ለላፉት ሁለት አስርት ዓመታት በስደት ላይ የነበሩት 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
በውጭ በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስና በአገር ውስጥ የነበረው ሲኖዶስ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ እርቀ ሰላም ከፈጠረ በኃላ ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር የተመለሱት፡፡
ሁለቱ ሲኖዶሶች በእርቀ ሰላሙ ስምምነት መሰረት ቃለ ውግዘታቸውን አንስተው በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ለመስራት ይፋ አድርገዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ቤተክርስቲያኒቷን በፓትርያርክነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቤተክርስቲያኗን የአስተዳደር ስራ ሲሰሩ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ደግሞ በጸሎት እና በቡራኬ ቤተክርስቲያኗን እንዲመሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ሁለቱ ፓትርያርኮች በሕይወት እስካሉ ድረስ በቤተ ክርስቲያቲያኗ ዘንድ የአባትነት ክብራቸው በእኩል ደረጃ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞችም በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ወደ አገራቸው ለተመለሱት አባ መርቆሪዎስና ሌሎች አባቶችም ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የአቀባበል ስነ ስርዓቱ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ድረስ የሸፍነ ነው፡፡
የፊታችን ሐምሌ 28ም ፣ በሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የተለያዩ እንግዶችን ጨምሮ ከ25 ሺህ ሰው በላይ ታዳሚ በሚገኝበት መድረክ ሁለተኛው የዕርቀ ሰላም እንደሚፈፀም ይጠበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment