Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 2, 2018

ዝም የማንለው፤ ለነገ የማናሳድረው! – ጋዜጠኛ ወብሸት ታየ


   ይህችን አጭር ጽሁፍ ለወዳጆቼ ለማጋራት ያነሳሳኝ በዚሁ ማሕበራዊ ሚዲያ የተላከልኝ አንድ  መልዕክት(ጥያቄ) ነው። መልዕክቱ ወይም ጥያቄው በአጭሩ ከቤኒሻንጉል ክልል እየተሰደዱ ስላሉ የአማራ ተወላጆች ምነው ዝም አልክ? የሚል ነው።
ጥያቄውን ዝም ብሎ ማለፍ ወይም ለነገ ማሳደር በጣም አስቸጋሪ ነው። ከተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በዚህ ጉዳይ ላይ የተደራጀ መረጃና ትንታኔ ለመስጠትም ይቻለኛል ብዬም አላምንም። – አብረውኝ በእስር ላይ የቆዩ ወንድሞቼና እህቶቼ ሁኔታም ተመሳሳይ ይመስለኛል። እንዲህ ካልኩ በሁዋላ ግን አንድ ሶስት ነጥቦችን እንዳነሳ ይፈቀድልኝ።
 የመጀመርያው የአገራችን ሕዝብ ታሪክ በአብዛኛው የጭቆናና የመከራ በመሆኑ የጥቃቱ መገለጫ ወቅትና መጠን ይለያይ እንደሆነ እንጂ ያልተነካ ነበር ለማለት አይቻልም። የመፈናቀሉ እና በገዛ አገር ስደተኛ የመሆኑ፣ እንደሞኙ ከቀዬው ሞፈሩን ማስቆረጡ፣ በብሔር ማንነቱ መንቋሸሹ ወይም መገፋቱ ወይም መሸማቀቁ ያልዳሰሰው ኖሮ አያውቅም። በቅርቡ ተዘጋ በተባለው ማዕከላዊ ያለፍን የተለያየ የብሔር ዳራ ያለን የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ይኸው ንዑስ መገለጫችን እየተነሳ አስፀያፊ ዘለፋዎች ወርደውብናል። ፈልገን የአንዱ ወይ የሌላው ብሔር አባል የሆንን ይመስል አሁን መዘከር የማያስፈልጉ ብዙ ሰቆቃዎችን አልፈናል።
 ሁለተኛውና ወደተነሳንበት ነጥብ የሚመልሰን ጉዳይ እንደተባለው ከቤኒሻንጉል ክልልም ሆነ ከየትኛውም ክልል በብሔር ማንነታቸው ብቻ የሚፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በፍፁም ለነገ የማይባል፣ እኛ ሞልቶልንና የሞቀ ቤታችን ሆነን ትናንት ለጎደለው በሞቴ እያሉ ይደርሱ የነበሩ  ውዶቻችን በየመንገዱ ተሰጥተውና ከዜግነት ጥያቄ አልፎ ሰው የመሆን ህልውናቸው መደቃደቂያ ሆኖ ከቶም የህሊና ሰላም ሊኖረን አይችልም።
 በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ግን ለእነዚህና ስፍር ቁጥር ለሌላቸው አገራዊ ችግሮቻችን በአስቸኳይ ማድረግ የምንችለውን ሰብአዊ ድጋፍ እያደረግን ከዚህ እንደሕዝብ መጨረሻ የሌለው ቅርቃር ውስጥ ከገባንበት መቃተት በሚያወጡን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ስልቶች፣ አማራጮችና እስትራቴጂዎች ላይ የተጠናከረ፣ የተደራጀና ሳይንሳዊ መፍትሔዎች ላይ መረባረብ አለብን። በዜጎቻችን መፈናቀል ተቆጭተው በሙያቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው እየተረባረቡ ላሉት ሁሉም ያለኝን አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስባት፤ ሕዝቧን ይባርክ
Image may contain: 5 people

No comments:

Post a Comment

wanted officials