የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ እንድትሆን እውቅና ሰጡ ።
ይህን ተከትሎም የአረብ ሀገራት መሪዎች የፕሬዝዳንት ትራምፕን ርምጃ ሲያወግዙ የካቶሊካውያኑ ሊቀጳጳስ ኢየሩሳሌም የሁሉም ነች በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በጉዳዩ ላይ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት እንደሚያነጋግሩ አስታውቀዋል።
አሜሪካ ቴል አቪቭ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ ኢየሩሳሌም ለማዛወር መወሰኗንም ሆነ ለኢየሩሳሌም ዋና ከተማ የሰጡትን እውቅና የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ ተቀባይነት የሌለው በማለት ተቃውመዋል።
ይህ ቃል ወደ ድርጊት ከተሻገረ የሰላም ሂደቱን የሚያውክ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት የሚገታው መሆኑንም የመሀሙድ አባስ ቃል አቀባይ ናቢ አቡ ረድኒህ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የፍልስጤማውያኑ ፕሬዝዳንት ሙሀሙድ አባስ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች አማካሪ ማጅዲ ካሊድ በበኩላቸው አሜሪካ ከሽምግልና ሂደቱ ለመውጣት መወሰኗን የሚያሳይ ርምጃ ነው ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናትናዬሁ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባይሰጡም የትምህርት ሚኒስትሩ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ከተማ ከንቲባ ርምጃውን አድንቀው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሳውዳረቢያው ንጉስ ሰልማን ለዶናልድ ትራምፕ ስልክ በመደወል አጠቃላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ በኢየሩሳሌም ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ የሰላምሂደቱን ይጎዳል በማለት አሳስበዋል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የአረብ ሊግ ኢራን እንዲሁም ዮርዳኖስ ርምጃውን በማውገዝ አቋማቸውን ከገለጹ መንግስታት ውስጥ ተጠቃሽ ሆነዋል።
የካቶሊካውያኑ ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ መሰረት የኢየሩሳሌም ይዞታ በነበረበት እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ኢየሩሳሌም የክርስቲያኑም ፣የአይሁዱም፣የሙስሊሙም ከተማ ነች ሲሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ የኢየሩሳሌም መጨረሻ የሚወሰነው በቀጥታ ንግግር ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የሰላም ሂደቱን ወደፊት በማስቀጠል ችግሩ እንዲፈታ ጥሪ አቅርቧ።
ሩሲያና ቻይና በአካባቢው ቀውስ ያባብሳል ሲሉ ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል።
የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በጉዳዩ ላይ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት እንደሚያነጋግሩና በሀገራቸው ብሪታኒያ በኩል ግን የአቋም ለውጥ አለመኖሩን አስታውቀዋል።
እስራኤል ምስራቃዊውን የኢየሩሳሌም ክፍል ኣንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 በተካሄደው የእስራኤል አረቦች ጦርነት ከዮርዳኖስ በሃይል የወሰደችው መሆኑ ይታወቃል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ቤቶችን በመገንባት ወደ 200ሺ አይሁዶችን አስፍራለች።
ይህም ምስራቃዊ የኢየሩሳሌም ክፍል ፍልስጤማውያን የራሳቸው ይዞታ እንደሆነ በመግለጽ ሲሟገቱ ጉዳዩም ሲያወዛግብ ቆይቷል።
No comments:
Post a Comment