Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, January 10, 2018

በሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ 4 የህግ ታራሚዎች በፖሊስ በጥይት ተደብድበው መገደላቸው ተገለጸ።


(ኢሳት ዲሲ–ጥር 4/2010)
በሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ 4 የህግ ታራሚዎች በፖሊስ በጥይት ተደብድበው መገደላቸው ተገለጸ።
ፖሊስ ሊያመልጡ ሲሉ ነው የተገደሉት ይላል።
የሲዳማ ሀርነት ንቅናቄ በግፍ ተገድለዋል ሲል ለኢሳት ገልጿል።
የሲዳማ ወጣቶች መብታቸውን በመጠየቃቸው በጅምላ እየታፈሱ መሆኑም ተገልጿል።
በሌላ በኩል በሲዳማና በወላይታ ወሰን ላይ ግጭት ለመፍጠር በህወሃት አገዛዝ የሚደረገውን ቅስቀሳ ህዝቡ እንዲያከሽፈው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ጥሪ አድርጓል።
ግድያው የተፈጸመው ታህሳስ 30 ሰኞ ዕለት ነው።
የእስር ጊዜያቸውን የጨረሱ እስረኞች በህግ አግባብ ለመፈታት ሲጠይቁ የተሰጣቸው ምላሽ ጥይት ነው ይላሉ ኢሳት ያነጋገራቸው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ሚሊዮን ቶማቶ።
አራቱ እስረኞች የአመክሮ መብታቸው እንዲከበርላቸው በተደጋጋሚ ይጠይቁ እንደነበርም ታውቋል።
ሆኖም ከእስር ቤቱ አስተዳደር ምንም ምላሽ ሳይሰጣቸው ቆይተዋል።
ያለፈው ሰኞ እዚያው በእስር ቤቱ የተኩስ እሩምታ ይሰማ ነበር ያሉት የኢሳት ምንጮ በኋላ ላይ አራት እስረኞች ተገድለው መገኘታቸውም ታውቋል።
ከፖሊስ አካባቢ እየተሰጠ ያለው ምላሽ እስረኞቹ ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ የሚል ቢሆንም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ግን አይቀበለውም።
በግፍ የተገደሉ ዜጎች ናቸው ሲል አስታውቋል።
ጉዳዩ የህዝብ ቁጣ እንዳይቀሰቅስ እንዲደበቅ በአካባቢው ባለስልጣናት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል በሲዳማ ጥያቄ የሚያነሱ ወጣቶች በጅምላ እየታፈሱ መሆናቸውን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ አስታውቋል።
በተለይም ተምረው ተመርቀው ስራ ያጡ ወጣቶችን አመጽ ልታስነሱ ነው በሚል በጅምላ በመታፈስ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
ዶ/ር ሚሊዮን ቶማቶ ለኢሳት እንደገለጹት በቅርቡ ከወንዶ መልጌ፣ ቦና፣ በንሳና አርቤጎና ወረዳዎች በዲግሪና በሌሎች የትምህርት ደረጃዎች ተመርቀው ስራ በማጣት የተቀመጡ ወጣቶች ወደ አመጽ መግባታቸው አይቀርም በሚል ታፍሰው ተወስደዋል።
ለደኢህዴን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ገጽታ ታበላሻላችሁ ተብለው ከሀዋሳ ከተማ ከ500 በላይ የኔ ቢጤዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ወራት መቆጠሩን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሲዳማና በወላይታ ወሰን ላይ በአገዛዙ የተቀነባበረ የእርስ በእርስ ግጭት እየተቆሰቆሰ በመሆኑ ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ጥሪ አድርጓል።
የወሰን ይገባኛል ጥያቄው በሀገር ሽማግሌዎች ጭምር መፍትሄ በተሰጠበት ሁኔታ በየጊዜው የግጭት ምክንያት እንዲሆን መፈለጉን ንቅናቄው አውግዟል።
ለአገዛዙ የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ የሲዳማና የወላይታ ወንድማማች ህዝብ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ቅድሚያ በመስጠት የአገዛዙን ድብቅ አጀንዳ እንዲያከሽፈው ነው ሊቀመንበሩ ዶ/ር ሚሊዮን ቶማቶ የጠየቁት።

No comments:

Post a Comment

wanted officials