የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሰፋፊ እርሻዎች ካበደረው 5.6 ቢሊየን ብር ውስጥ 3.6 ቢሊየን ብር የተበላሸ ብድር ሆኗል ሲል አረጋገጠ።
ልማት ባንኩ ለሰፋፊ እርሻዎች መቀበል የጀመረውን የብድር ጥያቄም ማቆሙን አስታውቋል።
በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ለተሰማሩበት የጋምቤላ የእርሻ ልማት የተሰጠው ብድር ከ63 በመቶ በላይ የተበላሸ ተብሎ የተሰረዘው ባለሀብቶቹ ተጠያቂ እንዳይሆኑ በሚል መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።
የኦክላንድ የምርምር ተቋም በጋምቤላ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከ70በመቶ በላይ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው ይላል።
ራሳቸው ባለሃብቶቹ በተወካያቸው አማካኝነት እንደተናገሩትም በአጋጣሚ የትግራይ ተወላጆች እንበዛለን ነው።
በአጋጣሚም ይሁን በእቅድ በጋምቤላና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰፋፊ እርሻዎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የአንድ አካባቢ ተወላጆች በበላይነት የተቆጣጠሩት ስለመሆኑ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ሳይቀር ምስክርነት የተሰጠው ሆኗል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ከ500 በላይ ለሚሆኑት ለእነዚህ ባለሀብቶች 5.6 ቢሊየን ብር ብድር መሰጠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁንና የተሰጠው ብድር ሳይመለስ የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንቱ ኪሳራ እንደገጠመው ተገለጿል።
በልማት ባንኩ የተደረገ አንድ ጥናት ላይ እንደተረጋገጠውም የእርሻ ኢንቨስትመንቱ ውድቀት ገጥሞታል።
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም በዋናነት ባለሃብቶቹ የወሰዱትን ብድር በቀጥታ ለእርሻ ተግባር ከማዋል ይልቅ ግዙፍ ህንጻዎችን በመስራት እያከራዩ መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ሾልከው ወተዋል።
የአገዛዙ ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው ከልማት ባንክ ከተወሰደው 5.6 ቢሊየን ብር ውስጥ 3.6ቱ ተበላሽቷል።
ማለትም ተበዳሪዎቹ የሚከፍሉት አይሆንም።
ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከ63በመቶ በላይ እንደሚሆን ያመለክታል።
ልማት ባንኩ ከእንግዲህ ለሰፋፊ እርሻ ስራ የብድር ጥያቄ ያቆመው ለአንድ መሬት ሁለት ባለሀብቶች ተመዝግበው ሁለቱም ብድር በመውሰዳቸው እንደሆነም በዘገባው ተገልጿል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ሲጠበቅ በህወሀት አገዛዝ ጫና ጉዳዩ ተመልሶ ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሄደበት ምክንያትም ብድር ወስደው ያልመለሱ ባለሀብቶችን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ እንደሆነ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በፖለቲካዊ ውሳኔ ያለመያዣ ብድር የሚሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መነሻ ካፒታሉን ከ30 በመቶ ወደ 10በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው ከ1ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወደ ልማት ባንክ እንዲዛወር ተደርጎ በኋላም የተበላሸ ብድር በሚል እንዲሰረዝ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ልማት ባንኩ ለኢፈርት እንዲሰረዝለት ካደረገው ብድር ሌላ በ2002 እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሰጠው 7.6 ቢሊየን ብር ብድር ውስጥ ኢፈርት 2.6 ቢሊየን መውሰዱን ለማወቅ ተችሏል።
በጋምቤላ የትግራይ ባለሀብቶች ለእርሻ ብለው የወሰዱትን ብድር በመቀሌና አዲስ አበባ ህንጻዎችን በመገንባትና ውድ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት እንደተጠቀሙበት ኢሳት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment