Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 13, 2018

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ መሪዎችን (የናፍቆት መልዕክተኞቻችንን) በጋራ እንቀበል ከአርበኞች ግንቦት 7 አቀባበል ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ መሪዎችን (የናፍቆት መልዕክተኞቻችንን) በጋራ እንቀበል
ከአርበኞች ግንቦት 7 አቀባበል ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ ፦
አዲስ አበባ !!
ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓም
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ “የመንግሥትና የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበት፤ የሀገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበት፤ ማኅበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታ” የማገዝ ተልዕኮ አንግቦ፤ ተልዕኮዉን ለማሳካት ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ ነድፎ በአገር ውስጥ በህቡዕ፣ በጎረቤት አገር በኤርትራ እና ኢትዮጵያዊያን በሚገኙባቸው አገራት በሙሉ በህቡዕና በግልጽ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
አርበኞች ግንቦት 7 ሁለገብ ትግልን የመረጠው በሁኔታዉ አስገዳጅነት እንጂ የሚፈልገው፣ አሳምሮ የሚያውቀው እና የሚናፍቀው በዜግነት ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ የፓለቲካ ፉክክር መሆኑ በተጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
አሁን በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ጅምር ንቅናቄያችን የታገለለት እና ሲናፍቀው የቆየውን በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፓለቲካ እና በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበት ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔዎችን ለመፍጠር የሚያመቻች በመሆኑ በውጭ አገራት ይገኙ የነበሩ አመራሮቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ጉዞ “ናፍቆት” ብሎ ሰይሞታል።
በዚህም መሠረት ከሀገር ውጪ የሚገኙ የንቅናቄው አመራሮችና አባላት ወደሚናፍቁት አገራቸውና ሕዝብ እና ወደሚናፍቁት የትግል ስልት ለመመለስ የቀራቸው ጊዜ በሳምንታት የሚቆጠር ብቻ ነው።
የናፍቆት መልዕክተኞችን ለመቀበል ከተቋቋሙ ኮሚቴዎች መካከልም ይህ የሀገር ውስጥ ኮሚቴ አንዱ ሲሆን ይህ ኮሚቴም ከዛሬ ጀምሮ የአቀባበል ሥነ ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ድረስ የሚኖሩ የአቀባበል ተግባራትን እንዲያስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በዚህም መሠረት ይህ የአቀባበል ኮሚቴ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ሥራውን መጀመሩን ያበስራል።
በመሆኑም
1 የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ወደሚናፍቁት አገርና የትግል ስልት ሲመለሱ የሚኖረው አቀባበል የደመቀ ለማድረግ በምናደርገው ጥረት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት እንድትተባበሩን፣
2 የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አባላትን ለመቀበል በተለያዩ መንገዶች ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ከኮሚቴው ጋር በመገናኘት የተቀናጀ ተግባር እንዲፈፀም አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ፣ እና
3 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በዕለቱ በተለመደው ሰላም ወዳድነቱና የዴሞክራሲ አጋርነቱ መሠረት በአቀባበሉ ላይ በመገኘት ለዲሞክራሲ ታጋዮች ያለውን ክብር እንዲገልፅ በትህትና እንጠይቃለን።
የናፍቆት መልዕክተኞች መግቢያ ቀንና ቀጣይ ፕሮግራሞችን በተከታታይ የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን።
የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች አቀባበል በዜግነት ላይ ለተመሠረተ ፓለቲካ፣ ለሰላም እና ለዲሞክራሲ ያለንን ናፍቆት መግለጫ እናድርገው።
አንድነት ኃይል ነው !
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !

No comments:

Post a Comment

wanted officials