Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, January 8, 2018

በግብጽና ሱዳን መካከል የተጀመረው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

በግብጽና ሱዳን መካከል የተጀመረው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 1/2010)
ሱዳን ደሴቷን ለቱርክ መስጠቷን ተከትሎ በግብጽና ሱዳን መካከል የተጀመረው ውዝግብ መቀጠሉ ተሰማ።
ግብጽ ወታደሮቿን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው የኤርትራ ድንበር ላይ ማስፈሯ የተገለጸ ሲሆን ሱዳንም ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።
ለግብጽና ሱዳን ውዝግብ መንስኤ የሆነው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሪስፕ ጣይብ ኤርዶጋን ባለፈው ታህሳስ በሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ መንግስታት መካከል የተደረገው ስምምነት ነው።
ሱዳን ነጻነቷን ካገኘችበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1956 ወዲህ ሱዳንን ሲጎበኙ የመጀመሪያው ናቸው የተባሉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ከሱዳን መንግስት ጋር በርካታ ስምምነቶችን ያደረጉ መሆናቸውም ታውቋል።
ለውዝግቡ መነሻ የሆነውም ሱአኪን የተባለችው የሱዳን ደሴት በጊዜያዊነት ለቱርክ መሰጠቷ ነው።
በስምምነቱ ቱርክ ደሴቷን ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ እንደተረከበች ቢገለጽም የግብጽና የሳውዳረቢያ መገናኛ ብዙሃን ግን ድርጊቱን በማውገዝ ደሴቷ ለቱርክ ወታደራዊ ሰፈር ልትሆን ነው ሲሉ ጽፈዋል።
በሳውዳረቢያ የሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ስምምነቱ የአረብ ሀገራትን ጸጥታ የሚጎዳ አይደለም በማለት አስተባብሏል።
ሆኖም ሱአካን ደሴት የሱዳን እንጂ የማንም አለመሆኑ ደግሞ ሊታወቅ ይገባል በማለት በገዛ መሬታችን ምን አገባቸው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ግብጽም ይህንን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ኤርትራ ወደሚገኘው የዩናይትድ አረብ ኤምሬት ጦር ሰፈር በመላክ ኤርትራ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ሰራዊቷን ማስፈሯ ተመልክቷል።
ግብጽ ሰራዊቷን ወደ ኤርትራ መላኳን ተከትሎ ሱዳን በካይሮ የሚገኙትን አምባሳደሯን የጠራች ሲሆን አንድ የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣን ግብጽን በመወንጀል መግለጫ ሰጥተዋል።
እኚህ የሱዳን የድንበር ቴክኒካል ኮሚቴ ሊቀመንበር አብዱላሂ አልሳዲቅ ግብጽ ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት እየወሰደችን ነው በማለትም ካይሮን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሱዳን አምባሳደሯን ከመጥራትና ድርጊቱን ከማውገዝ ባሻገር ከኤርትራ ጋር ያላትን ድንበር ሙሉ በሙሉ በመዝጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ድንበር አስጠግታለች።
ወትሮውንም አንደኛቸው የሌላኛውን ተቃዋሚ ይደግፋሉ በሚል የሚወነጃጀሉትን ግብጽና ሱዳንን የቱርክ በአካባቢው መከሰት ይበልጥ ውጥረት ውስጥ አስገብቷቸዋል።
የሱዳን ሱአኪን ደሴትን በስምምነትና በጊዜያዊነት የወሰደችው ቱርክ በየመን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሳውዲ ከሚመራው ሃይል ጋር እንደ ግብጽ ሁሉ በአጋርነት የቆመች ቢሆንም በመሀመድ ሙርሲ ላይ ተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በማውገዟ ከግብጽ ጋር ጤናማ ግንኙነት የላትም።
በግብጽ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት መሀአድ ሙርሲ በጄኔራል አብድል ፈታህ አልሲሲ በተመራ መፈንቅለ መንግስት ተባረው በወህኒ ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።
በታህሳስ ወር ላይ እየከረረ የመጣውን የግብጽና የሱዳን ውዝግብን ተከትሎ ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ የሚደረገው ድርድር ሱዳንን ባገለለ መልኩ እንዲሆን ኢትዮጵያን መጠየቋ የተዘገበ ቢሆንም ግብጽ አልጠየኩም ስትል አስተባብላለች።
ሱዳን በበኩሏ የሀገሪቱን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል ኢሚድ አልዲንን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲሆን ጄኔራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials