Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 30, 2018

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከረጅም እስር በኋላ ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር መገናኘቱ ለእንግሊዝ መንግስት ትልቅ ደስታ ነው

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር በመለቀቃቸው የእንግሊዙ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደስታቸውን ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን እንዳሉት የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ለእንግሊዝ መንግስት ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ ከእስር ለማስፈታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
እናም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከረጅም እስር በኋላ ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር መገናኘቱ ለእንግሊዝ መንግስት ትልቅ ደስታ ነው ብለዋል።
በአንዳርጋቸው ጽጌ መለቀቅ በርካታ ሰዎች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከየመን ታፍነው በኢትዮጵያ ደህንነቶች ከተወሰዱ በኋላ የእንግሊዝ መንግስት የእስር ርምጃውን በማውገዝ ከኢትዮጵያው አገዛዝ ጋር ሲወዛገብ ቆይቷል።
በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ በመጡ ቁጥር ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ ከሀገሪቱ አገዛዙ ባለስልጣናት ጋር መክረዋል፣ከፍተኛ ጫና ለማድረግም ሞክረዋል።
በኢትዮጵያ አገዛዝ ባላስልጣናት በኩል ግን የሕዝብ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነው የቆዩት።
እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ በመቀነስም ማድረግ የምትችለውን  ጥረት ሁሉ ማድረጓም ነው የሚታወቀው።
ሪፕሪቭ የተባለው የእንግሊዝ የሲቪክ ተቋምና የአቶ አንዳርጋቸው ቤተሰቦች እንዲሁም የሃገሪቱ የተወሰኑ ዜጎች የእንግሊዝ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲለቀቁ በቂ ግፊት አላደረገም በሚል ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር።
ጉዳዩ እየተጠናከረ ሲመጣም እንግሊዝ ከ2 ጊዜ በላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን እስከመላክም ደርሳለች።
ይህ ሁሉ ሆን በመጨረሻ የሕዝቡ ተቃውሞ ገፍቶ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ ከጀመሩ በኋላ አቶ አንዳርጋቸው የመለቀቅ ተስፋ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ቆይቷል።
እንደተገመተውም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ተለቀው ከቤተሰባቸው ጋር ለመገናኘት በመብቃታቸው የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
እናም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሒደት መነሻ በማድረግ አቶ አንዳርጋቸውን መልቀቁ የሚያበረታታ ርምጃ ነው ብለዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ባለመለቀቃቸው ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ መንግስት ልታገኝ የምትችለውን በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ማጣቷን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መግለጻቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials