በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ግምገማ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የተባረሩት አቶ አባይ ወልዱ ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነት ቦታቸውም በይፋ ተነሱ።
ሁለት የዞን አስተዳዳሪዎችም ከስልጣናቸው የተባረሩ ሲሆን የደህንነት ዋና ሃላፊው የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም ደግሞ የቢሮ ሃላፊ በመሆን ተሹመዋል።
በቅርቡ የሕወሃት ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የትግራይ ክልልን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውም ይፋ ሆኗል።
አቶ ደብረጺዮን ትግራይ ክልል በመመደባቸው በርሳቸው ምትክ የኢንፎርሜሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንደሚሾም ይጠበቃል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባል ያልሆኑት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የትግራይን ክልል በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተወሰነው ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚመረጥ ሰው የክልል ምክር ቤት አባል እንዲሆን ህግ ስለሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጿል።
የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው በየትኛውም ስያሜና ማዕረግ የአንድ ክልል መሪ መሆን ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ከወዲሁ እያነጋገረ ነው።
አቶ አባይ ወልዱን ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ያሰናበተው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ምክትላቸውን ዶክተር አዲስአለም ባሌማንም ዝቅ በማድረግ በካቢኔ አባላነት ብቻ ገድቧቸዋል።
የሰሜን ምዕራባዊ ትግራይ ዞን አስተዳደርን በማንሳት በምትካቸው አቶ ተክላይ ገብረመድህን የተባሉ ግለሰብ ሲሾሙ ለማዕከላዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪነት ደግሞ አቶ ማሞ ገብረእግዚአብሔር የተባሉ ግለሰብ ተሹመዋል።
የደህንነት ሃላፊው ጌታቸው አሰፋ ወንድም ዳንኤል አሰፋ የፋይናንስና እቅድ ቢሮ ሃላፊ ሆነዋል።
በአቶ ስብሃትና ቡድናቸው ይደገፋል የሚባለው አዲሱ የሕወሃት አመራር ከላይ የጀመረውን ብወዛ ወደ ወረዳና ቀበሌ ያወልዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነር ትግራይ/ህወሃት/ ከ2 ሺ የሚበልጡ ካድሬዎቹን በዚህ ሳምንት ለማወያየት በመቀሌ ስብሰባ የጠራ ሲሆን በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት የተደረሰበትን ውሳኔ በተመለከተም ማብራሪያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
እስረኞቹን የመፍታቱ ርምጃ የዘገየው በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ደጋፊዎች የተፈጠረውን ጫጫታ ተከትሎ እንደሆነም መረጃዎች ጠቁመዋል።
የመቀሌውን የካድሬዎች ስብሰባ ተከትሎም እስረኞቹ ይለቀቃሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ሆኖም ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ላለመፍታት የሕወሃት አመራር እያንገራገረ መሆኑንም ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment