በግሪክ አቴንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ገዳም ቤተ ክርስቲያን
ጉዳያችን / Gudayachn
መጋቢት 15/2010 ዓም (ማርች 24/2018)
መጋቢት 15/2010 ዓም (ማርች 24/2018)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሃገራት ያላት ይዞታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።በያዝነው 2010 ዓም በአውሮፓ ብቻ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአራት ሀገሮች ውስጥ የራሷ ይዞታ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን ገዝታለች።እነርሱም በእንግሊዝ፣ለንደን የደብረ ገነት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ በኦስሎ፣ኖርዌይ የቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣በጀርመን ፍራንክፈርት የመድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲሆኑ በእዚህ ዜና ላይ ትኩረት የሚደረግበት አዲሱ ገዳም ደግሞ በግሪክ አቴንስ ከስድስት ሺህ ካሬ በላይ ስፋት ያለው ገዳም ነው።
በጥንታዊቷ ግሪክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ገዳም የመሬቱ ስፋት ብቻ ሳይሆን ግቢውን አልፎ የሚሄድ ክረምት ከበጋ የሚፈስ ወንዝ ፣ባለ አንድ ፎቅ ሰፊ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን፣የዘንባባ እና የወይራ ዛፎች ያሉት ሲሆን የወይራ ዘይት ለማምረት የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው። ክረምት ከበጋ የሚፈሰው ወንዝ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የገዳሙ ይዞታ የመስኖ ልማት ለማልማት የሚያስችለው ነው። ገዳሙ የተገዛበት ቦታ ከአቴንስ ዋና ከተማ ወደ አየር መንገዱ ወጣ ያለ በመሆኑ ፍፁም የሆነ ፀጥታ የሰፈነበት እና ለፀሎትም ሆነ ለአርምሞ የተመቸ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ገዳሙ በቂ የእንግዶች ማረፍያ ክፍሎች እና ሽንት ቤት ስላለው ለሱባኤ የሚመጡ ምእመናንን ወደፊት የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ይታሰባል።
ከሀገር ውጭ ገዳማትን በመግዛት የሚታወቁት የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአውሮፓ፣አሜሪካ እና አውስትራልያ ገዳማት እየገዙ እንደሚያለሙ ይታወቃል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሚልዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ይዛ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ማስፋፋት ላይ እንጂ ገዳማትን መገደም ላይ ብዙ እንዳልሰራችበት ይታወቃል። የገዳማት መኖር ግን ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።የመጀመርያ ጥቅሙ ለመንፈሳዊ ሕይወት ነው።ሁከት በመላበት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ምዕመናን አእምሮ የሚያረጋጋ፣አርምሞ የተሞላበት ህሊና የሚሰበሰብበት ገዳማት ሄደው ከአምላካቸው ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ።ሆኖም ግን ገዳማት ባለመኖራቸው ይቸገራሉ።
በክረምት ወር የሚጨምረው በበጋ ወቅት የማይደርገው በገዳሙ መሃል የሚያልፈው ወንዝ
ሁለተኛው ጥቅም ካህናትን ለማሰልጠን ይረዳል።ይሄውም ኢትዮጵያዊም ሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችን ስልጠና ለመስጠት ገዳማት ያስፈልጋሉ።ሶስተኛው በውጭ ለተወለደው ትውልድ ገዳማት ማለት ብዙ ነገር ናቸው።በገዳማት የአጭር ጊዜ ስልጠና በውጭ ለተወለዱ ወጣቶች መስጠት ይቻላል።በውጭ የተወለዱ ወጣቶች በእረፍት ሰዓት የአጭር ጊዜ ስልጠና ለመስጠት ለተወሰኑ ቀናት ገዳማቱ ውስጥ እያደሩ ማስተማር እና ለአገልግሎት ማብቃት ይቻላል።ከእዚህ ውጭ ማንነታቸውን የሚረዱበት አይነተኛ ቦታም ገዳማት ናቸው።በውጭ ከተወለዱት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ወደ ውጭ ሀገር ዜጎች አገልግሎቷን ለማድረስ የገዳማት ሚና ቀላል አይደለም።ይህ እንግዲህ ከመንፈሳዊ ጥቅሞቹ ሁሉ ጋር ነው።
የግብፅ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ካሏት ገዳማት ውስጥ ጀርመን ከፍራንክፈርት የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ ርቀት የሚገኘው የአቡነ እንጦስ ገዳም ተጠቃሽ ነው። የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እንደተመለከተው ይህ ገዳም ከሃምሳ በላይ ሰዎች ሊያሳድር የሚችሉ ከመታጠብያ እና መመገብያ አዳራሽ ጋር የተሟሉ የመኝታ ክፍሎች፣ እራሱን የቻለ ዘመናዊ የመሰብሰብያ አዳራሽ፣እና ሰፊ ቤተ ክርስቲያን የያዘ ነው። በእዚህም ግብፃውያን ብቻ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን ጭምር በነፃ ያስተናግዱበታል።
የገዳሙ የውስጥ ክፍል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሰረት እየተሰራ ያለ
በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምትገባው ለረጅም ዓመታት በአቴንስ ከተማ አገልግሎት በመስጠት ላይ የምትገኘው የመክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ሕግ ሲሆን ታቦቱ በአቡነ ኤልያስ ከዓመታት በፊት በአቴንስ ከተማ የተተከለ ነው።የግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ በአቡነ ተክለሃይማኖት ፕትርክና ወቅት አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እና አቡነ ኤልያስ የቲዎሎጂ ትምህርት የተማሩባት ከተማ ነች።ይህች ታቦት ነች ወደ አዲስ ወደተገዛው ገዳም የምትሄደው።
ይህ በግሪክ አቴንስ የተገዛው የቤተ ክርስቲያን ቦታ እና ህንፃ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 ዓም የተገዛ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቀላል የውስጥ እድሳት ወይንም የቀለም መቀባት ሥራ እየተደረገለት እና በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በነፃ እያገለገሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያኑን በማገልገል ላይ ያሉት አባ ወልደ ሚካኤል እና አባ ናሁ ሰናይ በምዕመናን የሚወደዱ እና ምዕመናኑን በማስተባበር የገዳሙ ግዥ እንዲፈፀም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ምዕመናን ይናገራሉ። የአዲሱ ቤተ ክርስቲያን እድሳት እንደተጠናቀቀ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሀገር ቤት መጥተው ቡራኬ እንዲያደርጉ መልዕክት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደላከች እና (ይህንን ዜና ጉዳያችን እስካጠናከረችበት ያለፈው የካቲት ወር 2010 ዓም የመጀመርያ ሳምንት ድረስ)ቤተ ክርስቲያን ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። እዚህ ላይ ጉዳያችን እንደተረዳችው የምእመናን እና የአባቶች አገልግሎት በተሳካ መንገድ የቤተ ክርስቲያን ግዥ ቢፈፅሙም ከቤተ ክህነት በኩል ተገቢው ድጋፍ እና በተለይ ቤተ ክርስቲያኑን በገዳምነት የመገደም እና የመባረክ አገልግሎቱን በማቀላጠፍ በኩል ከአገልጋይ አባቶች አይሰማ እንጂ ዘገምተኛ ምላሽ እንዳለ ግን አንዳንድ ምዕመናን ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል። በአቡነ ማትያስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ትልቅ ትኩረት የሚሻ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ በሁሉም መልክ ማገዝ ሲገባ የተሰጠው ትኩረት ግን ምዕመናን እና በቦታው ያሉት ካህናት ያላቸውን ትጋት ልክ አለመሆኑን ጉዳያችን በቦታው በምዕመናን ዙርያ የሚሰማውን ቅሬታ ለማዳመጥ ችላለች።በመሆኑም ይህንኑ ጉዳይ ለአባቶች በማድረስ እና አገልጋይ ሰባክያንም ምዕመናኑን በማፅናት በኩል ትኩረት እንዲያደርጉ በእዚህ አጋጣሚ ጉዳያችን ታሳስባለች።
በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ይህ ቀደም ብሎም በግሪክ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት አያፎሎፊ በተሰኘች ቅድስት ስም የሚጠራ የሴቶች ገዳም በአውሮፓ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንዱ መዳረሻ የፀሎት እና የሱባኤ ቦታ እንደሚሆን ይታመናል።በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት፣መረዳዳት እና መተሳሰብ በሌሎች ቦታዎች ከሚታዩት የተለየ ነው። በስደት ከሊብያ፣ከቱርክ እና ከአረብ ሀገሮች የመጡ በርካታ ወጣቶች በስደት እና በመሸጋገርያነት የሚጠቀሙባት ግሪክ ሥራ ያላቸው ወጣቶች ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች ቤት ተከራይተው ሙሉ የምግብ ውጪያቸውን እየቻሉ የሚያደርጉት መረዳዳት ክርስትና እና ኢትዮጵያዊነት በትክክል የሚንፀባረቅባቸው ወጣቶች መሆናቸውን አስመስክረዋል።የእዚህ ዜና አቅራቢ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚያገለግሉ ወጣቶች ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እጅግ አስደማሚ ቃላትን ሰምቷል። ለምሳሌ አንድ መንፈሳዊ መርሃ ግብር ላይ የተሰበሰቡ ወንድ ወጣቶች እንባ እየተናነቃቸው እየተቀባበሉ የተናገሩትን ላስፍር እና ዜናውን ላተናቅ።የወጣቶቹ ንግግር እንዴት ወጣቶች ተሳስበው እንደሚኖሩ ስለሚያሳይ የወጣቶቹን ንግግር በአንድ ላይ በመጠቅለል እንዲህ አቀርበዋለሁ።
“ እኛ እዚህ ሀገር ከወገኖቻችን ያገኘአው ደግነት በእውነት ክርስትና ምን እንደሆነ የተረዳንበት ነው።አውደ ምህረት ላይ ከምንማረው ባላነሰ ወንጌል የተማርነው ሥራ ካላቸው እህቶቻችን ነው።እዚህ ሀገር እንደምታውቁት ሥራ ብዙ ያለው ለሴቶች ነው ወንዶች የለንም።ሴቶቹ ግን ተሰባስበው እዚህ ለምታዩን ወጣቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቤተ ተከራይተው ክራያችንን እየከፈሉ ፍርጅ አንድ ቀን ሳይጎድል አንድ ላይ እያዋጡ ሞልተውልን ይሄዳሉ።እዚህ ማንም ስደተኛ ቤት ውስጥ ያድራል።ከእዚህ ወደ ሌላ ሀገር ሲሄድም ይህንን ቤት አይረሳም ደብዳቤ እየፃፉ እስካሁን ሰላም የሚሉን የሚረዱን አሉ።በእየዕለቱ ፀሎት አለን።ትምህርት እንማማራለን።ባለን ጊዜ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንም እናገለግላለን።ዛሬ ሰው እንድንሆን የረዱን እህቶቻችንን በጣም እናመሰግናለን እግዚአብሔር ዋጋቸውን ይክፈላቸው።ቤተ ክርስቲያናችንን እንድንወድ አድርገውናል።‘
”
“ እኛ እዚህ ሀገር ከወገኖቻችን ያገኘአው ደግነት በእውነት ክርስትና ምን እንደሆነ የተረዳንበት ነው።አውደ ምህረት ላይ ከምንማረው ባላነሰ ወንጌል የተማርነው ሥራ ካላቸው እህቶቻችን ነው።እዚህ ሀገር እንደምታውቁት ሥራ ብዙ ያለው ለሴቶች ነው ወንዶች የለንም።ሴቶቹ ግን ተሰባስበው እዚህ ለምታዩን ወጣቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቤተ ተከራይተው ክራያችንን እየከፈሉ ፍርጅ አንድ ቀን ሳይጎድል አንድ ላይ እያዋጡ ሞልተውልን ይሄዳሉ።እዚህ ማንም ስደተኛ ቤት ውስጥ ያድራል።ከእዚህ ወደ ሌላ ሀገር ሲሄድም ይህንን ቤት አይረሳም ደብዳቤ እየፃፉ እስካሁን ሰላም የሚሉን የሚረዱን አሉ።በእየዕለቱ ፀሎት አለን።ትምህርት እንማማራለን።ባለን ጊዜ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንም እናገለግላለን።ዛሬ ሰው እንድንሆን የረዱን እህቶቻችንን በጣም እናመሰግናለን እግዚአብሔር ዋጋቸውን ይክፈላቸው።ቤተ ክርስቲያናችንን እንድንወድ አድርገውናል።‘
”
የገዳሙ ግቢ መግቢያ ውጭያዊ ክፍልም የገዳሙ ይዞታ ነው
በመጨረሻም ለማጠቃለል ግሪክ የአዲሱ ትውልድ የእርስ በርስ መረዳዳት እና የእውነተኛ ኢትዮጵያዊ መልክ የሚታይበት ቦታ ነው።ቤተ ክህነት በሙስና እና በጎሳ ያልተማከለ አገልግሎቱን ለእዚህ ገዳም መስጠት አገልጋይ ሰባክያን ለወጣቶቹ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል በማለት ይህንን ዘገባ እደመድማለሁ።
ጉዳያችን GUDAYACHN
No comments:
Post a Comment