ከዚያ በኋላ ‹እንደሥራቸው› ማን ናቸው? የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ጀመር፡፡ በተለያየ አጋጣሚ የደብረ ታቦርና የተክሌ አቋቋም ሊቃውንትን ባገኘሁ ቁጥር እኒህን ሊቅ በተመለከተ እጠይቃቸው ነበር፡፡ ሁሉም የሚመሰክሩልኝ ‹ከአለቃ ተክሌ በኋላ የመምህር እንደሥራቸውን ያህል አቋቋምን የሚያውቀው የለም› በማለት ነው፡፡ ዛሬ በቦታው የሚገኙት የደብረ ታቦር ኢየሱስ አለቃ መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፋንታሁንና የተክሌ ምስክሩ የኔታ መርሻ መምህር እንደሥራቸውን ሲያነሡ ዕንባ ይቀድማቸዋል፡፡ በምስክር ትምህርት ቤቱ ዛሬም ‹የእንደ ሥራቸው ዜማ› እየተባለ የእርሳቸው ስልት ይሰጣል፡፡ እንደ ብዙዎቹ የድጓና የአቋቋም ሊቃውንት አስተያየት ሊቁ እንደሥራቸው በዜማ ዕውቀታቸውና ስልታቸው ከተድባበ ማርያሞቹ አዛዥ ጌራና አዛዥ ራጉኤል፣ ከቤተ ልሔሙ እጨጌ ቃለ ዐዋዲ ጋር የሚተካከሉ ናቸው፡፡
ከአቶ አግማሴ መኮነንና ከወ/ሮ ሙሉነሽ ዓይናለም በ1939ዓ.ም. ሚያዚያ 23 ቀን በደብረ ታቦር አካባቢ ልዩ ስሙ ‹ሰላምኮ› በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ በዚህም የተነሣ አምኃ ጊዮርጊስ ተባሉ፡፡
ከአቶ አግማሴ መኮነንና ከወ/ሮ ሙሉነሽ ዓይናለም በ1939ዓ.ም. ሚያዚያ 23 ቀን በደብረ ታቦር አካባቢ ልዩ ስሙ ‹ሰላምኮ› በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ በዚህም የተነሣ አምኃ ጊዮርጊስ ተባሉ፡፡
በእናት አባታቸውና በዘመድ አዝማድ በጣም ብርቅና ድንቅ የሆኑ ልጅ ነበሩ፡፡ መጀመሪያ በአካባቢያቸው ከነበሩ መምህር አባ ባያፈርስ ከመምህር መርሻ ዓለሙ ጋር ከፊደል እስከ ፆመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ቀጥለዉም ፀዋትዎ ዜማ ከአለቃ ማኅተም ጌጤ፤ ቅኔ ወረታ አካባቢ ከሚገኙት መሪጌታ ጌቴ ተምረዋል፡፡ እንደገናም ከመምህር ጥበቡ ቅኔና ምሥጢር አደላድለዋል፡፡ የተክሌን አቋቋም ከአለቃ ማኅተም ጌጤ ካጠኑቁ በኋላ አዛወር ኪዳነ ምሕረት ከመሪጌታ ጀንበር ድጓን እንደ ገና ተምረውታል፡፡ ቀጥለውም ታች ጋይንት ከምትገኘው የኢትዮጵያ የድጓ ዩኒቨርሲቲ ቅድስት ቤተ ልሔም ገብተው ድጓን ከመምህር ጥበቡ አስመስከረው የድጓ መምህር ሆነዋል፡፡
ሊቁ እንደሥራቸው ድጓን አስመስክረው ከተመረቁ በኋላ በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምስክር ከሆኑት ከአለቃ ቀለመ ወርቅ ይማም የተክሌ ዝማሜን ጥሩ አድርገው ተምረው አስመስክረዋል፡፡ በቅድስት ቤተልሔም በዐቢይ ጾም ዝማሜ ይሰጥ የነበረው ለመምህር እንደሥራቸው እንደ ነበር የሚያስታዉሱ ሊቃውንት አሉ፡፡ መምህር እንደሥራቸው ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጸሎተ ሃይማኖትን በዝማሜ በሚዘምሩበት ጊዜ ንብ ከእጃቸው ላይ ያርፍባቸው እንደ ነበር የዓይን ምስክሮች ዛሬም በአድናቆት ይተርኩታል፡፡
ወደ ጎንደር ከተማ ከመጡ በኋላ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በጎንደር ለማንም የማይሰጠው የተክሌ ዝማሜ ለመምህር እንደሥራቸው ይሰጥ ነበር፡፡ ጎንደር በነበሩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ የታሪክ፣ የሂሳብና የዜማ መምህር በመሆን ሰፊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ፤ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ፤ ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤ መምህር የነበሩት፤ ክቡሩ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር እኒህን ሊቅ ሲያስታውሱ በቁጭት፣ በግርምትና በዕንባ ነው፡፡
ከዚህ አልፈው በጎንደር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና የአስተዳዳር ክፍል ሆነው ያገለገሉት ሊቁ እንደሥራቸው 2 ሴት ልጆችና 7 ወንድ ልጆች አሏቸው፡፡
እኒህ በጳጳሳቱ የተፈቀሩ፤ በሊቃውንቱ የተደነቁ፣ በካህናቱ የተወደዱና በምእመኑ የተናፈቁ ሊቅ ድንገት በሐምሌ 1986 ዓ.ም. የውኃ ሽታ ሆነው ጠፉ፡፡ ይህም የተክሌ ዝማሜ ሊቃውንትንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አስደነገጠ፡፡ አንዳንዶቹ መንነዋል ሲሉ አንዳንዶቹ ተሠውረዋል አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሞተዋል ሲሉ ደመደሙ፡፡
ቤተሰቡ፣ ወዳጆቻቸው፤ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ምእመናንና ታሪክና ኪነ ጥበብ ወዳጆች ሊቁን እንደሥራቸውን ፍለጋ አገሩን ማሰሥ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ እንዲህ ሆኖ ተገኘ፡፡
ሐምሌ 12 ቀን 1986 ዓ.ም. ሲሠሩበት ከነበረው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ቢሮ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሆኑ ሰዎች ይቀርቧቸውና ወደ መኪናቸው ያስገቧቸዋል፡፡ ከሌሎች የታፈኑ ሰዎች ጋር ጎንደር ራስ ግንብ ተብሎ ወደሚጠራው እሥር ቤት ይወሰዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ያያቸው የለም፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቻቸው ጭንቀት ውስጥ ወደቁ፡፡ ‹‹የእስር ቤቱ ጠባቂ ያውቃቸው ስለነበር፣ ማታ ማታ የታሠሩበትን ሰንሰለት ያላላላቸው ነበር፡፡ በቅዳጅ ወረቀት መታሠራቸውንና ከእርሳቸው ጋር የነበሩት እንደተገደሉ፣ ከእርሳቸው ላይ ሲደርስ ግድያ አቁሙ የሚል ትእዛዝ መድረሱን፣ ጠቅሰው መልእክት በእሥር ቤት ጠባቂው በኩል ለቤተሰብ ላኩ፡፡ በወቅቱም ባለቤታቸውና ትልቁ ልጃቸው ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ የሚሰማቸው አካል አጡ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ እንቆቅልሽ ሆኖ ቀረ› ይላሉ ታሪኩን የሚያውቁት የአካባቢው ሰዎችና ቤተ ዘመዶች፡፡
መምህር እንደሥራቸው ዛሬም በሕይወት በአንድ እሥር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ከእሥር ተፈትተው ለቤተሰቦቻቸው መረጃ የሰጡ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶችም በአካል ባያዩዋቸውም ዜማቸውን መስማታቸውን መስክረዋል፡፡ እነሆ ከተሠወሩ 24 ዓመት ሆነ፡፡ ሀገሪቱ ብዙ ዘመናትን አሳለፈች፡፡ አሳልፋም አይለቀቁም የተባሉ የፖለቲካ እሥረኞችንም ለቀቀች፡፡ እኒህ ሰው ቢፈረድባቸው እንኳን እስከ ዛሬ ሊፈቱ ይገባ ነበር፡፡ ሀገሪቱ ካለፉት ዘመናት ችግሮቿ ራሷን ለማላቀቅ በምትጥርበት በዚህ ዘመን ሊቁን መምህር እንደ ሥራቸውን ያሠረ አካል እንዲፈታቸው በልዑል እግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፡፡ በሕይወት መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እኒህን ሊቅ በዚህ ሁኔታ ጠፍተው እንዲሞቱ ማድረግ የተክሌ አቋቋምን መግደል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይም የሞት ፍርድ መፍረድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ መከራ መሸመት ነው፡፡ ምናልባት ያጠፉት ነገር አለ ቢባል እንኳን 24 ዓመት ከበቂ በላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው እንኳን የሚታሠረው 25 ዓመት ነው፡፡ ይህ ወቅት የይቅርታና ንስሐ ነው ይባላል፡፡ ይቅርታና መሻሻል ደግሞ ያለፉትን ስሕተቶች ከማረም ይጀምራል፡፡ አያሌ ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ‹ወደፊት የኔታ እንደ ሥራቸው ሲመጡ እንቀጽለዋለን› እያሉ ዛሬም በጉጉትና በጸሎት ይጠብቋቸዋል፡፡
ዳግማዊውን አለቃ ተክሌን መልሱልን፡፡
ዳግማዊውን አለቃ ተክሌን መልሱልን፡፡
(ዳንኤል ክብረት ጥሩ ፅፎ ሊቁ ትግራይ ውስጥ መታፈናቸውን እያወቀ “አንድ እስር ቤት” ብሎ አልፎታል። ጎንደር የታሰሩበትን ገልፆአል። የትግራዩን እስር ቤት በስም ሳይጠቅስ አልፎታል። ይህን ያህል ምን እንደሚያስፈራ ግራ ያጋባል። ሊቁ የሚማቅቁበትን፣ እኛ ለምን መግለፅ እንፈራለን?)
No comments:
Post a Comment