የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ስለመሆኗ እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ አንድ ሰው ሲገደል 200 ያህል ቆሰሉ።
በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ እንዲሁም በእስራኤልና ጋዛ ድንበር ላይ ከፍተኛ ግጭት ተከስቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ነች አሜሪካም ኤምባሲዋን ከቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ታዞራለች ማለታቸው ግጭት እንደገና እንዲያገረሽ ምክንያት ሆኗል።
በፍልስጤም በመሀሙድ አባስ የሚመራው የፋታህ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን በዚህ ወር መጨረሻ በአካባቢው ጉብኝት ለማድረግ እቅድ የያዙት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እንዳይመጡብን ብለዋል።
ባለስልጣኑ አክለውም በፋታህ ስም የትራምፕ ምክትል የሆኑት ሰው እንዳይመጡብን በፋታህ ስም እንጠይቃለን ብለዋል።
ማይክ ፔንስ አባስን ለማግኘትና በቤተልሄም ስብሰባ ለመቀመጥ ቀጠሮ ይዘው ነበር።
ይህ ስብሰባ ግን አይከናወንም ብለዋል የፍልስጤሙ ባለስልጣን ጅብሪል ራጁብ።
የእስራኤሉ የመከላከያ ሃይል በታንክና በጦር ጀቶች በመታገዝ የሃማስ ኢላማዎችን መደብደቡን ኢየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።
ከጋዛ ሰርጥ የተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች ግን በእስራኤል ግዛት ሳይደርሱ መቅረታቸው ታውቋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋንና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሜር ፑቲን በስልክ ባደረጉት ውይይት የትራምፕ ውሳኔ በሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል ቀድሞውንም ኢየሩሳሌምን እንደ መዲናዋ ስትቆጥር ፍልስጤሞች በበኩላቸው በ1967ቱ ጦርነት በእስራኤል የተያዘችው ምስራቅ ኢየሩሳሌምን የወደፊቱ የፍልስጤም አስተዳደር መዲና ነች ብለው ያምናሉ።
እስራኤል በ1948 ከተመሰረተች ወዲህ ኢየሩሳሌም መዲናዋ እንደሆነች እውቅና ስትሰጥ አሜሪካ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የአሜሪካንን ኤምባሲ ከቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ለማዞር በትንሹ 2 አመት ሊፈጅ ኣንደሚችል መናገርቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ብጥብጡ ግን ከአሁኑ የሰው ሕይወት መቅጠፍ ጀምሯል።የእስራኤል ፖሊሶች በጋዛ ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ የ30 አመት ወጣት ሲገደል በየአካባቢው በተደረገው ተቃውሞ ወደ 200 የሚሆኑ ሰዎች ቆስለዋል።
በዮርዳኖስ፣ግብጽ፣ቱርክ፣ቱኒዚያ፣ኢራን፣ማሌዢያ፣ባንግላዴሽ፣ፓኪስታን፣አፍጋኒስታንናበሕንድ በምትተዳደረው ካሽሚር ግዛት የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ በመቃወም ከፍተኛ ሰልፍ ተካሂዷል።
በአንዳንድ ቦታዎች ሰልፈኞቹ የአሜሪካንን ባንዲራ አቃጥለዋል።
No comments:
Post a Comment