ጎንደር የተጠራው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ለሁለተኛ ቀን ተደርጓል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። ወሃ ገዝቶ ለመጠጣት እንኳን አልተቻለም። በከተማዋ የጋሪ አገልግሎት በተከለከለ ቦታ ሳይቀር ስራ ላይ ውሏል። ባለጋሪዎቹ ለስራ የወጡት ለፈረሶቻቸው ቀለብ መግዣ ስለሚያስፈልጋቸው እንደሆነ ተነግሯል።
በጎንደር ከተማ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ መዋሉን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ አድማው ነገም እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ሰኞ ዕለት የስራ ማቆም አድማ የተካሄደባት ባህርዳር ከተማ ከትላንት አመሻሽ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሳለች ተብሏል፡፡
ከአድማው ጋር በተያያዘ ወጣቶች ታስረዋል ተብሏል
በአማራ ክልል ከሰኞ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ በማህበራዊ ድረገጾች መልዕክቶች መሰራጨታቸውን ተከትሎ በጎንደር ከተማ ትላንት የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በከተማይቱ የአገልግሎት ሰጪዎች ዛሬም ተዘግተው መዋላቸውን፣ ትራንስፖርትም እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ የንግድ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ተዘግተው መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ማጓጓዣዎች በመንገድ እንደማይታዩ የገለጹት እኚሁ ነዋሪ ባሉበት አካባቢ ያስተዋሉትን እንዲህ ይገልጹታል፡፡
“አሁን መሀል ከተማ ፒያሳ እምብርቱ ላይ ነው ያለሁት፡፡ መስቀል አደባባዩ ላይ ማለት ነው፡፡ ባለሁበት ቦታ የስራ ማቆም አድማው እንደቀጠለ ነው፡፡ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ሰዎች ጥግ ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ከፖሊሶች ጋር ተፋጠዋል፡፡ ሊከፍት ፍቃደኛ የሆነ ምንም ዓይነት ድርጅት የለም፡፡ የትራንስፖርት ሰጪ ነገሮች የሉም፡፡ ጋሪዎች ናቸው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ጋሪዎች ደግሞ ያው የዕለት ፍጆታቸውን፣ ለፈረሶቻቸው የሚሆን ምግብ ማግኘት ስላለባቸው፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ማለፍ በማይችሉባቸው አስፋልት መንገዶች ሁሉ እየተጓጓዙ ነው ያሉት” ይላሉ፡፡
ማንነታቸው እንዳይነገር የሚሹ ሌላኛው የጎንደር ነዋሪም ተመሳሳይ የትራንስፖርት ችግር በከተማይቱ አስተውለዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ከትላንት ጀምሮ ከአገልግሎት መታቀባቸውን ይገልጻሉ። የዛሬው የስራ ማቆም አድማ በጎንደር ከተማ በሞላ መተግበሩን ሶስተኛው የከተማይቱ ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች የስራ ማቆሙን አድማ ማን እንደጠራው በግልጽ እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ህብረተሰቡ እርስ በእርስ በመነጋገር መረጃውን እንደተቀባበለ ይስማማሉ፡፡ የስራ ማቆም አድማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም የተጠራ ነው በሚል በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም ሲሉ የመጀመሪያው ነዋሪ ያስተባብላሉ፡፡ ከአድማው በስተጀርባ ያሉ ጥያቄዎችንም ያብራራሉ፡፡
በጎንደር ዛሬ አድማ ቢኖርም ከተማይቱ ምንም ችግር አለመፈጠሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ አባላት በከተማይቱ በብዛት እንደሚታዩም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የከተማይቱ አስተዳደር ሰራተኞች ከትላንት ጀምሮ ስራ ባቋረጡ የንግድ ተቋማት እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ በቀይ ቀለም የኤክስ ምልክት ሲያደርጉ እንደተመለከቱም እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመንግስት መስሪያ ቤቶችም ስራ ያልገቡ ሰራተኞችን ስም እየዞሩ የሚመዘገቡ ሰዎች ነበሩ ባይ ናቸው፡፡ ከአድማው ጋር በተያያዘ ትላንት እና ዛሬ ወጣቶች እንደታሰሩም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ነዋሪዎች የስራ ማቆም አድማው ነገም እንደሚቀጥል መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡
በአድማው የመጀመሪያ ቀን ተሳትፋ የነበረችው የአማራ ክልል መቀመጫ ባህር ዳር ከትላንት ምማሻውን ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ተዘግተው እንደሚስተዋሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ጠቁሟል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ አንድ የከተማይቱ ስለ ባህር ዳር የትላንት እና ዛሬ ውሎ አብራርተዋል፡፡
የጎንደር የስራ ማቆም አድማን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ወደ ከተማይቱ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ብንደውልም የሚመለከታቸው አካላት ቀኑን ሙሉ ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተገልጾልናል፡፡ የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንንም በተመሳሳይ ምክንያት ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
ዝርዝር ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ፡፡
ተስፋለም ወልደየስ ሂሩት መለሰ
ቢቢሲ አማርኛ የሚከተለውን ዘግቧል
ብዙ ሁነቶችን ባስተናገደው ባለፈው ሳምንት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የመብት አቀንቃኞች በምህርትና በይቅርታ ተፈተዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንዲሁም ከፓርቲያቸው አመራር ኃላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡ ማግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ለብዙዎች አነጋጋሪ ሆኗል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን በይፋ ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስሜቶች እየተስተናገዱ ሲሆን፤ በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች በአፀፋው የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ 72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ በጎንደር ከተማ የስራ ማቆም አድማ የተነሳ ሰሆን የንግድ ቤቶች ተዘግተዋል እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል። የጎንደር ከተማ ፀጥ ረጭ እንዳለችም ጨምረው ተናግረዋል።
በተቃራኒው የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ክፍት እንደነበሩና አገልግሎትም ሲሰጡ እንደነበር ተነግሯል።
የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ላይ እንዳሰፈረው ትናንት ምሽት የከተማው ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በከተማው ውስጥ የስራ ማቆም አድማ በተለይም የንግድ ቤቶችን መዘጋትና ትራንስፖርት ማቆም እንዳለ አምነው ነገር ግን “ህገወጥ ስለሆነ ህዝቡ ሊቃወመው ይገባል” ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጎንደር ነዋሪዎችም ግልፅ በሆነ ሁኔታ ማን አድማውን እንደጠራው አልታወቀም ብለዋል። የከተማው ከንቲባ በበኩላቸው “ባለቤቱ ያልታወቀ አድማ” ብለውታል።
“ህዝቡ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቹን አሁንም በማቅረብ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ መስራት አለበት” ቢሉም ከንቲባው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሀገሪቱ ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ ካልተነሳ በአድማው እንደሚቀጥሉ እየገለፁ ነው ።
ትናንት አመሻሹ ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር የመፈታታቸውንም ዜና ተከትሎ በጎንደር ከተማ ደስታቸውን ለመግለፅ ብዙዎች እንደወጡ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በባህርዳር ከተማም ትናንት ጥዋት አካባቢ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የስራ ማቆም አድማ እንደነበርና የንግድ ቤቶችም መዘጋታቸውን ነዋሪዎች ገልፀዋል እንዲሁም በደብረ-ታቦር ከተማ መጠነኛ የሚባል የሥራ ማቆም አድማ እንደነበር መረዳት ተችሏል።
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ በጎንደር እንደቀጠለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል። የንግድ ቤቶች እንደተዘጉ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎትም ዛሬም እንደሌለ እየተናገሩ ነው። ትናንት ክፍት የነበሩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት አንዳንዶቹም ዝግ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።