(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2010)
ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ሆነበት የተባለውና ሁለት ጊዜ የተመረቀው የጎንደር የውሃ ፕሮጀክት መቋረጡ ተገለጸ።
የህዝብ ቁጣ ይቀሰቀሳል በሚል ጉዳዩ በሚስጢር መያዙም ታውቋል።
በሌላ በኩል ጎንደርን ጨምሮ በአማራ ክልል በበርካታ ከተሞች የውሃና መብራት አገልግሎት መቋረጡ ታውቋል።
ከውሃና መብራት ሌላ ዘይትና ስኳር ከገበያ በመጥፋታቸው ህዝቡ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝ በደረሰን መረጃ ላይ ተመልክቷል።
የጎንደርን የውሃ ጥም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያረካል በሚል በአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን ሲነገር የነበረው፣ ሁለት ጊዜም የምርቃት ስነስርዓት የተደረገለትና 525 ሚሊዮን ብር የተመደበለት የጎንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ውሃ በልቶት ቀርቷል።
ኢሳት ያገኘው መረጃ ላይ እንደተመለከተው በ2007 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው።
ወቅቱ ደግሞ የህዝብ አመጽ የተቀጣጠለበት ሲሆን የአገዛዙ ዓላማ አመጹን ያበርዳል በሚል በችኮላ የታቀደ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
በሁለት ዓመት ውስጥ ያልቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ያለበቂ የአፈርና የመልከዐምድር ጥናት መካሄዱን ምንጮች ገልጸዋል።
ከቆላድባ አካባቢ ካለው መሬት ላይ ውሃ ላማውጣት የተጀመረው ፕሮጀክት አዘዞ መድረስ አቅቶት፡ ጎንደርን በሩቅ ትቶ መቆሙ ታውቋል።
ውሃው ወደላይ ከመውጣት ይልቅ ወደታች መሬት ውስጥ ሰርጎ የሚገባ መሆኑ የታወቀው ቁፋሮ ተካሂዶ ግንባታው ከተጋመሰ በኋላ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች ጉዳዩ የህዝብ ቁጣ እንዳያስነሳ በሚል እንዲደበቅ መወሰኑንም ገልጸዋል።
ጎንደር ውሃ ሳታገኝ የፕሮጀክቱ ምርቃት ሁለት ጊዜ የተከናወነ ሲሆን በክልሉ ማስሚዲያና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መተላለፉ ታውቋል።
የሃይል እጥረት በመግጠሙ የውሃ ስርጭቱ አልተጀመረም የሚል ምክንያት በመንግስት በኩል በመቅረብ ላይ ነው።
ይሁንና 525 ሚሊየን ብር የወጣበት የውሃ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ የከሸፈ መሆኑን ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የመብራትና የውሃ እጥረት በመከሰቱ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በጎንደር፣ ወረታ፣ ባህርዳር፣ ወልዲያና ደብረማርቆስ የተከሰተው የውሃና የመብራት እጥረት የህዝቡን የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ መክተቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይም በወረታ ከተማ የውሃ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ መሆኑ ታውቋል።
የወረታ ከተማ ነዋሪ ቁጣውን ለመግለጽ እየተዘጋጀ ሲሆን የአገዛዙ ታጣቂዎች የህዝቡን ተቃውሞ ለማፈን ከወዲሁ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በየከተማው የተከሰተውን የውሃና የመብራት እጥረት ለመቅረፍ በአገዛዙ በኩል ምንም ዓይነት ርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑም ታውቋል።
በአሁኑ ጊዜ የህወሀት አገዛዝ መሰረታዊ የሆኑ ፍጆታዎችንና አገልግሎቶችን ማቅረብ የተሳነው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚያ ይልቅ ብሶት የሚያሰማውን ህዝብ በሃይል ለማፈን የሰራዊትና የደህንነት አቅሙን በማጠናከሩ ላይ መጠመዱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ከውሃና መብራት ሌላ ዘይትና ስኳር ከገበያ መጥፋታቸውም ታውቋል።
ለቀላል ህክምና የሚሆኑ መድሃኒቶች ከመደብሮች በመጥፋታቸው በህሙማን ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑንም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚደርሱን መረጃዎች ላይ ተመልክቷል።
አገዛዙ ለመድሃኒት መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እያጠረው በመሆኑ በቀጣይ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ይነገራል።
No comments:
Post a Comment