ከአንድነት ፓርቲ ጋር የሚደረገው ውህደት…” አቶ አበባው መሐሪ (የመኢአድ ፕሬዝደንት ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ)
መጋቢት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መካከል የነበረው የቅድመ ፓርቲዎች ውህደት ሳይፈጸም ቀርቷል። ሁለቱም ፓርቲዎች አንዱ አንዱን እየከሰሱ ይገኛሉ።
በተለይ አንድነት በአመራሩ በኩል ከመድረክ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መግለፁ ለውዝግቡ መፈጠር በአይነተኛ ምክንያትነት ይጠቀሳል። መኢአድ በበኩሉ በብሔር ከተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንደሌለው ከበፊቶቹ አመራሮች እስከ አሁን ፓርቲውን ከሚመሩ አመራሮች ጭምር ወጥ አቋም ሲያንፀባርቁ ይሰተዋላል። ከዚህ መነሻነት ከአንድነት ፓርቲ ጋር ውህደት ለመፈጸም የጀመሩት ጉዞ በአንዳንድ የአንድነት አመራሮች ተጨናግፏል በማለት መግለጫ አውጥቷል። እኛም ይህን የውህደት ልዩነት ከግምት በመውሰድ የመኢአድ ፕሬዝደነት የሆኑትን አቶ አበባው መሐሪን አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ድርድሩ ለምን በተፈለገው ፍጥነት አልሄደም? ለድርድሩስ አለመሳካት በመሰረታዊነት የሚያነሷቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው?
አቶ አበባው፡-በመጀመሪያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ የምፈልገው ድርድሩ አሁን በያዘው ቅርጽ ይሄዳል የሚል እምነት አልነበረንም። ሁሉም ነገር በቀና መንገድ ይጓዛል የሚል ጤናማ አመለካከት ይዘን ነበር ወደ ድርድሩ የገባነው። ሆኖም በእኛ ቀናነት ብቻ የሚሆን ነገር ባለመሆኑ ውህደቱ አለመሳካቱን ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል የሚል እምነት አለን።
ለድርድሩ አለመሳካት ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ማስቀመጥ ተገቢ ነው። አንደኛው፤ አንድነት ፓርቲ ከመድረክ ጋር በግንባር ለመስራት ፈቃድ የወሰደው ከምርጫ ቦርድ ነው። ይሄውም ከሌሎች ሶስት ፓርቲዎች ጋር በጋራ በምርጫ ሕጉ መሰረት ለመስራት አመልክተው ተፈቅዶላቸው እየሰሩ የሚገኙበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፈጸም አንድነት ከመድረክ የግንባር አደረጃጀት መልቀቅ ይጠበቅበታል። አንድነት ከመድረክ መውጣት እስካልቻለ ድረስ ሕዝቡም እንደሚያውቀው ከመኢአድ ጋር መዋሃድ አይችልም። ምክንያቱም መኢአድ ከመድረክ ጋር ያለው ልዩነት ግልፅ በመሆኑ ነው። በእኛ በኩል ። አያይዘንም ከእኛ ጋር ውህደት ከፈጸሙ፣ ከመድረክ ጋር በጋራ ሊሰሩ እንደማይችሉ አቋማችንን ግልጽ አድርገናል። እነሱም እንደሚገነዘቡት ውህደት ፈጽመን ወደ መድረክ በጋራ ልንሄድበት የምንችልበት አንዳችም ውለታ የለንም። ይህን መስመር ሊያጠራ የሚችል በአንድነት በኩል የቀረበ ማስረጃ የለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ በጥድፊያ የቅድመ ፓርቲ ውህደት ፊርማ የምናኖርበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ገልጸንላቸዋል።
ሁለተኛው ነጥብ፤ በውህዱ ፓርቲ ውስጥ አስራ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ ቦታዎች ላይ እኩል ሃምሳ ሃምሳ ቦታ ይኑረን ብለናል። መኢአድ መዋቅራዊ አደረጃጀትና ስፋቱ የተሻለ መሆኑ ሁሉም ቢያውቀውም በመርህ ደረጃ ይህን ጥያቄ አቅርበናል። ሌላው፣ ለሊቀመንበሩ ቦታ ግልፅ መስፈርት ይውጣለት ለሚለውም ጥያቄ በምንም መልኩ መስፈርት ሊወጣ አይችልም የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን። በአጠቃላይ ሲታይ የድርድሩ ነጥቦቹ በግልፅ ሳይቀመጡ እና ውይይት ሳይደረግባቸው እንፈራረም ነው የሚሉት።ይህን መሰል አካሄድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከዚህ በፊት ብዙ ተሞክሮዎች ስላሉ አልተቀበልነውም። ተመሳሳይ ስህተትም ለመፈጸም ዝግጁ አይደለንም።
ሰንደቅ፡- በውህደቱ ላይ የጊዜ ጥያቄ ብቻ ነው ያላችሁ?
አቶ አበባው፡- የጊዜም የሕግም ጥያቄ ነው ያቀረብነው። ጊዜ ለምትለው በአንድነት በኩል እነአቶ ብሩ ቢያንስ የቅድመ ፓርቲው ፊርማ ለመጋቢት 18 ይሁን የሚል መቃወሚያ አቅርበው ነበር። ኢንጂነር ግዛቸው ፈጽሞ አይሆንም የሚል ምላሽ አቅርበው በግድ ለመጋቢት 11 ነው የሆነው። መሰረታዊ ነጥቡ ግን አንድነት በመድረክ ላይ የሚከተለው ግልፅ ያልሆነ አካሄድ ነው። የሚገርመው የተፈጠሩትን ችግሮች ለመመልከት ከሥራ አስፈፃሚዎች መካከል አቶ ካሳሁን አበባ፣ አቶ ሲራክ አጥናፉ እና አቶ ገለቱ ጀጀርሳ የደቡብ ቀጠና አስተባባሪን ልከን ከኢንጅነሩ ጋር ውይይት እንዲያርጉ አድርገናል። በውይይቱም ከስምምነት ለመድረስ የቻሉ ቢሆንም፣ ከተስማሙ በኋላ መኢአድ ድርድሩን አፈረሰው የሚል መግለጫ ማምሻውን ማውጣታቸው በጣም አሳዛኝ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። በተለይ ይህን መሰል ጥድፊያ የሚያሳየው፣ ከጀርባቸው የተለየ ተንኮል መኖሩን ነው።
ሰንደቅ፡- ከእርስዎ መረዳት አንፃር፣ የአንድነት ፓርቲ አቀራረብ ስትራቴጂክ ወይንስ ስልታዊ ነበር?
አቶ አበባው፡-እየተፈጸመ ካለው ሁኔታ የተረዳሁት ሂደቱ በሙሉ የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ ወይም የምክር ቤቱ አካሄድ አይደለም። የግለሰብ እርምጃ ነው ጎልቶ የወጣው። በግለሰቦች እይታ ድርድሩ የሞተ ነው የሚመስለው። በፓርቲዎቹ በኩል ግን የሞተ ነገር አለ፣ የሚል እምነት የለኝም። በተለይ የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ እየሆኑ ያሉትን ነገሮች በጥልቀት ያወቃቸው አልመሰለኝም። የግለሰቦች ማፈግፈግ፣ መቁነጥነጥ ከተመለከትነው ግን የአንድነት አካሄድ ስልታዊ እንጂ ስትራቴጂካዊ አካሄድ አድርጎ ለመቀበል በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው።
ሰንደቅ፡- በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል አደራዳሪዎች መኖራቸው ይታወቃል። አደራዳሪዎቹ ይህን ችግር ሊፈቱት አልቻሉም? በምንስ አግባብ ነው የአደራዳሪነት ሚና የወሰዱት?
አቶ አበባው፡- መታወቅ ያለበት እነዚህን አደራዳሪዎች ኢንጅነር ግዛቸው ናቸው መርጠው ያመጧቸው። ቤታችንን አንኳኩተው የገቡት እራሳቸው ናቸው። እኛ አልመረጥናቸውም። እናሸማግላችሁ ሲሉን ነው ያየናቸው። መልካም፣ ለማሸማገል ከሆነ ብለን ተቀበልናቸው። በሂደት ግን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው የሆነው። ይህን ስል ግን ሁሉንም ሽማግሌዎች ማለቴ አይደለም።
ሰንደቅ፡- መኢአድ ባልመረጣቸው ሽማግሌዎች ለመደራደር መዘጋጀቱ በየዋህነት የሚወሰድ ነው ወይንስ የፖለቲካ ስህተት መሆኑን ይቀበላሉ?
አቶ አበባው፡-በእኛ በኩል የነበረው፤ እነዚህ ሰዎች ሙሁራን ናቸው። ለሀገር አስበው ነው ከሚል ቀና መነሻ ነው የተቀበልነው። በጀርባ በኩል የሚመጣ ነገር አለ ብለን አላሰብንም። እየወቀስኩ አይደለም፣ መጡብን ብቻ ለማለት ነው። በቀና ልቦና ነገሮችን መውሰድ በእኔ እምነት የፖለቲካ ስህተት አይደለም።
ሰንደቅ፡- በሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚቀርበው ውህደቱ ሀገር በቀል ሳይሆን ውጭ ባሉ አካላት የተፈበረከ በመሆኑ ነው፣ ለአለመስማማት የዳረጋቸውም ከውጪ የመጣ ስለሆነ ነው እየተባለ ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ አበባው፡- ትክክል ነው። ሆኖም ውህደቱን ሕዝቡ ይፈልገዋል። ዋናው ነጥብ መታየት ያለበት ይህ ይመስለኛል። ነገር ግን ከሁኔታዎች መነሻነት ከተመለከትነው የውህደቱ ጥንስስ ከውጪ ተቀምሮ የመጣ ነው የሚለው ጥርጣሬ ሚዛን የሚደፋ ነው። ስትራቴጂው የተነደፈው ውጪ ነው። ሀገር ውስጥ ያሉት አስፈፃሚዎች ናቸው። በእውነተኛ ፍላጎት የመጣ የድርድር ሂደት ቢሆን ስህተት ማንም ይስራ ማንም በትዕግስት ውህደቱን መፈጸም እንጂ ይቋረጥ የሚል የተጣደፈ የአደባባይ ምላሽ አይሰጥም። በእኛ በኩል ውይይቱ ይቀጥል እያልን እየጠየቅን በር ዘግተውብን ጥለውን ባልሄዱ ነበር። ስለዚህ የውህደቱ ቅመራው ያለው ውጪ ሀገር ነው።
ሰንደቅ፡- ቅመራው ውጪ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ፣ እንዴት በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ይሆናሉ?
አቶ አበባው፡- ይህን ነጥብ በትክክል መመልከት ተገቢ ነው። የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ እና የምክር ቤት አባላት ሁኔታውን በጥልቀት ሳይመለከቱት በቀናነት በተቆርቋሪነት እየሰሩ ነው የሚገኙት። የቅመራው ባለቤቶች አንዳንድ ግለሰቦች ናቸው። መታወቅ ያለበት ከአንድነት ፓርቲ ጋር የሚደረገው ውህደት በግለሰቦች ደረጃ እንጂ በተቋም ደረጃ አልሞተም። በርግጠኛነት ሁለቱ ፓርቲዎች ይህን ስልታዊ ቅመራ በጋራ በመሆን እናከሽፈዋለን። ምክንያቱም ይህ አሁን እየተቀነቀነ ያለው አስተሳሰብ የግለሰቦች በመሆኑ ነው። እንዲሁም የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ የምክር ቤት አባላት ፍላጎት እንዳልሆነ ስለምንረዳ ነው።
ሰንደቅ፡- በእናንተ አባላት የሚቀርበው ቅሬታ፣ አንድነት የመኢአድን መዋቅር ጠቅልሎ በመውሰድ ራሱን የበለጠ ለማደራጀት የሚፈልግ ፓርቲ ነው የሚል ነው፤ በዚህ ነጥብ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ አበባው፡- አንድነት መዋቅር አለው፣ የለውም የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መኢአድ ያለውን መዋቅር ሰጥቶም ቢሆን ለሕዝባችን አማራጭ ፓርቲ መሆን በጋራ እስከቻልን ድረስ ብዙ ችግር የለውም።
ሰንደቅ፡- ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው ገዢው ፓርቲ ሁለቱ ፓርቲዎች እንዳይስማሙ ሰርጎ ገብቷል እያሉ ነው የሚገኙት። ይህን ሃሳብ ምን ያህል ይጋሩታል?
አቶ አበባው፡- እንዲህ እንደሚባል እኛም እንሰማለን። የሚገርመው እኛ የተስማማነው ነገር ሳይኖር ገዢው ፓርቲ ምኑን ነው የሚያፈርሰው። አንድነት ከመድረክ ሙሉ ለሙሉ መውጣት አለበት ለሚለው ጥያቄ፣ አንድነት እንጂ ገዢው ፓርቲ ምላሽ መስጠት ያለበት አልመሰለኝም። መጠራጠሩ ግን ክፋት የለውም፣ ተጨባጭ ለማድረግ ግን ብዙ መስራት ይፈልጋል።
ሰንደቅ፡- በተደጋጋሚ ግለሰቦች እያሉ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ለምን በይፋ በማሳወቅ አትታገሏቸውም?
አቶ አበባው፡- ጋዜጠኛ እንዲህ ብሎ አይጠይቅም። ከዚህ በፊት የነበረውን ቅንጅት ማን እንዳፈረሰው ታውቃላችሁ። ለምሳሌ ብርቱካን በእስር በነበረችበት ጊዜ ብርቱካን የታሰረችው በራሷ ችግር እንጂ በፓርቲ አይደለም። አዲስ ሰው መሾም አለበት ያለው ማነው? ከዚህ በፊት አንድነትን ከመድረክ ጋር ለማዋሃድ ሽማግሌ የነበሩት ሰዎች እነማን ናቸው? ከዶክተር ነጋሶ ጋር ከስምምነት የደረስንበትን ሰነድ አልፈርምም ያለው ማን ነው? ለምንስ ተደራዳሪ የነበሩት እንዲነሱ ተፈለገ? ድርድሩ ከቆመበት መጀመር ሲገባው ለምን እንደአዲስ እንዲጀመር ተፈለገ? ከመድረክ ውጪ ሆነናል ተብሎ በአደባባይ ከተናገሩ በኋላ፤ መለስ ብሎ ጋዜጦችን ጠርቶ ከመድረክ ጋር እንሰራለን ማለት ምን ማለት ነው? የአንድነት ወጣት አመራሮች መድረክን በአደባባይ እየተቃወሙ፣ ግለሰቦች ግን ከመድረክ ጋር እንሰራለን ለምን ይላሉ? ስለዚሀም የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤት ይህን እውነት ፈትሾ የውህደቱን ሂደት እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ። ይህ የማይሆን ከሆነም እንደበፊቱ በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነን።
No comments:
Post a Comment