(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2010)ጤና ለጣና በሚል እምቦጭ አረምን ለመከላከል በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ በአንድ ቀን ብቻ 140ሺ የአሜሪካን ዶላር ተሰበሰበ።
በዝግጅቱ ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።
በመድረኩ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያንና ኮመዲያን ተገኝተው ለዝግጅቱ ድምቀት ሰጥተውታል።
የዝግጅቱ አስተባባሪ አለም አቀፍ ትብብር የጣና መልሶ ማልማት ድርጅት ሰብሳቢ ዶክተር ሰለሞን ክብረት ጣናን ከጥፋት ለመታደግ የባለሙያዎች ቡድን የጥናትና የቴክኒክ እገዛ ማድረጉንና እምቦጭ አረሙን የሚያስወግድ መሳሪያ ወደ ስፍራው መላኩን ገልጸዋል።
እምቦጭ የተባለው መጤ አረም የጣና ሃይቅን ከፊል ገጽታ በመውረር የጥፋት አደጋ በመደቀኑ ብዙዎችን ያሳሰባ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።
በጣና ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው የጣና ሃይቅ ከ5 ሺህ ሔክታር በላይ ገጽታው በእንቦጭ አረም ተወሯል።
እምቦጭ አረሙን ማን እንዳመጣው በውል ባይታወቅም ሆን ተብሎ የተሰራጨ እንደሆነ የሚገምቱ ብዙ ናቸው።
አረሙ ከመስፋፋቱ በፊትስ ለምን በጊዜ መከላከል አልተቻለም በሚል የሚጠይቁም በርካታ መሆናቸው ነው የሚታወቀው።
እምቦጭ አረም ከተከሰተና ችግሩ ከታወቀ በኋላ የጣና ሃይቅ ተቆርቋሪዎች ሕዝብን በማስተባበር ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉም ቆይተዋል።
ከነዚሁ ጥረቶች መካከል በአሜሪካ የተቋቋመው አለምአቀፍ ትብብር የጣና መልሶ ልማት ድርጅት የተሰኘው ተቋም ከፍተኛ ስራ እያከናወነ ይገኛል።
የተቋሙ ሰብሳቢ ዶክተር ሰለሞን ክብረት ለኢሳት እንደገለጹት እምቦጭ አረምን ለመከላከል በ4 መንገዶች ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በዚሁ መነሻነትም የገንዘብ ማሰባሰብ ስራው ተጀምሮ በአትላንታ ብቻ ከ67ሺ ዶላር በላይ ተሰብስቦ እምቦጭ አረምን የሚከላከል የማጨጃ ማሽን በ68 ሺ ዶላር ተገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን አስታውቀዋል።
ከዚህ በመቀጠልም የጣናን ሕልውና በአስተማማኝ ደረጃ ለመጠበቅ ጥረቱ ቀጥሎ ትላንት በዋሽንግተን ዲሲ የገቢ ማሰባሰቢያ ተካሂዷል።
በዚሁም ከ1ሺ 5 መቶ የማያንሱ የጣና ሃይቅ ተቆርቋሪዎች ተገኝተው በአንድ ቀን ብቻ 140ሺ ዶላር አሰባስበዋል።
በዝግጅቱ ታዋቂውን ድምጻዊ መሃመድ አህሙድን ጨምሮ በርካታ የኪነጥበብ ሰዎች እንዲሁም ኮመዲያን ተገኝተው ዝግጅቱን አድምቀውታል።
በዝግጅቱ አስተባባሪነት ጣይቱ የትምህርትና የባህል ማዕከል፣ ጎጃም አሊያንስና ርዮት የተባሉ ተቋማት መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በዝግጅቱ ከተሳተፉ የአካባቢው ተቆርቋሪዎች መካከል ወይዘሮ አቢ ታደሰ ስለ ጣና ያላትን ትዝታ በማውሳት ሃይቁን ለመታደግ በዝግጅቱ ላይ መገኘቷን ገልጻለች።
ጤና ለጣና በተሰኘው መድረክ የጣና ችግርን ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለውን ችግር ለመፍታት ሁላችንም የዜግነታችንን እንወጣለን ሲሉም የመድረኩ ተሳታፊዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment