Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, March 6, 2014

በቁጫ ወረዳ አንድ ወጣት ራሱን እናቱንና ከብቶቹን በእሳት አጋየ


የካቲት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በቁጫ ወረዳ በቦላ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው የ9ኛ ክፍል ተማሪ ኢዮብ ኢማን የካቲት 21 ቀን 2006 ዓም ከምሽቱ 3 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ ራሱን ጨምሮ እናቱን፣ 8 የቀንድ ከብቶችንና ሌሎች ንብረቶችን በእሳት አጋይቷል። ወጣቱ የካቲት 3 ቀን የቁጫ ወረዳ ባህላዊ ዘፈን ከጓደኞቹ ጋር እየዘፈነ በሄደበት ወቅት አንድ የፖሊስ ባልደረባ ” ለምን ትዘፍናላችሁ ብሎ በጫማ ጥፊ እንደመታውና እንደወደቀ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመረበሽ ባህሪ ይታይበት እንደነበር” የደቡብ ዘጋቢያችን ገልጿል። ወጣቱ በእራሱና በበእናቱ ላይ የወሰደው እርምጃ ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ የሚገልጸው ዘጋቢያችን፣ በወቅቱ በወረዳው በተካሄደው አፈሳ ምክያት በቂ ህክምና ሳያገኝ መቅረቱን ገልጿል። በቁጫ ወረዳ የሚገኙ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ባህላዊ ዘፈን በጋራ እየዘፈኑ ሲሄዱ በፖሊሶች ታፍሰው እንደተደበደቡ ኢሳት በወቅቱ ዘግቦ ነበር። የሟቾቹ ቀብር የካቲት 22 ቀን በቦላን ቀበሌ ተፈጽሟል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የወረዳው ህዝብ ያቀረበውን የማንነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተከትሎ የታሰሩት ከ1 ሺ 700 በላይ ሰዎች ቢሆንም በአርባ ምንጭ እስር ቤት ታስረው የሚገኙት ከ246 እንደማይበልጡና ሌሎች የደረሰቡት እስካሁን አለመታወቁን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በአርባ ምንጭ እስር ቤት ውስጥ 152 አርሶደሮች፣ 43 ተማሪዎች፣ 59 የቢሮ ሰራተኞች፣ 12 መምህራን፣ 5 የግል ባለሀብቶችና 5 ሌሎች ታዋቂ ምሁራን ታስረው ይገኛሉ። የቁጫን ጥያቄ ያራምዳሉ የሚባሉ ሰዎች አሁንም ድረስ እየታደኑ ነው። ቀደም ብለው የተፈቱት ደግሞ ከስራ ከመባረር ጀምሮ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እየተደረገ ነው። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የአንድ ሰው ህይወት ያጠፋው ወታደርም እስካሁን ለፍርድ አለመቅረቡን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials