ኢትዮጵያ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ የተበደረችውን ብድር በወቅቱ ለመክፈል አቅሟ እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ በአጭር የክፍያ ጊዜና በከፍተኛ የወለድ መጠን የሚሰጡ ብድሮችን መበደር ማቆሟን የገንዘብ ሚኒስትሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል። አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች ተብሎ ቢታቀድም እቅዱ ሊሳካ አለመቻሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በአጭር ጊዜ የሚመለስ ብድሮችን ከምዕራባውያን ባንኮች፣ ከቻይናና ከሌሎችም አገሮች በከፍተኛ ወለድ ስትበደር ቆይታለች። እነዚህ ብድሮች ብዙዎቹ የመክፈያ ጊዜያቸው በመድረሱ አገሪቱ ለወለድና ለዋናው ብድር ክፍያ ከፍተኛ ወጪ እያወጣች ነው። አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያ የእዳ ጫና አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ፣ እጅግ ከፍተኛ የእዳ ጫና ካለባቸው አገሮች ተርታ የመደባት ሲሆን፣ መንግስት ብድር ለመውሰድ ያለውን ፍላጎት እንዲያጤነው መክሮ ነበር። ኢትዮጵያ በራሷ ፍላጎት የአጭር ጊዜ ብድሮችን መውሰድ ታቁም ወይም አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ለማበደር ፈቀደኛ ሳይሆኑ ይቅር የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ የቻይና ባንኮች ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ብድር ይመለሳል የሚል እምነት እያጡ በመምጣታቸው፣ በአሁኑ ሰአት ከዚህ በፊት ያደርጉት እንደነበረው ለኢትዮጵያ በቀላሉ ለማበደር ፍላጎታቸው እየቀነሰ ነው። ባለፉት 2 ዓመታት በአገሪቱ የታየው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቀቃሴ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞና በሌሎች ምክንያቶች ወደ አገሪቱ የሚልኩት ገንዘብ በመቀነሱ ለውጭ ምንዛሬው መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። የአገሪቱን ዋና ዋና የሚባሉ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በማሸሻቸው ለውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። በአገሪቱ የሚታዬው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያሳሰባቸው ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ በውጭ ባንኮች ገንዘብ ያስቀመጡ ባለስልጣኖቻቸውን አካውንት እንደሚያስመረምሩ፣ በዱባይና ሌሎችም አገራት ገንዘባቸውን ያስቀመጡ ባለሃብቶች ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመልሱ፣ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ገንዘብ ወደአገራቸው እንዲልኩና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው ነበር። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አዲሱ ጠ/ሚኒስትር መሰረታዊ የሆነ የፖለቲካ ለውጥ እስካላመጡ ድረስ የዶላር ተአቆቦ ጥሪያቸውን እንደሚያስቀጥሉ በመግለጽ ላይ ናቸው። የዶላር እጥረቱን ተከትሎ በርካታ ፋብሪካዎች ስራ በማይሰሩበት ደረጃ ደርሰዋል። ስርዓቱ አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ ራሱ ላወጣቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚያውል በመሆኑ፣ የግል ባላሀብቶች ዋነኛ ተጎጂዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። ብዙዎቹ እቃዎችን እንደ ልብ ለማስገባትና የጀመሩዋቸውን ግንባታዎች ለማስፈጸም እንደተቸገሩ ሲገልጹ፣ በስራ ላይ ያሉት እንዱስትሪዎች ደግሞ ሰራተኞችን እስከመ መቀነስ የሚደርስ እርምጃ እየወሰዱ ነው። ዶላር በጥቁር ገበያ እስከ 40 ብር እየተመነዘረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
No comments:
Post a Comment