Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 17, 2017

ከወዲሁ ያልተጠበቁ ነገሮችን ያሳየን ታላቁ የዓለም ዋንጫ – ሩሲያ world cup 2018







ከዓመታት የማጣሪያ ውድድሮች በኋላ በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የ2018 የዓለማችን ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ሊጀመር የወራት ዕድሜ ቀርቶታል። ከወዲሁም ያልተጠበቁ ክስተቶችን ማመልከት ጀምሯል። በፍልሚያው ሜዳ የተጠበቁት ሲቀሩ፤ ያልተጠበቁት የተሳትፎ ትኬት ቆርጠዋል። የመድረኩ ድምቀቶች ብርቱካናማዎቹ ሆላንዶች እና ጣሊያኖች በአይስላንድ እና በፓናማ ተተክተዋል።

በመድረኩ በአምስት አገራት የምትወከለው አህጉራችን አፍሪካም ብትሆን አብዛኞቹን ተወካዮቿን ቀይራለች። ከአራት ዓመት በፊት በነበረው መድረክ በጋና፤ ካሜሮን፤ ኮትዲቯር፤ ናይጄሪያና አልጄሪያ የተወከለችው አፍሪካ፤ ከአራት ዓመት በኋላ ናይጄሪያዎችን አስቀርታ አራቱን ቀይራለች። የተሳታፊዎቹን 32 አገራት አስቀድሞ ያስተዋወቀን የዓለም ዋንጫም ከቀናት በፊት ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖቹን በምድብ ከፋፍሎ የመጀመሪያ ዙር ተፋላሚዎቻቸውን ይፋ አድርጓል።

በምድብ አንድ

በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 65ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙትና የዓለም ዋንጫው አስተናጋጆች ለሆኑት ሩሲያዎች ከምድባቸው በጊዜ መሰናበት ከምንም በላይ የማይዋጥ ነው። እናም አንድ ጨዋታ መሸነፍ የሚያስከፍለውን ዋጋ ጥንቅቀው ያውቁታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩበትን የፖለቲካ አቅምና አቋም በስፖርቱም መስክ ማሳየት ይፈልጋሉ። ለዚህ ዓላማቸው ተፈፃሚነትም ልምድ ያላቸውን አላን ድዛጎኤቭ፤ ፊዮዶር ስሞሎቭ የመሳሰሉ ኮከቦች ላይ ተስፋ ጥለዋል። ለውድድሩ ዝግጅት የሰጡትን ትኩረት በእግር ኳሱ ፍልሚያ መድገም ከቻሉም ታሪክ ይፅፋሉ።

ከጣሊያኑ 1990 የዓለም ዋንጫ ወዲህ ዓመታትን ቆዝመው ዳግም ወደ ታላቁ መድረክ የተመለሱት የአፍሪካ ተወካዮቹ ግብፆችም ቢሆኑ በሩሲያው መድረክ ያልተጠበቀ አስደማሚ ታሪክ መፃፍ ይፈልጋሉ። «ግብፃዊው ሜሲ» የሚል ቅፅል ከተሰጠው ውድ ልጃቸው መሃመድ ሳላህና ከአርሴናሉ ኮከብ መሃመድ አልኒኒ ብዙ ተዓምር ይጠብቃሉ።

በሉዊስ ሱዋሬዝ ልዩ ክስተቶች የምትታጀበው ኡራጓይ ከባርሴሎናው ኮከብ በተጓዳኝ በፓሪሴን ጄርሜኑ የጎል አውራ ኤዲሰን ካቫኒ ላይ ዕምነት ጥላለች። ከ1950 ወዲህ ዋንጫ ማንሳት ያልሆነላቸው ኡራጎዮች በሩሲያ ምድር የዋንጫ ረሃባቸውን ለማስታገስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።

እግር ኳስ ሲነሳ እምብዛም ስሟ አብሮ የማይነሳውና በቀድሞው የአርጀንቲና አሰልጣኝ ኤድጋርዶ ባውዛ የምትመራው የመካከለኛው ምስራቅ አገር ሳዑዲ ዓረቢያ በሞስኮ ሰማይ ስር ያላትን አቅም ለማሳያት ዝግጅቷን አጠናቃለች። ከዚህ ምድብ ኡራጋይና ግብፅ በኮከብ ተጫዋቾቻቸው ብቃት ታግዝው ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ ተገምቷል። ክብር የሚሰጠው የመክፍቻ ጨዋታ በሳዑዲና ሩሲያ መካከል ይደረጋል።

ምድብ ሁለት

የ2016 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ፖርቹጋል የአውሮፓ ኃያልነቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ መድገም አቅዳለች። ይህን ኃላፊነትም ለዓለማችን ኮከብ የግብ ማሽን ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአደራ ሰጥታለች። ተጫዋቹ ከሰሞኑ እያሳየ በሚገኘው ደካማ አቋም ከቀጠለ ግን የአውሮፓ ሻምፒዮኖቹ የሚፈለጉት ሳይሆን የማይፈልጉት መሆኑ አይቀሬ ነው።

ስፔኖች ከስምንት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ የፃፉትን ወርቃማ ታሪክ በሩሲያ ምድር ዳግም ማድመቅ ይፈልጋሉ። በወጣት ተጫዋቾቿ ተወክላ ወደ ሞስኮ የምታቀናው ስፔን፤ ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት ካላቸው አገራት አንዷ ብትሆንም የቀድሞው አስፈሪነቷ ግን አሁን ያለ አይመስልም።

በ1978 በዓለም ዋንጫው መድረክ ጨዋታን በማሸነፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ከብር ያገኙት የሰሜን አፍሪካዎቹ ድንቅ ልጆች ሞሮኮዎች፤ የዓለም ዋንጫው ልዩ ክስተት እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ሞሮኮዎች በመጨረሻው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ በጠንካራ ስብስብ የተዋቀረው የኮትዲቭዋር ቡድን አሸንፋው ሩሲያ የሚወስደውን ትኬት መቆረጣቸው ይታወሳል። የዚህ ምድብ ሌላኛዋ አገር ኢራን ናት። ወደ ዓለም ዋንጫ ስታልፍ የአሁኑ አምስተኛዋ የሆነው ኢራን ከዚህ ቀደሙ የተሻለ አዲስ ውጤት ታስመዝግባለች ተብሎ አይጠበቅም። የታላቁን መድረክ የመጀመሪያ ፈተና ማለፍ ስለመቻሏም ከራሳቸው በቀር ማንም አይተማመንም።

ከዚህ ምድብ ፖርቱጋልና ስፔን በቀላሉ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን የሁለቱ አገራት ጨዋታም የመድረኩ ትልቅ ጨዋታ እንደሚሆን ታምኖበታል። በሁለቱ አገራት ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ከግማሽ በላይ ከሚሆኑ የሪያል ማድሪድ ቤት ጓደኞቹ ጋር ለተቃራኒ ዓላማ ይፋጠጣል። ስፔናዊው የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ሰርጂዎ ራሞስም ሮናልዶን ለማቆም አለኝ የሚለውን ብቃት አሟጦ ይጠቀማል።

ምድብ ሦስት

የ1998 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅና የዋንጫው ባለቤት ፈረንሳይ ባለተሰጥኦ የወጣት ተጫዋቾችን የያዘ ስብስብ ይዛ ሞስኮ ትደርሳለች። በሰላማዊው የፍልሚያ መድረክ ለማንቸስተር ዩናይትዱ ፖል ፖግባ፣ ለቼልሲው የመሃል ሜዳ ሞተር ንጎሎ ካንቴ የመሃል ደጀን ኃላፊነቱን ስትሰጥ፤ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አንቷን ግሪዝማን ደግሞ የግብ ኃላፊነቱን ይረከበዋል።

አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻም ብቁ ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን የተጫዋቾችን የግል ብቃት ወደ ቡድን የማምጣት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። የዘንድሮ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ዋንጫ ካላነሳም መቼም አያነሳም የሚል አስተያየት ከወዲሁ መሰጠት ጀምሯል።

እ ኤ.አ ከ2010 በኋላ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ የሆነችው ዴንማርክ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ አምስተኛ ተሳትፎዋ ነው። ዴንማርኮች በብራዚል ከውድድሩ በወጡበት የ1998ቱ የዓለም ዋንጫ እስከ ሩብ ፍፃሜ መጓዝ መቻላቸው ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ከዚህ የተሻለ ታሪክ ለመሥራት ለቶተንሃሙ አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰንን ከባድ ኃላፊነት አስረክባለች።

የዘንድሮው የአውስትራሊያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ ግን አምስተኛዋ ነው። ጥሩ ተሳትፎ አድርጋበታለች የሚባለው በ2006 በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ሲሆን፤ ከመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ገብታ ከጣሊያን ጋር ባደረገችው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ በተሰጠባት ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፋ የወጣችበት ነው።

የደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ በሞስኮው ፍልሚያ የሎኮሞቲቭ ሞስኮውን ጨዋታ ቀያሪ ጀፈርስን ፋርፋንን ተስፋ አድርጋለች። በዚህ ምድብ የዓለማችንን ውድ ተጫዋች ይዛ መድረኩን የምትቀላቀለው ፈረንሳይ በኮከቦቿ ተዓምር ከምድቧ ማለፏ ጥርጥር አይኖረም። ዴንማርኮችም ለሁለተኛነት ሰፊ ግምት አግኝተዋል።

ምድብ አራት

በዚህ ምድብ የአህጉራችን ተወካይ ናይጄሪያ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን መሆን ከቻሉት በኮከቦች ስብስብ ከተዋቀሩት አርጀንቲናዎች ትፋጠጣለች። ከ1994 የአሜሪካ የዓለም ዋንጫ ወዲህ አንድ የዓለም ዋንጫ ብቻ ያመለጣቸው ንስሮቹ፣ በማጣሪያ ጨዋታዎች የነበራቸው ያለመሸነፍ ጉዞ በሩሲያው ታላቅ እግር ኳስ መድረክ ይደግሙታል ተብለው እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል።

ቪክቶር ሞሰስ፣ የአርሴናሉ አሌክስ ኢዮቢ እና ሌሎችም ተጫዋቾች ያካተቱት ንስሮቹ፤ በተለይም በምድብ ማጣሪያዎች በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግብ እያስቆጠሩ መምጣታቸው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሳያ ተደርጓል።

አርጀንቲና አንሄል ዲማሪያ፣ ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ሊዮኔል ሜሲ፤ ኩን አጉዌሩ፤ ጎንዛሎ ሄጊዌን እንዲሁም የጁቬንቱሱን ጨዋታ ቀያሪ ፓውሎ ዲያባላን በመሳሰሉ ኮከቦች ብትወክልም ወደ መድረኩ ለመምጣት በእጅጉ ተቸግራ መታየቷ በሩሲያው መድረክ ብዙም ግምት እንዳይሰጣት አድርጓል። ይሁንና አስፈሪ ቡድን መያዟ እርግጥ ነውና የዋንጫ ግምት የሚሰጧትም በርካታ ሆነዋል።

ሉካ ሞድሪች፣ ኢቫን ራኪቲች፣ ማሪዮ ማንዙኪች፣ ኢቫን ፔርሲችና ኒኮላ ካሊኒችን የመሳሰሉ በድንቅ ክህሎት የታገዙ ብቁ ተጫዋቾች ባለቤት የሆነችው ክሮሺያ የመድረኩ ክስተት ትሆናለች ተብሎ ትጠበቃለች።

የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ለአይስላንዶች የመጀመሪያ ተሳትፏቸው ነው። በኮከቦች ከተዋቀረችው አርጀንቲና ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርገው ትንሸ አገር ምንም እንኳን በሩሲያው መድረክ ብዙ ርቀት ትጓዛለች ተብሎ ባይገመትም መድረኩን መቀላቀሏ ብቻውን እንደ ስኬት ይቆጠርላታል።

ምድብ አምስት

የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከየትኛውም ብሄራዊ ቡድን በላይ ለብራዚሎች የላቀ ዋጋ አለው። የአምስት ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ብራዚል፤ የቀደመ የእግር ኳስ ኃያልነት ተምሳሌትነቷን እና ከአራት ዓመት በፊት ራሷ ባዘጋጀችው መድረክ የደረሰባትን ሃፍረት ለመቀልበስ ሌላ ተጨማሪ ዓመት መጠበቅ አትፈልግም።

ኔይማር ጁኒየር፤ ጋብሬል ጀሱስ እና ፊሊፔ ኮቲንሆ የመሳሰሉ ምትሃተኛ ተጫዋቾችን የያዙት ቢጫ ለባሾቹ፤ በዓለም ዋንጫው እያንዳንዱ የማጣሪያ ጨዋታ ያሳዩትን አቅምና አቋም በዋናው ውድድር የሚደግሙት ከሆነ የፍላጎታቸውን እንደማያጡ ጥርጥር የለውም።

የማጣሪያ ጨዋታዎችን በብቃት አሸንፈው ወደ ዓለም ዋንጫ መግባታቸውን ካረጋገጡ አገራት አንዷ ስዊዘርላንድ ናት። አገሪቱ የውድድሩ ልዩ ክስተት ከሚሆኑ ክለቦች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ስትሆን፣ ዤርዳን ሻኪሪ፣ ብሬል ኤምቦሎ፣ ግራኒት ዣካ፣ የተለየ አቋም ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።

ከዚህ ምድብ ኮስታሪካና ሰርቢያ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ብራዚልና ሲውዘርላንድ የታላቁን መድረክ የመጀመሪያ ፈተና በማለፍ ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሊቨርፑሉን ፊሊፕ ኩቲኒሆን ከአርሴናሉ ግራኒት ዣካ የሚያፋጥጠው የሁለቱ አገራት ጨዋታም ከወዲሁ ተጠባቂ ከሆኑት ትርታ ተመድቧል።

በምድብ ስድስት

ከአራት ዓመት በፊት በድንቅ ቡድናዊ ጥምረትና ሜሱት ኦዚልን በመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾች ግላዊ ብቃት ዋንጫውን ማነሳት የቻሉት የወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ብሄራዊ ቡድን የሆኑት ጀርመኖች፤ ያለፈውን ታሪክ ዘንድሮም መድገም ይፈልጋሉ። ቶማስ ሙለርና ቶኒ ክሩስን በመሳሰሉት ተጫዋቾች ጠንካራ ቡድን መመስረታቸውን ዋቢ በማድረግ ያለፈውን ድል እንደሚደግሙት የማይጠራጠሩት ከሚጠ ራጠሩት ይልቃሉ።

ሜክሲኮ ከዚህ ቀደም በነበሩት የዓለም ዋንጫዎች የነበራትን ምርጥ ተፎካካሪነት አሁንም እንድትጠበቅ ያደርጋታል። የውድድሩ ድምቀትና ክስተት እንደምትሆን የማትጠረጠር ሌላኛዋ አገር ስውዲን ናት። ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ጨዋታ መሳተፏን ያረጋገጠችው የእስያ ዞን ተወካይዋ ደቡብ ኮሪያ የቶተንሃሙን ኮከብ ሰን ሄዩንግ ሚን እና ሌሎችም ተጫዋቾች ይዛ ለተቃራኒ አገራት ፈታኝ እንደምትሆን ይጠበቃል። ጠንካራ ምድብ ከተባለው ከዚህ ምድብ ጀርመኖች በቀላሉ እንደሚያልፉ ጥርጥር የለውም። ከሲውዲንና ከሜክሲኮ ማን ያልፋል የሚለውን ግን መገመት አዳጋች ሆኗል።

