Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, May 13, 2018

መንግስት ከሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ጋር ስላደረገው ድርድር መግለጫ ሰጠ



ከመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚ/ር የተሰጠ መግለጫ:
ራሱን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ብሎ ከሰየመው ግንባር ጋር ስለተካሄደው ውይይትና ድርድር ከመንግስት የተሰጠ መግለጫ፡፡
ይህች ሀገር የሁሉም ኢትዮጰየዊ የጋራ ቤት ናት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊም ይህችን ምትክ የሌላት ቤቱን ሰላሟን የመጠበቅ፣ ለብልጽግናዋ የመትጋት፣ ወደፊት ያራምዳታል ብሎ ያሰበውን አመለካከትም በግሉ እና በቡድን በመሆን የማራመድና ተከታዮችንም የማፍራት ህገመንግስታዊ እና እንደዜጋም ያለገደብ የሚጠቀምበት ሙሉ መብት እንዳለው ይታወቀል፡፡ ይህ ሁሉ ለሀገር እና ለወገን የሚበጅ ተግባር የምንጠብቀውን እና የምንናፍቀውን መልካም ውጤት ሊያስገኝልን የሚችለው በህግ እና በስርዓት ማእቀፍ ውስጥ ሲከናወን ብቻ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስትም የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም የአገራችንን ህገ-መንግስት ተቀብለውና በህጋዊ የመጫወቻ ሜዳ ላይ ሆነው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አቋማቸውን ማራመድ ከሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በየጊዜው ሲያሳውቅ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም መንግስት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሰረት ምንም እንኳን ከዚህ በፊት የተካሄዱት መሰል ውይይቶችና ድርድሮች ፍሬያማ ያልነበሩ ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ፖለቲካዊ አሰላለፉን ከኦነግ ከለየውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴፍ) በሚል ስያሜ ራሱን በመጥራት ከሚንቀሳቀሰው ግንባር ጋር ባካሄዱት ውይይትና ድርድር ድርጅቱ ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ አክብሮ፣ ህገ-መንግስቱን በማክበር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ የግንባሩ አቋም በመንግስት በኩል ከከፍተኛ አድናቆት ጋር ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አጠቃላይ ውይይቱ የተሳካ፣ ጥሩ አገራዊ መንፈስና መግባባትም የሰፈነበት ነበር፡፡ ይህንን በሰከነ፣ ሀገር እና ህዝብን ባስቀደመ እና በሰለጠነ መንገድ የሚደረግን ውይይት እና ድርድር መንግስት የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ ሰላማዊ በሆነ መስመር መታገልም ውጤታማ ያደርጋል ብለው ከሚያምኑ አካላት ጋር በቀጣይም ውይይትና ድርድር ለማድረግ በጽኑ ይፈልጋል- ለተግባራዊነቱም አበክሮ ይሰራል፡፡
የኦዴፍ ከፍተኛ አመራሮችም በቅርብ ቀናት አዲስ አበባ እንዲገቡም ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ቀሪዎቹ ውይይቶችም እዚሁ አዲስ አበባ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ ለወደፊቱም ህገመንግስቱን ባከበረ አና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሀገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመወያየት እና ለመደራደር መንግስት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡
ግንቦት 6/2010 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

wanted officials