የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር መገናኘታቸውና ፎቶ መነሳታቸው ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ መሆኑ ታወቀ።
ይህን ተከትሎም አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር የተነሱትን ፎቶ ከማህበራዊ ገጻቸው ላይ መሰረዛቸው ተሰምቷል።
ያያዙትንም ጽሁፍ አጥፍተውታል።
አለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን ቢቢሲ በድረገጹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባሰራጨው ጽሁፍ አቶ ሃይለማርያም ኮለኔል መንግስቱን ያገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተልከው ሊሆን ይችላል ሲል አስተያየቶችን መሰረት አድርጎ ዘገባውን አስፍሯል።
በዚምባቡዌ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመታዘብ ወደ ሐራሬ የተጓዙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያምን ያገኙት በዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ቤተመንግስት ውስጥ መሆኑም ተመልክቷል።
በስፍራው አብረዋቸው የነበሩት የሰላምና ግጭት ጥናት ተቋም ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ትዕግስት የሺዋስ የሁለቱ የቀድሞ መሪዎች ውይይት ቤተሰባዊ አይነት እንደሆነም በቲውተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝም ከቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር የተነሱትን ፎቶ በማያያዝ በማህበራዊ ገጻቸው መገናኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከፎቶው ግርጌ ባሰፈሩትም መልዕክት “ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር ተገናኝቻለሁ” ካሉ በኋላ የቀድሞ ርዕሰ ብሔርና ርዕሰ መንግስታት ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በኋላ በሃገራቸው ለሃገራቸው አስተዋጽኦ ማየት ምኞታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የአቶ ሃይለማርያምና የኮለኔል መንግስቱ ፎቶግራፍ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።
ለምስሉና ለኮለኔሉ ድጋፋቸውን የሰጡ የመኖራቸውን ያህል ኮለኔሉ ምህረት አይገባቸውም ለፍርድ ይቅረቡ የሚሉ አስተያየቶች እንዲሁም እስካሁን ይቅርታ ባልጠየቁበት ሁኔታ እሳቸውን ለመደመር መንቀሳቀሱ ተገቢ አይደሉም የሚሉ ትችቶችም ተንጸባርቀዋል።
በሌላ ወገን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በሃገር ወዳድነት ያንቆለጳጰሱም ጽሁፎች ታይተዋል።
በዚህ መልክ አወዛጋቢ ሆኖ የወጣውን ፎቶ ግራፍ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከማህበራዊ ገጻቸው ከነ አስተያየቱ መሰረዛቸው የአለም አቀፍ መገናኛ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
ቢቢሲም በድረገጹ በእንግሊዝኛ ባሰራጨው ጽሁፍ ውዝግቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ፎቶግራፉን ከማህበራዊ ገጽ ላይ ማንሳታቸውን በጽሁፉ አስፍሯል።
No comments:
Post a Comment