Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, December 16, 2017

በሰሜን ጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ





በሰሜን ጎንደር ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ መካሔዱ ታወቀ፡፡ ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ በሰሜን ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ የህወሓትን አገዛዝ ሲቃወም ውሏል፡፡ በዚህ የስርዓት ተቃውሞ ሰልፍ ላይ፣ በርከት ያለ ህዝብ ተገኝቶ ጸረ ህወሓት አመለካከቱን እንዳንጸባረቀ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በዚሁ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተለያዩ መፈክሮች የተስተጋቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሰልፉ ዓላማ ግን የህወሓት አገዛዝ እንዲያከትም የሚጠይቅ መሆኑን እማኞች ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር ጭልጋ ወረዳ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የንግድ መደብሮች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን የጠቆሙት የመረጃ ምንጮች፣ ሰልፉም እስከ አስር ሰዓት ገደማ ድረስ መካሄዱን መረጃዎቹ አክለው ጠቁመዋል፡፡ ህዝቡ የህወሓት አገዛዝ እንደመረረው የገለጸበትን ይኸው ሰልፍ ለመበተን የሞከሩ የጸጥታ አካላት ሳይሳካላቸው መቅረቱም ተሰምቷል፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለጻ ከሆነም፣ ህዝቡ ፍጹም ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ድምጹን ሲያሰማ ነበር፡፡

ሰልፉን እንዲከታተሉ የታዘዙ የጸጥታ አካላት፣ ምንም እንኳን በሰልፉ ወቅት ሰልፈኛውን ባይተናኮሉም፣ ሰልፉ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን በድብቅ የታሰሩ ወይም የተደበደቡ ሰዎች ስለመኖራቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ አገዛዙ አንዳንዴ፣ በአደባባይ የሚካሔዱ ሰልፎችን በዝምታ ከተመለከተ በኋላ፣ ህዝቡ ድምጹን አሰምቶ ወደ ቤቱ ሲገባ ጠብቆ፣ ብዙዎችን እስር ቤት እንደሚወረውር ከዚህ ቀደም ተስተውሏል፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ የተደበደቡ እና የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ዳግም ያገረሸው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲሁም የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎችን አካትቶ በሰፊው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials