የአፄ ዮሐንስ ማኅተም
ንቄ ያለፍኩትን ርእስ እንድመለስበት ኅሊናየ አስገደደኝ። ጉዳዩ የአፄ ዮሐንስን ማኅተም ይመለከታል። የምጽፈው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚጥረው ኤርትራዊው ተስፋየ ገብረአብ በአማርኛ በጻፈው መጽሐፉ ያደረገውን የታሪክ ማዛነፍ ለማቃናት፣ነው። በአማርኛ ሲጽፍ በኢትዮጵያ መኖር ኤርትራውያንንም እንደሚጠቅም ልብ ያላለው ይመስላል። ለመጽሐፉ የኢትዮጵያን ገበያ ባይፈልግ በአማርኛ አይጽፍም ነበር። ይኸንን አስፋፍቶ መተቸትን ለሌላ ጊዜ ላድርገውና፥ በአሁኑ መጽሐፉ ውስጥ ካሰፈራቸው እኩይ ትችቶች አንዱን ጠቅሼ ላስተባብል። እንዲህ ይላል፤
""አዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አጤ ዮሃንስ ራሳቸውን “የጽዮን ንጉስ” ብለው ይጠሩ ነበር። በማህተማቸው መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረ። የሸዋ መሳፍንት እንደሚያደርጉት ራሳቸውን ከሰሎሞናዊ ዘር ጋር የማቆራኘት ዝንባሌ ግን አልነበራቸውም። የአጤ ዮሃንስ የዘር ግንድ በቀጥታ ከአጤ ፋሲል ጋር የተያያዘ ነው። የፋሲል (የልጅ ልጅ - አምስተኛ ትውልድ የሆነችው) መና እስራኤል አያታቸው ናት። የአጤ ዮሃንስ ማህተም ላይ በአረብኛ የሰፈረው ጽሁፍ፣ “ንጉሰነገስት ዮሃንስ፣ ንጉሰ ጽዮን ዘኢትዮጵያ፣ ዘምነገደ እስማኤል” ይላል። “እስማኤል ማነው?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ አብርሃም አጋር ከተባለች ገረዱ ወለደው የተባለው ልጅ ስሙ እስማኤል ነበር።
የአቡነ ተክለሃይማኖት (ተክልዬ) የስጋ ዘመድ ይኩኖ አምላክ ዘሩን ቆጥሮና ተርትሮ ንጉስ ሰሎሞን ላይ ሲያደርስ፤ አጤ ዮሃንስ ደግሞ ተሸዋ ተረት ጋር ለመፎካከር በሚመስል መልኩ ከዚያም በላይ ርቀው የዘር ግንዳቸውን እስማኤል አብርሃም ላይ አደረሱት። አጤ ዮሃንስ ህጋዊ ሚስት ሃሊማ ሙስሊም ነበረች። አጤ ዮሃንስ ራሳቸውን ከአምላክ ጋር ለማገናኘት የእስማኤልን ሃረግ የተከተሉበት፣ ህጋዊ ሚስታቸውን ከሙስሊም ቤተሰብ የመረጡበት ስነ ልቦናዊ ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም። “ዘእምነገደ እስማኤል” የሚል ጽሁፍ የያዘውን የአጤ ዮሃንስን ማህተም ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ አስተውሎ ትርጓሜ የሰጠው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ነበር። ፍቅሬ ቶሎሳ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ ልቦለድ የሚቀላቅል ግዴለሽ ታሪክ ጸሃፊ ቢሆንም የማህተሙን ፎቶግራፍ ስላተመልን መረጃውን እንቀበለዋለን።""
አሁን ደግሞ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ አፄ ዮሐንስ ማኅተም ምን እንዳለ እንይ፤
""አጼ ዮሐንስ 4ተኛ ለአግአዚ-ሰሎሞናዊ ሐረጉ የሚጨነቅ አልነበረም። በዚህም ምክንያት እንደሌሎቹ አግአዚ-ሰሎሞናዊ ነገሥታት በማህተሙ ላይ “ድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ” የሚል ጽሁፍ አላስቀረፀም። ሆኖም ራሱን የጽዮን ንጉስ ብሎ ይጠራ ነበር፤ በማሕተሙ መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረው።
የአጼ ዮሐንስን ማሕተም ይመለከቷል፡ ማህተሙ የአረብኛ ጽሑፍ ነበረው። ጽሑፉ “ንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ዘ ኢትዮጵያ፥ ዘ አምነገደ እስማኢል” የሚል ነበር። “ዘ እምነገደ-እስማኢል” የሚለውን ጽሁፍ ሳይ ዐይኖቼን አላመንኩም ነበር። የገዛ ዐይኖቼን ተጠራጠርኳቸው። ሌሎች ሰዎች እንዲያነቡልኝ እስከመጠየቅም ደረስኩ። ሁሉም “ነገደ እስማኤል” እያሉ አነበቡልኝ። እስካሁን አልተዋጠልኝም። ዐይኖቸ ቢሳሳቱ እመርጣለሁ። አጼ ዮሐንስን የአረብ ዝርያ ያላቸው ይመስል በማህተማቸው ላይ ለምን “ነገደ እስማኤል” የሚል ጽሁፍ አስቀረጹ?""
ይህን ጥቅስ የፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደወጣ አይቼ ንቄ ትቸው ነበር። እንደ እውነተኛ ታሪክ እየተጠቀሰ ሲታይ ግን፥ ዝም ማለት ተገቢ አልመሰለኝም።
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከላይ የተቀስኩን ከጻፈ በኋላ፥ አንድ የማይነበብ የአጼ ዮሐንስ ማኅተም ፎቶግራፍ አንሥቶ ከመጸሐፉ ውስጥ አስገብቷል። ፎቶግራፉ ከወሰደበትና ከሌሎች ቦታዎች ስናየው የማኅተማቸው ጽሑፍ የሚለው እንዲህ ነው፤
"ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል።
(የጽዮን ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ፤ መስቀል እስላሞችን ድል ነሣ።)"
(የጽዮን ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ፤ መስቀል እስላሞችን ድል ነሣ።)"
ነገሥታቱ ሁሉ በማኅተማቸው ላይ የሚጽፉት የየራሳቸው ቃላት ነበሯቸው። የአፄ ቴዎድሮስ፥ “ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ይል ነበር፤ ተጨማሪ አርማ አልነበራቸውም። ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት የነገሡት ነገሥታት አርማቸው ምን እንደነበረ የሁሉም አይታወቅም። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት አርማ፥ “ነግሡ፡ በጽድቅ፡ አብርሃ፡ ወአጽብሐ፡ ነገሥተ፡ ጽዮን” (የጽዮን ንጉሦች አብርሃና አጽብሐ በትክክል ነገሡ) የሚል ነበረ።
“ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” (የይሁዳ ነገድ አንበሳ ድል ነሣ) የሚል አርማ የጀመሩት አፄ ምኒልክ ናቸው።
አፄ ዮሐንስ ራሳቸውን “ንጉሠ ጽዮን” ማለታቸውም አዲስ ነገር ወይም “አዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት” የሚባልም አይደለም። ከነገሡበት ዕለት ጀምሮ የሚጠሩበት የሹመት ስማቸው ነው። ከዚያ ቀጥሎ፥ አርማቸው፥ ከላይ እንደጠቀስኩት፥ “መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል” (መስቀል እስላሞችን ድል ነሣ) ይላል። ከእስላሞች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻካራ እንደነበረ የታወቀ ነው። ይህ አርማ ያንን ግንኙነት ያንጸባርቃል።
ራሳቸውን “ዘእምነገደ እስማኤል” ብለው ግን አያውቁም። አንበሳው የሚያመለክተው የነገደ ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሆነ፣ ራሳቸውን ከቀደሟቸው ነገሥታት በምንም ረገድ አልለዩም።
የአፄ ቴዎድሮስና የአፄ ዮሐንስ ማኅተም በተጨማሪ በዐረቢኛ “መሊክ አል-ሙሉክ አል-ሐበሻ” የሚል አለበት፤ “ንጉሠ ነገሥ ዘኢትዮጵያ” ማለት ነው።
Getatchew Haile
No comments:
Post a Comment