በግላቸውም ኾነ በመንግሥት ደረጃ፣ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታወቁ
አንዲትና ታላቅነቷ የተጠበቀ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የማየት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
“ለአንድነት ታሪካዊ ሚና ያላት ተቋም፣ራሷ መከፋፈሏ ለብሔራዊ ተግባቦቱ ተግዳሮት ነው፤”
“ልዩነቱ ምንም ቢኾን የማይፈታ አይደለም፤ችግር ፈቺዎቹ ከተቸገሩ ትልቁ ችግር እርሱ ነው፤”
“በጥረታችሁ ግፉበት፤ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ልዩነቱን ሥበሩና ለኛም አርኣያ ኹኑን፤”
“የልኡካን አባቶችን ስጋት የሚያስወግድና የሰላም ኮሚቴውን የሚያበረታታ ነው፤”/ታዛቢዎች/
†††
“ለአንድነት ታሪካዊ ሚና ያላት ተቋም፣ራሷ መከፋፈሏ ለብሔራዊ ተግባቦቱ ተግዳሮት ነው፤”
“ልዩነቱ ምንም ቢኾን የማይፈታ አይደለም፤ችግር ፈቺዎቹ ከተቸገሩ ትልቁ ችግር እርሱ ነው፤”
“በጥረታችሁ ግፉበት፤ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ልዩነቱን ሥበሩና ለኛም አርኣያ ኹኑን፤”
“የልኡካን አባቶችን ስጋት የሚያስወግድና የሰላም ኮሚቴውን የሚያበረታታ ነው፤”/ታዛቢዎች/
†††
በውጭ ሀገር በስደት በሚኖሩት አባቶች ከተቋቋመው ሲኖዶስ ጋራ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ጥረት መሳካት፣ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ኹሉ እንደሚሰጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሯቸው ሲኾን፤ ቅዱስነታቸውና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ አንድነት ለማስጠበቅ በጀመሩት የዕርቀ ሰላም ጥረት እንዲገፉበት አሳስበዋል፤ለሥምረቱም መንግሥታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
ለሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላት ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሲኖዶሳዊ አስተዳደሯ መከፋፈሏ በግላቸውም ቢኾን እንደሚያሳዝናቸው ያልሸሸጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አንዲትና ታላቅነቷ የተጠበቀ የተጠናከረች ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ማየት ፍላጎታቸው እንደኾነ ለቅዱስነታቸው ገልጸውላቸዋል፡፡
በሀገራችን ለግጭት መንሥኤ የኾኑ ልዩነቶችን በጋራ ለመፍታት እየተደረገ ባለው ጥረት፣ ለሀገራዊ አንድነት መጠበቅ ታሪካዊ ሚና ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷ በማዕከላዊ አስተዳደሯ ለሁለት መከፈሏ፣ ለብሔራዊ ተግባቦቱ ትልቅ ተግዳሮት በመኾኑ በተጀመረው የአባቶች ዕርቀ ሰላም ጥረት መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“ልዩነቶቹ በተለያየ ምክንያት ተከሥተው ሊኾን ይችላል፤ ነገር ግን ለመፍታት የማይቻሉ አይመስለኝም፤ ይቻላል፤ ሃይማኖታዊ ሰው ደግሞ አይደለም የውስጡንና የራሱን፣ የሌሎችንም ችግር መፍታት አይሳነውም ተብሎ ነው የሚታመነው፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም፣“የሌሎችን ችግር ይፈታሉ የተባሉት ችግር ፈቺዎቹ ራሳቸው ከተቸገሩና ሌላ ችግር ፈቺ ካስፈለጋቸው ትልቁ ችግር የሚኾነው እርሱ ነው፤” በማለት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ልዩነቷን ለማስወገድ በያዘችው ጥረት እንድትቀጥልበት አበረታታዋል – “እንደ ግልም እንደ መንግሥትም ከእኛ የሚፈለገውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ እናንተ ግን ግፉበት፤ ይህን ልዩነት በመሥበር ለእኛም አርኣያ ኹኑን፤”ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስለ ማበረታቻ ሐሳባቸውና አቋማቸው በማድነቅና በማመስገን፣ በውጭ ከሚኖሩት አባቶች ጋራ የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ስላደረጋቸው ጥረቶች አብራርተውላቸዋል፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባጠናቀቀው የግንቦቱ ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤውም፣በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የሰላምና አንድነት ኮሚቴ፣ ከቀድሞው በተሻለ አያያዝ ሒደቱን ለማስቀጠል ላቀረበው ጥያቄ ይኹንታውን በመስጠት የሚነጋገሩ ልኡካን አባቶች መሠየሙንም ነግረዋቸዋል፡፡
ትላንት ማምሻውን፣ ከአማራ ክልል የመጡና የባሕር ዳር ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ባደረጉት የራት ግብዣ ላይም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት፤ ለሀገር አንድነት ለመሥራት የሃይማኖት ተቋማት ውስጣዊ አንድነት ወሳኝ መኾኑን በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ መድኃኒቱ ራሱ ሲበከል መጥፎ በመኾኑ፣ ውስጣዊ ችግራቸውን በራሳቸው በመፍታት ለሀገራዊ ተግባቦት መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት በጋራ እንዲሰለፉ አሳስበዋል፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቁ አስተያየት ሰጭዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አስተዋፅኦ በመነሣት ለሲኖዶሳዊ አንድነቷ መጠበቅ ያሳዩት መቆርቆር እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ ጽ/ቤታቸው በመጥራት ማበረታታቸውም፣ ቢያንስ ሦስት ፋይዳዎች እንዳሉት አመልክተዋል፡፡ በመንግሥት እያመካኙ ወይም መንግሥት እንዲህ ሊያስብ ይችላል፤ እያሉ ወደ ኋላ የሚሉትንና በዕርቀ ሰላሙ ሒደት ላይ ሻጥር የሚፈጥሩትን የሀገር ቤት አካላት ያስታግሣል፤ የሚለው የመጀመሪያው ነው፤ በውጭ ባሉትም ዘንድ፣ “ዕርቀ ሰላሙን መንግሥት አይፈልገውም፤” የሚለውን ስጋታቸውን ያስወግዳል፤ ከዚህም ጋራ ተያይዞ፣ የዕርቀ ሰላም ሒደቱን በተሻለ አያያዝ ለማስቀጠልና ከዳር ለማድረስ ተነሣሽነቱን ለወሰዱ ሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የሰላምና አንድነት ኮሚቴ አባላት ጉልበት ይኾናቸዋል፡፡
የሀገር ቤቱ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሔደው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባው፥ ለዕርቀ ሰላሙ እንዲነጋገሩ፣ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሚመሩ ሦስት አባቶችን የሠየመ ሲኾን፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው የውጩ ሲኖዶስም፣ ከጥቅምት 22 እስከ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በኮለምበስ ኦሃዮ ባደረገው ጉባኤ፣ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ሦስት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ልኡክ ሠይሟል፤ “እግዚአብሔር ይጨመርበት፤ አምላከ አበው ሥራችሁን የተቃና ያድርግላችሁ፤” ሲልም ለሰላምና አንድነት ኮሚቴውቡራኬውን ሰጥቷል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ቅርንጫፎችን በማቋቋም የሚንቀሳቀሰው፣ሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ዓለም አቀፍ ኮሚቴ፣ ልኡካን አባቶች የሚገናኙበትንና ድርድሩ የሚካሔድበትን ቦታና ጊዜ በቅርቡ ለኹለቱም ወገኖች እንደሚያሳውቅ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Source: ሐራ ዘተዋሕዶ
No comments:
Post a Comment