዳግም እንዲነሳ እንደማይፈልግ ይታወቃል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው “የወልቃይት ጉዳይ ለምን ምላሽ አላገኘም? ጎንደር በኢንዱስትሪ መንደር አለመካተቱ ኢፍትሀዊ ነው፣ ጣና ሃይቅ በእንቦጭ ሲጠቃ የፌደራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ምን ሰራ?፣ በእስር ላይ የሚገኙ የደርግ ባለስልጣናት ጭምር ይቅር ተብለው ሊፈቱ ይገባል፣ የአማራ ክልል ከሱዳን ጋር ያለው ድንበር ችግር ስላለበት መፍትሄ ሊሰጠው ይገባዋል፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋታል ።ይህን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘው ሊፈፅሙት ይገባል፣ ከፍተኛ አመራሩ ህዝቡ ጋር ወርዶ መስራት አለበት እንዲሁም -የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአንድ ወገን ያደላ ሳይሆን ህዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ መሆን አለበት የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
የህዝቡን ጥያቄ የተቀበሉት ዶ/ር አብይ አያይዘውም ከሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ለሚታየው ችግር አፋጣኝ መልስ ለማግኘት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials