Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, January 6, 2018

ዳግማዊና ሳልሳዊ ማእከላዊ እንደማይኖር ማስተማመኛ የለም -ግርማ_ካሳ




እንግሊዞችና ፈረንሳዮች የመቶ አመት ጦርነት አድርገዋል። በዚያን ወቅት እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1937 ዓ.ም አንድ ግንባታ ይጀመራል።ፓሪስ ውስጥ ባስቲይ( Bastille) የሚባለው እስር ቤት። ብዙ እስረኞ የሚገረፉት፣ የሚሰቃዩትና ቶርቸር ይደረጉበት የነበረ እስር ቤት።በፈረንሳያዉያን አይምሮ ውስጥ ባስቲል/Bastille የስቃይ፣ የሰቆቃ ምልክት ነበር።

ከአራት መቶ አመታት በኋላ በ1789 በፈረንሳይ አብዮት ወቅት ህዝቡ በቀዳሚነት ያደረገው ነገር ቢኖር የባስቲይን እስር ቤት ማቃጠል ነበር። እንዳለ አወደሙት። አሁን እስር ቤቱ በነበረበት ቦታ አንድ ማስታወሻ ሃዉልት ተቀምጧል፡ የባስቲይ አደባባይ ተብሎ ይታወቃል። እንደዉም አምባገነናዊ የንጉሳዊ አገዛዝን የተወገደበት የፈረንሳይ አብዮት ቀን፣ አንዳንዴ የባስቲይ/ Bastille ቀን ተብሎም ይጠራል።

የአገራችን ባስቲይ/Bastille የሆነው፣ የማእከላዊ እስር ቤት ተዘግቶ ሙዚየም ይሆናል እየተባልን ነው። አቶ ሃይለማሪያም ማእከላዊ እንዲዘጋ የተወሰነው በደርግ ጊዜ በወህኒ ቤቱ የተፈጸመው ሰቆቃ በዜጎች አይሞሮ ውስጥ ጥሩ ስሜት ስለማይፈጥር እንደሆነ ነው የገለጹት። እስቲ አሁን በደርግ ጊዜ የነበረውን ስቃይ ማን ነው የሚያስታወሰው ? ከሆነስ ማእከላዊን ለመዝጋት 26 አመታት ለምን ተጠበቀ ? ምን አለ ቢያንስ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ሰዎቹ ቢናገሩ ?

ነገሩ ያለው ወዲህ ነው። ለ26 አመታት ማእከላዊ ከነጌታቸው አሰፋ መመሪያ በቀጥታ እየተሰጣቸው በዜጎች ከፍተኛ ሰቆቃና ግፍ የሚፈጸሙ የሰይጣን ቁራጮች የሚርመሰመሱበት ቦታ ነው። በደርግ ጊዜ ተፈጸመ ከተባለው ሰቆቃ አሥር እጥፍ በሕወሃት ነው በማእከላዊ ግፍ የተፈጸመው። ሌላው ቢቀር የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በማእከላዊ የደረሰባቸው ስቃይ በመገልጽ የጻፍቱን ደብዳቤዎችና እስረኞች(በተለይም ከአማራ ክልል የመጡ) በተለያዩ ጊዜ በፍርድ ቤት የተናገሩትን መጥቀስ ብቻ በቂ ነው።

እንደ ፓሪሱ ባስቲይ፣ ዉሳኔ ባያስተላለፉም፣ ማእከላዊ በሕዝብ መቃጠሉ ወደፊት የማይቀር ቢሆንም፣ እነአቶ ሃይለማሪያም ማእከላዊ እንዲዘጋ ዉሳኔ ማስተላለፋቸው የሚደገፍ ዉሳኔ ነው። ሆኖም ግን ስለ ደርግ ማንሳታቸው ፣ እስር ቤቱን ለመዝጋት ለወሰኑት መልካም ዉሳኔ ትንሽም ቢሆን ክሬዲት እንዳይሰጣቸው ነው ያደረገው።

ሌላው የማእከላዊ እስር ቤት መዘጋት በአዎንታዊነት የሚወሰድ ቢሆንም ቶርቸሩ፣ ሰቆቃው ፣ በእስረኞች ላይ የሚደረሰው ግፍ በሌሎች እስር ቤቶች የሚቀጥል ከሆነ ፣ ዳግማዊና ሳልሳዊ ማእከላዊዎች በሌላ ቦታ ካሉ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። ነው። ጉዳዩ ያለው ግንቡ፣ ጣሪያው፣ አጥሩ ላይ ሳይሆን ገራፊዎቹ፣ አሰቃዮቹና በደህንነት መስሪያ ቤት የተቀመጡ የሕወሃት አለቆቻቸው ናቸው። እነ ጌታቸው አሰፋ። እነዚህ ሰዎች አሁንም በሃላፊነታቸው ላይ ነው ያሉት። እነዚህ ሰዎች አሁንም ዜጎች በፈለጉ ጊዜ እንዳያስሩ፣ እንዳያፍኑ፣ እንዳይገርፉ፣ ቶርቸር እንዳያደረጉ የሚከለክላቸው ምንም አይነት የአሰራር ለዉጥ አላየንም። አሁንም ደህንነቱንና መከላከያዉን የሚቆጣጠሩት የፈለጉትን የሚያፈርሱና የሚነቅሉ ሕወሃቶች ናቸው።

ስለዚህ ማእከላዊ ተዘጋ በሚል ብዙም ባንፈነድቅ ጥሩ ነው። ማእከላዊን ማከለካዊ ያደረጉ ሰዎቹ በሕግ ተጠያቂ ካልሆኑና ካልተወገዱ፣ ሲሰሩት የነበረው ግፍ አይነት ግፎች ዳግም እንዳይሰራ አስተማማኝ የሕግ ዋስተና ካልተቀመጠ፣ የሚባለው ነገር ብሎ ዋጋ የለውም። መዘናጋት አያስፈለግም። ትግሉን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር አስፈላጊ ነው።

የባስቲይ እስር ቤት በሕዝብ ሲቃጠል የሚያሳይ አርት/ስዕል እና የባስቲይ እስር ቤት በነበረበት ቦታ አይ የተቀመጠው የባስቲይ ሃዉልት( Place de la Bastille)

No comments:

Post a Comment

wanted officials