የህዝብ
ነጻነት
ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ
ይባል ነበር ድሮ ምንድንነን በሃገርስ
ከእንስሳ አሳንሰው አይደል የሚያዩንስ?
ከሰው ሳይቆጠር በትውልድ በሃገሩ
እነሱ ወርቅ ዘር እኛ አንሰን ከአፈሩ
መታፈን መገረፍ ጨለማ ቤት እስሩ
እንደከብት ቆዳ መሰነታተሩ
ዜጋው በሃገሩ ሞት ሲሆን ቀመሩ
ላይቀናው ሲያማትር ለስደት መብረሩ።
ሃገር የማይናፍቅ ምንድነው ነገሩ?
ከወራሪ ጠላት ይብሳል አብዝቶ።
ይብቃ መከተሉ እስቲ እንየው ቀርቶ።
ነጩ ፋሺዚምን የጣለው ክንድ ሳይዝል
ዘመን አመጣሹን ሊመክተው ሲችል
ከከገዢዎች ወህኒ አምልጦ ኮብልሎ
በሃገሩ ከመሞት ስንቱ ባህር ዘሎ
በረሃ አቋርጦ አካሉን አጉድሎ
ያገግማል እንጂ አይሄድ ሀገር ብሎ
ይመለሳል እንጂ አይወስን ጠቅልሎ።
የሚሞካሽልሽ ጋራው ሸንተረሩ
ዘፈን ሆነው ቀሩ ፥ስሜት እንዳይፈጥሩ
ጉልበት ቢሸፍነው ቀዬና አድባሩ።
ከዲስኮው መባቻ ወደራስ ሲዞሩ
በአካልም በመንፈስ እዚያ ሲያማትሩ
እኛን ሊያጫርሱ ከፋፍለው በዘሩ
ለደረቅ ምድራቸው በወዝም የሚያድሩ
ያለነሱ የለም አልያም ፎቅ ቢሰሩ።
የነሱ ክልልን ለሌላ የማይሰጡ
ከፋፍሎ በመግዛት ሁሉን በየጎጡ
ከተወለዱበት አኙዋኮች ውጡ!
አማራዎች ውጡ! ኦሮሞዎች ውጡ!
ያስተማሩት ቋንቋ ይኼ ነው ፈሊጡ።
በዘመኑ ገዢ ሰዉ ተማረረ
ከወራሪ ጠላት ይብሳል አብዝቶ።
ይብቃ መከተሉ እስቲ እንየው ቀርቶ።
ከመከተል አንዱ ፈረንጅ እንዳልመከትን
ያውም እኛው ሄደን
ስደት ቅኝ
አስገዛን
ሌላኛው ወያኔ የኛን
ቆዳ ለብሶ
እየተከተልነው ስንት አመት
በለቅሶ!
ለ ሃገሬ አብቃኝ ይሉ ነበር አበው
ወይ ሸሽተው ሳይሄዱም ህዝቤ ሃገሬ ብለው
እንደ አቡነ ጴጥሮስ በሃገር መሞት ድል ነው።
የአበው
ተተኪዎች ሲሆን እንበልጣለን
ባካል
ባንታደም ባየር እንገባለን
በውጭ በነጻነት በየትም ቢኖሩ
ለማንበብ ሲያወጡ አይወድቅ መነጽሩ
ምላስ አይቆረጥ እውነት ተናገሩ
ምድረ ርስት እንድንወርስ በአንድ ተባበሩ
ነጭን እንዳሸነፍን አንፍራ ለጥቁሩ
ሰው የሚከብርባት ይሁን የሃገር ቅጽሩ
ከወራሪ ጠላት ይብሳል አብዝቶ።
ይብቃ መከተሉ እስቲ እንየው ቀርቶ
ቅኝ ገዢው ጠፍቶ ፥ ስደቱ ተገቶ ።
የህዝብ ነጻነት ያብብ እንጂ ፈክቶ
ከ አብርሃም
(ሬገn) ህዳር
2007 ዓም
No comments:
Post a Comment