ምድብ ሰባት

ይህ ምድብ ምርጥ ጨዋታ ይታይበታል ከሚባሉ ጨዋታዎች መካከል ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የለውም። በጋሬዝ ሳውዝጌት የሚመሩት ሦስቱ አናብስት እንግሊዞች በማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ዓለም ዋንጫው ለመግባት ያሳዩት አቋም እጅግ ተደንቆላቸዋል። በቶተንሃሞቹ ጨዋታ ቀያሪዎች ሃሪ ኬንና ዴሌ አሊ ፊት አውራሪነት የሚመሩት አናብስቶቹ፣ ከ 1966 በኋላ የዓለም ዋንጫውን ዳግም ወደ ለንደን ይዘው መመለስ ከቻሉ ለቡድኑ አባላት በርከት ያለ ገንዘብ ተመድቦላቸዋል።

ወደ ሩሲያ ከሚያቀናው የቤልጄም ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ በእንግሊዝ ምድብ የሚጫወቱ 19 ጨዋታዎች አሉ። ዓለም በማግባትና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የመሰከረላቸው ኬቪን ደ ብሩይነ፣ ኤዲን ሃዛርድ እና ሮሜሉ ሉካኩ የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን ይዛ ወደ ሞስኮ የምትገባው ቤልጄም፣ ለሦስቱ አናብስት ፈታኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም።

ቱኒዚያ በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ አምስተኛዋ ነው፤ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድኗ ስብስብ በዋናነት ከአገር ውስጥ ክለቦች የተውጣጣ ነው። የአፍሪካዋ ተወካይ በጠንካራ ምድብ ውስጥ እንደ መገኘቷ በርካታ ወገኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን እንዲጠራጠሩ ሆነዋል። ከዚህ ምድብ ዝቅተኛ ግምት ያገኘችው ፓናማ ሆናለች።

ምድብ ስምንት

በሩሲያ የዓለም ዋንጫ ልዩ ክስተት እንደሚሆኑ ከሚጠበቁ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ሴኔጋሎች ይካተታሉ። የምዕራብ አፍሪካዋ አገር በ2002 በእነ አል ሃጂ ዲዩፍ ፊት አውራሪነት እየታገዘች የሠራችው ገድል ሁሌም የሚታወስና ታሪክ ተሻጋሪ ነው። የሊቨርፑሉን ፈርጣማ ግብ አዳኝ ሳዲዮ ማኔ ድንቅ ብቃት በሩሲያ ከሚደምቁት አፍሪካዊ አገራት አንዷ የሆነችው ሴኔጋል፤ የዘንድሮ ስብስብም ጥንካራ እንደሆነ በበርካታ ወገኖች ተመስክሮለታል።

ሃሜስ ሮድሪጌዝ፣ ራዳሜል ፋልካኦ፣ ሁዋን ኳድራዶ፣ ዬሪ ሚና እና ዳቪንሰን ሳንቼዝን ይዛ ወደ ሞስኮ የምታቀናው የደቡብ አሜሪካዋ የኮከቦች መፍለቂያ ኮሎምፒያውም የሞስኮ ሌላ ድምቀት ናት። አውሮፓዊቷ ፖላንድም ብትሆን ቀላል ግምት የሚሰጣት አይደለችም። የባየር ሙኒኩ አስፈሪ አጥቂ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ አገር በዓለም ዋንጫው ብዙ ርቀት መጓዝ እንደምትችል በርካታ ወገኖች ጥርጣሬ ውስጥ አልገቡም።

ሌላኛዋ የዚህ ምድብ ተካፋይ የሆነች አገር ጃፓን ናት። ምንም እንኳን በእግር ኳስ የሚሆነው ባይታወቅም፤ የኤሲያ ተወካይዋ በመድረኩ ታሳያለች የሚባለው ውጤት ዝቅተኛ ነው፡፡ የታላቁ መድረክ የመጀመሪያ ፈተና የማለፋቸው ነገር ያጠያይቃል። ቀላል ምድብ እንደሆነ በተለየው በዚህ ምድብ ኮሎምፒያ እና ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉ ከወዲሁ መገመት ጀምሯል።



ታምራት ተስፋዬ

No comments:

Post a Comment

wanted officials