ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይህን ያሉት ኢህአዴግ የ6 ወራት የስራ አፈፃፀሙን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዳራሽ በገመገመበት ወቅት ነው።
ስራ ፈጠራውም ሆነ ሳይታረሱ የኖሩትን ወል መሬቶችን እያደራጁ ለወጣቱ አርሶደአር መስጠት አላዋጣም ያሉት አቶ ሃይለ ማርያም ፣ በገጠር መሬት የማከፋፈል ስራ ከተሰራ በሁዋላ የምንሰጠው መሬት በማጣታችን ስራ ካገኘው ይልቅ የተሰደደው ወጣት ይበልጣል ብለዋል፡፡
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በንግግራቸው፡ በአማራ ክልል የሚታየው የገጠር ወጣቶች የእርስ በርስ ግድያ አሀዝ መጨመር፤ የደቡብ እና የኦሮሞ ክልሎች ወጣቶች በገፍ መስደድ ፣ የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ኢትዮጵያዊነታቸውን እየተው ደቡብ ሱዳናዊ ነን ማለት መጀመራቸውና ኢትዩጵያን እየተው ወደ ደቡብ ሱዳን መሄዳቸው፣ የኢትዩጵያ ሶማሌዎች ከአገራቸው ይልቅ ለመቋዲሾ ለመገበር ፍላጎት ማሳየታቸው፣ በመሬት እጦት እና መሰረት ባልያዘው የገጠር ወጣቶችን የስራ ፈጠራ መዳከም የመጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል። አቶ ሃይለማርያም ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ምንም አይነት የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ አስተያየት አልተሰጠበትም። በስብብሰባው ላይ የተሳተፉ አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ስር የሰደደው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ ድህነትና ተስፋ ማጣት ከመሬትና ከስራ እድል ፈጠራ መዳከም በተጨማሪ ለወጣቱ መሰደድ ምክንያት መሆናቸውን አቶ ሃይለማርያም ለማንሳት ሳይፈልጉ ቀርተዋል ብለዋል።
በጥቃቅን እና አነሰተኛ የስራ እድል ፈጠራ እስካሁን ድረስ ሪፖርት የሚደረገው በእጅጉ የተጋነነ ነው ያሉት አቶ ሃይለማርያም ፣ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በየአመቱ ሪፖርት ከሚደረገው በሚልየን ከሚቆጠረው ህዝብ ሩብ ያክሉ ስራ አለመያዙን ገልጸዋል፡፡
ስራ የያዙ ወጣቶችን በተመለከተ ከታች መስሪያ ቤቶች ሪፖርቶች ሲላኩ ቁጥሩ በ5 እንደሚባዛ አቶ ሃይለማርያም አልሸሸጉም።
“በወረዳ እና በከልል ደረጃ የሚገኙ የወጣት፣ የሴቶች እና ህፃናት መስሪያ ቤቶች አንዱን ወጣት አደራጀነው፣ የስራ እድል ፈጠርንለት ብለው ሪፖርት ይልካሉ፣ እንደገና ቴክኒክ እና ሙያ ፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ ፤ የሴቶች ሊገ ፤ የወጣቶች ሊግ ፤ ፊደሬሺን ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያንን ወጣት በአንድ ቀን ስብሰባ ስላገኙት ብቻ መልሰው በስራ እድል ፈጠራና በተደረጁ ወጣቶች ስም ሪፖርት ይልካሉ፣ ስለ አንዱ ነፍስ ደርበው ደራርበው ሪፖርት በመላክ አንድ ሰው ከአምስት ጊዜ በላይ ተቆጥሮ ሪፖርት እየተደረገ” ነው ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ በወረዳው ነበራዊ ሁኔታ ሲታይ ያ ሪፖርት የሚደረግበት ወጣት በቦታው የለም” ሲሉ አክለዋል። “ይህ ኪሳራ በምንም ሁኔታ ለሚዲያ ሳይወጣ የምክር ቤት አባላት ሊያውቁት ይገባል” ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋገሚ የሚያቀርበው የኢኮኖሚ እድገት ዘገባ ትክክል አይደለም የሚል ትችት ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።
ኢሳት ዜና
No comments:
Post a Comment