Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, January 3, 2018

በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በሁለት ቀናት ውስጥ ሊፈቱ ይችላሉ ተባለ





በታምሩ ጽጌ

ዜና፣ በቀለ ገርባ፣ መረራ ጉዲና፣ ኢሕአዴግ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤት

በምሕረትና የክስ ሂደታቸው ተቋርጦ ይፈታሉ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እስረኞች፣ ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ወይም ቅዳሜ ታኅሳስ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊፈቱ ይችላሉ ሲሉ የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ፍርደኛ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች የማረሚያ ቤት አስተዳደር ዝርዝራቸውን እንዲያቀርብ፣ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያሉትን ደግሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲያቀርብ መመሪያ መሰጠቱን ከምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዚህ መሠረት በመንግሥት ምሕረት ይደረግላቸዋል የተባሉ ፍርደኞችና ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች በቀናት ውስጥ ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ረቡዕ ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ሲባል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙና ጉዳያቸው በዓቃቤ ሕግ የተያዘ የፖለቲካ አመራሮችና ሌሎች ክሳቸው ተቋርጦ እንደሚለቀቁ መገለጹ ይታወሳል፡፡

የፖለቲካ አመራር ሆነው ፍርዳቸው በመታየት ላይ ካሉ ፖለቲከኞች መካከል ዶ/ር መረራ ጉዲናና አቶ በቀለ ገርባ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ተፈርዶባቸው በክስ ሒደት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃዎቹን ለዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲሰጣቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ባዘዘው መሠረት፣ ማስረጃው ለተከሳሹ ቢደርሳቸውም ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አስተያየት ሰምቶና ራሱም ሰነዶቹን ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ በማስረጃነት የቪዲዮ፣ የድምፅና የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ማስረጃዎቹ እንዲሰጣቸው ተከሳሹ በጠየቁት መሠረት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስረጃዎቹ ተሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለረቡዕ ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የተከሳሾቹን አስተያየት ለመስማትና ፍርድ ቤቱም ተመልክቶ ብይን መስጠት እንዲያስችለው ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በማስረጃዎቹ ላይ ያላቸውን አስተያየት በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ ተነግሯቸዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment

wanted officials